Skip to main content
x
ደርባ ሚድሮክ ሁለተኛውን ፋብሪካ ለመገንባት ድርድር እያካሄደ ነው
በ351 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው የደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ

ደርባ ሚድሮክ ሁለተኛውን ፋብሪካ ለመገንባት ድርድር እያካሄደ ነው

የሼክ መሐመድ አል አሙዲ ግዙፍ ኩባንያ ደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ሁለተኛውን የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር እየተደራደረ ነው፡፡ የሚድሮክ ሊቀመንበር ሼክ አል አሙዲ በሳዑዲ ዓረቢያ በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሏቸው ኩባንያዎች ከዕለት ተዕለት ሥራቸው ባሻገር በወጣላቸው ስትራቴጂ መሠረት ሥራቸውን እየሠሩ ነው ተብሏል፡፡

ደርባ ሚድሮክ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፣ በኦሮሚያ ክልል ጫንጮ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ደርባ አካባቢ የሲሚንቶ ፋብሪካ ባለቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡

ደርባ ሚድሮክ ሁለተኛውን ግዙፍ ፋብሪካ በዚሁ አካባቢ የመገንባት ዕቅድ ያወጣ ሲሆን፣ ይህንኑ ዕውን ለማድረግ ግንባታውን ሊያካሂዱ ከሚችሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቴክኖሎጂና በፋይናንስ ድርድር እያደረገ መሆኑን የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ኃይሌ ጨምረው እንደገለጹት፣ ደርባ ቁጥር ሁለት ሲሚንቶ ፋብሪካ በቀን 80 ሺሕ ኩንታል ሲሚንቶ የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡

ደርባ ሲሚንቶ የመጀመርያውን የሲሚንቶ ፋብሪካ በ351 ሚሊዮን ዶላር ገንብቶ ኅዳር 2004 ዓ.ም. ማስመረቁ ይታወሳል፡፡ ይህ ፋብሪካ በዓመት 25 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው የአውሮፓ ቴክኖሎጂ ውጤት ነው፡፡

ይህ የመጀመርያው ፋብሪካ 351 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት ሲሆን፣ ባለቤቱ ሼክ አል አሙዲ 100  ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርገውበታል፡፡ የተቀረው 251 ሚሊዮን ዶላር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽንና ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በብድር የተገኘ ነው፡፡

አቶ ኃይሌ እንደሚሉት ለሁለተኛው ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚሆን የፋይናንስ ችግር አይኖርም፣ ሁሉም አማራጮች እየታዩ ነው፡፡

ሼክ አል አሙዲ በእስር ላይ መሆናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ድርጅቶች ላይ የሚፈጠር ተፅዕኖ አይኖርም ያሉት አቶ ኃይሌ፣ እዚህ ያሉ ድርጅቶች በሙሉ ውክልና ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡

‹‹አዳዲስ ስትራቴጂዎች  ላይ ካልሆነ በስተቀር፣ ሁሉም ድርጅቶች በወጣላቸው  ስትራቴጂ መሠረት እየተመሩ ሥራቸውን እያከናወኑ ነው፤›› ሲሉ አቶ ኃይሌ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡