Skip to main content
x
‹‹የተረከብኩት ኃላፊነት የአገር ውክልናን ተቀብሎ ውጤት ከማስመዝገብም የበለጠ ነው››  ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት

‹‹የተረከብኩት ኃላፊነት የአገር ውክልናን ተቀብሎ ውጤት ከማስመዝገብም የበለጠ ነው›› ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት

በአይጠገብ ደማቅ ሳቋና ፍልቅልቅነቷ ዓለም የሚያውቃት አንጋፋዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ በ1984 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1992) ለአፍሪካ ሴት አትሌቶች ተምሳሌት የሆነችበት በኦሊምፒክ አኩሪ ድል አስመዝግባለች፡፡ በባርሴሎና ኦሊምፒክ በ10,000 ሜትር ዝናዋ የናኘው ደራርቱ፣ በዚሁ ብቻ ሳትገታ ለበርካታ ዓመታት በሩጫው ዓለም የኢትዮጵያ ሰንደቅና ክብር ከፍ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ከስምንት ዓመት ቆይታ በኋላ በሲድኒ ኦሊምፒክ እንደ ባርሴሎናው ሁሉ ተመሳሳይ ውጤት በማስመዝገብ የአገሯን ሰንደቅ ዓላማና ክብር ከፍ ያደረገች አንጋፋዋ አትሌት በእምባ ዘለላዎች የታጀበው ስሜቷ በብዙዎች ዘንድ አይረሴ ነው፡፡ በወቅቱ ከወሊድ ተነስታ ለብሔራዊ ውክልና መብቃቷ ቢያነጋግርም፣ የማታ ማታ በድል ሁሉንም ዝም ማሰኘት ችላም ነበር፡፡ እንዲህ ሲገነባ የቆየው የስፖርት ሜዳ ውሎዋ ከተደመደመ ከጥቂት ዓመታት ቆይታ በኋላ በስፖርቱ መድረክ የአመራርነት በትረ ሥልጣን፣ በተለይም በአትሌቲክሱ ስትበቃ ሁሉም በሙሉ ድጋፍ ያደረገላት ደራርቱ ቱሉ፣ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነቷ በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ለመሆን በቅታለች፡፡ በዓለም የውድድር መድረክ ያሳካችው በአመራርነት ዘመኗስ ምን ለማድረግ አቅዳለች? ደረጀ ጠገናው አነጋግሯታል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የመሪነት ሥፍራ ላይ በአብዛኛው በስፖርቱ ባሳለፉ ሙያተኞች ማለትም በአትሌቶች እጅ ይገኛል፡፡ ከተወዳዳሪነት ወደ አመራርነት መምጣት በአንቺ እንዴት ይገለጻል?

ደራርቱ ቱሉ፡- የአመራርነት ሚና ቀላል ሊሆን እንደማይችል እገምታለሁ፡፡ ያም ሆኖ ሁላችንም በስፖርቱ ያሳለፍን እንደመሆናችን በአትሌቲክሱ አካባቢ በተለይም በክለቦች፣ እኔን ጨምሮ በተወዳዳሪዎችና ሙያተኞች ምርጫ ላይ ሲነሱ የቆዩ ችግሮች ሙሉ በሙሉም ባይሆን ስለምናውቀውና ስለምንተዋወቅም፣ በተወሰነ መልኩ መፍትሔ እናመጣለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብን ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ይህን ካልኩ በሒደት በምንወስደው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የሚደሰቱ የመኖራቸውን ያህል የሚያኮርፉ እንደሚኖሩም ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም የሰው ፍላጎት ብዙ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን መርሕ አድርገን ለመንቀሳቀስ የምንሞክረው ግለሰቦችን ለማስደሰት ወይም ለማስከፋት ብለን ሳይሆን ለስፖርቱ ዕድገትና ልዕልና ነው፡፡ ‹‹ከልብ ካለቀሱ›› እንደሚባለው፣ አመራሩ አትሌቱና ሌሎችም የሚመለከተን አካላት ስፖርቱን ማዕከል አድርገን በአንድ ልብ ከተንቀሳቀስን ውጤታማ የማንሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡

ሪፖርተር፡- በስፖርቱ ሙያውን ለባለሙያተኛው በሚለው አትሌቲክሱ በብዙ መልኩ ተሳክቶለታል፡፡ አንቺ የዚሁ አካል በመሆንሽ ስሜቱ ምን ይመስላል?

ደራርቱ ቱሉ፡- ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ስሜቱ ስፖርቱ ላይ ካለው ጫና አኳያ ከባድ ነው፡፡ ግን ደግሞ አልጋ በአልጋ የሚሆን ምንም ነገር ስለሌለ ጉባዔውም ሆነ ኅብረተሰባችን በሙሉ ድጋፍና እምነት የሰጠን ኃላፊነት ስለሆነ ስሜቱን በውጤት ለማጣጣም በግሌ ዝግጁ ነኝ፡፡ እዚህ ላይ ሳልናገር የማላልፈው አትሌቶች ስፖርቱ ይመለከተናል፣ ከተወዳዳሪነት ባለፈ የመሪነት ሚናም ሊኖረን ይገባል ለሚለው ጥያቄያችን የተሰጠን አጥጋቢ ምላሽ መሆኑን ነው፡፡ በክብር የተሰጠንን ይህን ተቋም ክብር ላለው ውጤትና ሥርዓት ማብቃት ከምስጋና ጋር የእኛ ድርሻ ነው፡፡ ምክንያቱም መንግሥትም ሆነ ጉባዔው ይህን ሲያደርጉ ከእኛ የሚጠብቁት እንደሚኖርም እናምናለን፡፡ ትልቅ ኃላፊነትም ነው ብለን ነው የምንወስደው፡፡ የተረከብኩት ኃላፊነት የአገር ውክልናን ተቀብሎ ውጤት ከማስመዝገብም የበለጠ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ በፌዴሬሽኑ ለዓመታት ሲንከባለሉ ዛሬ ላይ የደረሱ የአሠራር ክፍተቶች መኖሩ ይታመናል፡፡ ለእናንተ አትሌቶቹ ወደዚህ ኃላፊነት መምጣት አንዱ ምክንያትም ይኼ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኃላፊነቱ እንዴት ይገለጻል?

ደራርቱ ቱሉ፡- እንደ ተባለው ስፖርቱ በራሱ ምንም ዓይነት ድብቅ ነገር ስለሌለው ውስብስብ ችግሮች ያሉበት ነው ብሎ ለመውሰድ ቢያስቸግርም፣ ነገር ግን ብዙ ፍላጎት ያለበት በመሆኑ ውስብስብ በሚለው እስማማለሁ፡፡ ለዚህ ከእኔ የ30 ዓመት የስፖርት ተሞክሮ ስነሳ በነዚህ ዓመታት የስፖርት ጉዞዬ ያለ ሀሜት ነገሮች በቀናነት ሲታዩ አልተመለከትኩም፡፡ የዓለም ዋንጫ፣ ኦሊምፒክና ሌሎችም ውድድሮች ሁሉም ያለ እሮሮና ሀሜት እንዲሁም ያለ ውዝግብ ያለፈበት ጊዜ ብዙም ትዝ አይለኝም፡፡ በአትሌቶች፣ በአሠልጣኞች ምርጫና ተያያዥ ችግሮች የሚስተዋሉ ቆይቷል፡፡ ይኼ ወደፊትም እንደሚኖር እጠብቃለሁ፡፡ ለዚህም ነው ቀደም ሲል በሥራ ሒደት የሚደሰቱ የመኖራቸውን ያህል የሚከፉ ስለመኖራቸው ጭምር ለመናገር የሞከርኩት፡፡ በዚህ መሀል የሚያስማማን ግን ይኖራል፡፡ አቅምና ብቃትን እንዲሁም ማዕከላዊነትን የጠበቀ ሥራ ለአገራዊው ፍላጎታችን የግድ ነው፡፡ የእኔ እምነትም ይኼ ነው፡፡ ይህም በፍላጎትና ምኞት ብቻ ሳይሆን የእረፍት ቀን ሳይቀር ጠንክሮ መሥራት የሚጠይቅ ነው፡፡ ምክንያቱም እኔም ሆንኩ የተቀሩት የሙያ ባልደረቦቼ ዳር ቆመን በነበረ ጊዜ ተናግረናል፣ ተችተናል፣ አሁን ደግሞ ኃላፊነቱ ተሰጥቶናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በመነሳት በአንቺም ሆነ በሌሎች የሙያ ባልደረቦችስ ኃላፊነቱ ቢሰጠን የሚለው ጉዳይ አሳስቧችሁ በቅድሚያ ተወያይታችሁ ታውቃላችሁ?

ደራርቱ ቱሉ፡- በአጋጣሚ ብቻ ሳይሆን ፕሮግራም ይዘን ተነጋግረናል፡፡ ምክንያቱም ኃላፊነቱ ከባድ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ እምነት ተጥሎብን እስከ መጣን ድረስ አሁንም ክብር ያለው፣ ለትውልድ የሚተላለፍ ጥሩ ሥራና የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት  ለሰከንድ ወደ ኋላ የምንልበት ጉዳይ እንዳልሆነ ጭምር ስምምነት ላይ ደርሰን ነው ቀደም ሲል ኃላፊነቱ ሊሰጠን ይገባል ስንል ጥያቄ ስናቀርብ የነበረው፡፡

ሪፖርተር፡- ስፖርት ውጤት ነው፡፡ ለዚህ ከቀደምት አትሌቶች ስኬት መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ በመነሳት ክፍተት ብለን ለምናነሳቸው ምክንያቶች መንስዔ የምትያቸው ካሉ በግልጽ ብትነግሪን?

ደራርቱ ቱሉ፡- ከውጤትም በላይ አንድ ተቋም የሚመራበትና የሚተዳደርበት ደንብና መመርያ እንዳለው ይታመናል፡፡ ይሁንና እነዚህ ሁሉ እንከን አልባና የወጣላቸው ናቸው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ ወደፊትም ቢሆን በዚህ ረገድ ፍፁም የሆነ ነገር ይኖራል የሚል እምነት አይኖረኝም፡፡ ሌላው ቀርቶ የብቃት ደረጃው የወጣለት ብለህ ትልቅ እምነት የጣልክበት አትሌት በ11ኛው ሰዓት ያልተጠበቀ ችግር ይገጥመዋል፡፡ በዚያን ጊዜ በሚወሰዱ የማስተካከያ ዕርምጃዎች ተገቢው ሰው ‹‹እኔ ነኝ፤ አይደለህም›› በሚል ያልተጠበቀ የአሠራር ክፍተት ይገጥማል፡፡ እንደ ምሳሌ ይህን አነሳሁ እንጂ ሌሎችም በርካታ ቴክኒካል ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ብዙ አትሌት ያስመረጠ የሚሉና ሌሎች ፍላጎቶች ስለሚኖሩ በዚህ ረገድ ወደፊትም ፍፁም የሚባል ነገር እንደማይኖር መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ችግሮቹን ማጥበብ ግን ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሁሉም ድርሻውን ከወሰደ ማለቴ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከፍላጎት ባሻገር ክፍተቶችን ሊያጠቡ የሚችሉ በፌዴሬሽኑ የተሟላ ሰብዕና ያለው ደንብና መመርያዎች ይኖራሉ ብለሽ ታምኛለሽ?

ደራርቱ ቱሉ፡- አሁን ላይ ለዚህ በቂ ምላሸ ሊሰጥ የሚችል በተቋሙ ውስጥ ደንብና መመርያ ለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሆኖም ግን ስለአትሌቲክስ ስናወራ የአገርና የሕዝብ ማንነት ጉዳይ አድርጎ መውሰድ እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ የደራርቱ ጉዳይ ከእነዚህ ሁለት ነገሮች ሊቀድም አይገባም፡፡ እነዚህን ታሳቢ ያደረገ ደንብና መመርያ እንደሚኖር እገምታለሁ፡፡ ከሌለም እንዲኖር ማድረግ ቀጣዩ የእኛ ኃላፊነት ነው የሚሆነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ብዙ የሚስተካከሉ ነገሮች እንደሚኖሩም መታወቅና ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ከውጪ ሆነሽም ቢሆን ወቅታዊውን የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ቅርፅና ይዘት እንዴት ትገልጪዋለሽ?

ደራርቱ ቱሉ፡- በእኔ ደህና ነው የሚለውን መውሰድ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በእርግጥ እኔን ጨምሮ ሌሎች ይህን ኃላፊነት ከመውሰዳችን በፊት የምናውቃቸውና እንሰማቸው፣ የነበሩ ክፍተቶች የተቀረፉበት እንከን አልባ ቅርፅና ይዘት ያለው ተቋም ነው ብዬም አልወስድም፡፡ ይኼ ደግሞ በሒደት እንጂ በአንድ ጀምበር የሚስተካከልና የሚቀረፍም ነው ብዬ አላምንም፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ወቅት አትሌቲሱ ከኋላ ታሪኩ በመነሳት ውጤቱ ወርዷል በሚል ጠንካራ ትችት እየገጠመው ይገኛል፡፡ ይህ ባለበት ወቅት ወደዚህ ተቋም ለዚህ ኃላፊነት መብቃት ዕድለኛነት አድርገሽ ትወስጅዋለሽ?

ደራርቱ ቱሉ፡- ዕድለኛነት ነው፣ አይደለም ወደ ሚለው አስተያየት ከመግባቴ በፊት  አትሌቲክሱ ቀደም ሲል ከነበረው ደረጃ አኳያ አሁን ላይ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ነው ለማለት ለማናችንም ያስቸግራል፡፡ ከአንድነቱና ብሔራዊ ክብሩ ጭምር የቀደመው ለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እዚህ ላይ በዚህ ብቻ ሳንወሰን ያስፈልጋል የሚል እምነትም አለኝ፡፡ ምክንያቱም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መነጋገር እኔ ኦሮሚያ ስለወከለኝ፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ ደግሞ አዲስ አበባ ስለወከለው በዚያ አስተሳሰብ ብቻ መሄድ የሚጠበቅብን አይመስለኝም፡፡ ይኼ በተለይም በአሁኑ ወቅት ከስፖርቱ መርህ ውጪ አትሌቲክሱን ከእምነትና ከብሔር ጋር በማገናኘት የምንቀሳቀስ አካላት ልንታረም ይገባል፡፡ የስፖርቱ መገለጫ አንድነትና ፍቅር ነው፡፡ አንድ ሰው ኦሮሞ ወይም አማራ በመሆኑ ብቻ ከአሠራርና ከመርሕ ውጭ ተሂዶ ተጠቃሚ ወይም ተጎጂ እንዲሆን የሚደረግበት አካሄድ መወገዝ ይኖርበታል፡፡ ማሰብ የሚኖርብን አገርንና ስፖርቱን በሚጠቅም መልኩ መሆን እንደሚኖርበት ነው የሚገባኝ፡፡ 

ሪፖርተር፡- አትሌቲክሱ ቀደም ሲል ከነበረው አንፃር አሁን ላይ ከአገርና ከግል ክብር በላይ ዋነኛ የፋይናንስ አማራጭ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ እንደነዚህ የመሰሉ አመለካከቶች ተቀባይነት ሊኖራቸው ይችላል ብለሽ ታምኛለሽ?

ደራርቱ ቱሉ፡- አንድነቱ፣ ፍቅሩ፣ ክብሩና ሌሎችም እንደተጠበቁ ስፖርቱ እየሰጠ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አስጠብቆ ለመቀጠል ችግሩ ምንድነው? በእርግጥ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ እንደ ትልቅ ሥጋት የሚታይ እውነትም ያለው ነገር አለ፡፡ ከሩጫው ከሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በተጓዳኝ የግለሰቦች ፍላጎት ለአንድነቱና ለአገራዊ ክብሩ አደጋ እንዳለው እገምታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከአትሌቲክሱ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በኃላፊነት በማገልገል ላይ ነሽ፡፡ ወንበሩ ምቾት አለው?

ደራርቱ ቱሉ፡- ምቾት አለው የለውም የሚለውን ለማወቅ ጊዜው ገና ነው፡፡ እስካሁን ባለው ከሆነ በኦሊምፒክ መሥራት ያለብኝን ያህል ሠርቻለሁ የሚል እምነት የለኝም፡፡ በእርግጥ ጅምሮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ኃላፊነቱን በተረከብሽ ማግሥት ከሌሎች የሥራ ባልደረቦችሽ ጋር በመሆን ክልሎችን ጎብኝታችኋል፡፡ ግብረ መልሱ እንዴት ነበር?

ደራርቱ ቱሉ፡- የክልሎቹ ከፍተኛ አመራሮች ስፖርቱን ለመደገፍ ቁርጠኝነቱ ያላቸው መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ ጉብኝት ቀደም ባሉት ዓመታት ያልነበረ ከመሆኑ አኳያ፣ የክልል አመራሮች አብረን መሥራት እንዳለብን፣ እያንዳንዱ ክልል ተሰጥኦውን አሟጦ እንዳልተጠቀመ፣ በቀጣይም ሁሉም የድርሻውን ወስዶ ወጣቱ በተሻለ በስፖርቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አቅጣጫ ማስቀመጥና በሥራ መተርጎም እንደሚያስፈልግ ነው መግባባት ላይ የተደረሰው፡፡ ከዚህ በመነሳት ኃላፊነቱ ባንዲራ ለብሰህ ከምታስመዘግበው ውጤት በላይ ቀጣዮቹን ባንዲራ ለባሾችን ማፍራት የሚጠይቅ በመሆኑ የሚያስተኛ አጋጣሚ እንዳልሆነም በግሌ የተረዳሁበት መድረክ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ በሁሉም ክልሎች አንቺ ከነበርሽበት ጊዜ  በመነሳት የአሁኑን በንጽጽር እንዴት ትገልጭዋለሽ?

ደራርቱ ቱሉ፡- ልዩነቱ በጣም ሰፊ ነው፡፡ በውድድር በነበርኩበት ወቅት አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ ዓለማት ውድድሮችን ባደረኩባቸው አገሮች ከስታዲየሞች ጀምሮ የምመለከታቸው ዘመናዊ ማዘውተሪያዎች መቼ ይሆን በኢትዮጵያ የምመለከታቸው እያልኩ እመኝ ነበር፡፡ አሁን ላይ እነዚያ ዘመናዊ ስታዲየሞችና ማዘውተሪያዎች በኢትዮጵያ ዕውን ሆነዋል፡፡ በክልሎቻችን ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ሁለገብ ዘመናዊ ስታዲየሞች ባለቤት ሆነናል፡፡ በእኔ ጊዜ እነዚህ አልነበሩም፡፡ ከዚህ በመነሳት መንግሥት ለስፖርቱ ምን ያህል ትኩረት እየሰጠ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ መሠረታዊ የሚባል የመንገድና የጤና፣ እንዲሁም የንፁህ ውኃና የመብራት አገልግሎት ባልተሟላበት ነው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለስፖርቱ እየወጣ ያለው፡፡ በዚህ ረገድ ስፖርቱ አሁን ላይ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ተራምዷል ማለት እችላለሁ፡፡ የሚቀረው የስፖርቱ ባለሙያተኞችና ኃላፊዎች ምን ሠራን የሚለው ነው፡፡ ይኼ አትሌቲክሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በእግር ኳሱ፣ በቦክሱ፣ በብስክሌትና በሌሎችም ስፖርቶች ምን ያህል ተተኪዎችን አፈራን? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ ወቅት ተወዳዳሪ የነበራችሁ አትሌቶች ዛሬ ደግሞ አወዳዳሪያችሁ ለነበረው ተቋም አመራር ሆናችኋል፡፡ የማያግባቡ ውሳኔዎች ቢገጥማችሁ፣ በተለይ በአንችና በኃይሌ መካከል ያለው ቅርርብ ስለሚታወቅ ምን እንጠብቅ?

ደራርቱ ቱሉ፡- ይኼ ሥራ ነው፡፡ ከኃይሌ በተጨማሪ ከሁሉም አትሌቶች ጋር ያለኝ ግንኙነት ጥብቅ ነው፡፡ ሁሉም ያከብሩኛል እኔም አከብራቸዋለሁ፡፡ ይኼ ግንኙነታችን ግን አሁን ባለንበት የኃላፊነት ድርሻ በፍፁም ቦታ አይኖረውም፡፡ ቦታ የሚኖረው የተሻለውና የተሻለው ሐሳብ ብቻ ነው፡፡ ኃላፊነቱ የአገርና የሕዝብን አደራ ነው፡፡ መግባባትና መሥራት ካለብን ስፖርቱ በሚፈልገው ጉዳይ ላይ ብቻ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እኔን ጨምሮ የሚሠራ ሰው መሳሳቱ ግድ ነው፡፡ አሁን በተሰጠን ኃላፊነት ልክ ለመሥራት ዝግጁነታችን ለአፍታም አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን የምንፈልገው አትሌቲክስ የተሻለ ውጤት ሊያመጣ የሚችለው፣ በፌዴሬሽኑ አመራሮች ጥረት ብቻ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ መንግሥት፣ ክልሎች፣ ክለቦችና ሌሎችም ባለድርሻ ነን ብለን የምናስብ የድርሻችንን መውሰድ ከቻልን ግን የማንደርስበት ስኬት አይኖርም፡፡ ስህተታችን በጓሮ ሳይሆን ፊት ለፊት ሊነገረን ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት የቀድሞ ክለብሽ ፌዴራል ማረሚያ ቤት ስፖርት ክለብን ጨምሮ በሦስት ትልልቅ ኃላፊነት ትገኛለሽ፡፡ የትኛውን ታስቀድሚያለሽ?

ደራርቱ ቱሉ፡- የኦሊምፒኩን ለኦሊምፒክ፣ የአትሌቲክሱን ለአትሌቲክ፣ ለዚህ ደረጃ ያበቃኝ የክለቤን ጉዳይም እንደየባህሪያቸው ካልሆነ መደበላለቅ አልፈልግም፡፡