Skip to main content
x
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስመራጭ ኮሚቴ የዕጩዎችን ዝርዝር ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስመራጭ ኮሚቴ የዕጩዎችን ዝርዝር ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በታኅሣሥ ወር አጋማሽ የቀጣዩን አራት ዓመት የፌዴሬሽኑን ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ያከናውናል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ኅዳር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ለምርጫ የሚቀርቡትን ዕጩ ተወዳዳሪዎች ዝርዝርም ይፋ አድርጓል፡፡ ሁለት ተወዳዳሪዎች ከዕጩ ተወዳዳሪነት ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

በአፋር ሰመራ ከተማ ለሚደረገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አምስት ዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ ለሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ደግሞ 16 ዕጩ ተወዳዳሪዎች ይቀርባሉ፡፡

አስመራጭ ኮሚቴው ይፋ ባደረገው ዝርዝር መሠረት ለፕሬዚዳንታዊው ምርጫ አቶ ጁነዲን ባሻ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ አቶ ተካ አስፋው ከአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ከደቡብ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና አቶ ዳግም መላሸን ዋኞክ ከጋምቤላ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡

ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ደግሞ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ከአዲስ አበባ፣ አቶ ሰውነት ቢሻው ከአማራ፣ አቶ አበበ ገላጋይ ከድሬዳዋ አስተዳደር፣ አቶ ከማል ሁሴን ከኦሮሚያ፣ ዶ/ር ኃይሌ ኢቲቻ ከኦሮሚያ፣ አቶ ኢብራሂም መሐመድ ከሐረሪ፣ አቶ አብዱዛቅ ሀሰን ከሶማሌ፣ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አቶ አሊሚራህ መሐመድ ከአፋር፣ ኮ/ል አወል አብዱራሂም ከትግራይ፣ ዶ/ር ሲራክ ሀብተማርያም ከአማራ፣ አቶ ወልደ ገብርኤል መዝገቦ ከትግራይ፣ አቶ አሥራት ኃይሌ ከአዲስ አበባ፣ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ከደቡብ፣ ዶ/ር ቻን ጋትኮት ከጋምቤላና ኢንጂነር ኃይለየሱስ ፍሥሐ ከአዲስ አበባ ሆነዋል፡፡

ከተወዳዳሪነታቸው የተሰረዙት አቶ ሙራድ አብዲ ከሐረሪና አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው ከኢትዮጵያ ዳኞች ማኅበር መሆናቸው ታውቋል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ከዕጩ ተወዳዳሪነት ውጪ ስለሆኑት ግለሰቦች ምክንያት ብሎ ያቀረበው ዝርዝር ማብራሪያ የለም፡፡