Skip to main content
x
ብጥብጥና ሁከት ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› የሆነበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ
የወልድያ ስታዲየም

ብጥብጥና ሁከት ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› የሆነበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ

  • መንግሥት የመፍትሔው አካል ሊሆን እንደሚገባ ተጠይቋል

በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ የሰው ልጆች በአንድ መድረክ ተገናኝተው በአንድ ቋንቋ ከሚግባቡባቸው መሣሪያዎች እግር ኳስ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ግለሰቦች በፈጠሯቸው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ለዓመታት ሰላም ርቋቸው የቆዩ አገሮችና ሕዝቦች በእግር ኳስና እግር ኳስ በፈጠራቸው ከዋክብት አማካይነት አንድ ሆነው የሰላምን ትርጉም እንዲሰብኩ ምክንያት እየሆነም ይገኛል፡፡

በዚህ መርሕ በተለያዩ መንግሥታዊ መዋቅሮች አልፎ ዛሬ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ እግር ኳስ፣ በምሥረታ ቀዳሚ ከሚባሉ የአፍሪካ አገሮች ይጠቀሳል፡፡ አሁን አሁን የዕድሜውን ያህል ዕድገት እንዳላስመዘገበ፣ እንዲያውም የነበረውን እንኳ ማስጠበቅ አልተቻለም በሚል በርካቶች ይተቹታል፡፡ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ በዋናነት ከ2008 የውድድር ዓመት ጀምሮ እግር ኳሳዊ ባህሪ በሌለው በ‹‹ወንዜነት›› ልክፍት መነሻነት የብጥብጥና ሁከት ቀጣና ሆኖ የእግር ኳሱን ውድቀት በማፋጠን ላይ ይገኛል፡፡

ይባስ ብሎ አሁን ላይ ክቡር የሆነው የሰው ልጆች ሕይወት የሚቀጠፍበት፣ ከፍተኛ ለሆነ የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት ውድመት ጭምር ምክንያት እየሆነም ይገኛል፡፡

ለዚህ በተጠያቂነት ደረጃ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቢሆንም፣ የዜጎችን ሰላም የመጠበቅ ኃፊነት ግን መንግሥታዊ አካሉም ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ የሚናገሩ አሉ፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በወልድያ ከተማ እንደሚካሄድ ፕሮግራም ተይዞለት፣ ነገር ግን የወልድያ ከተማና የመቐለ ከተማ ቡድኖች ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከጠዋቱ 3.30 ጀምሮ በተቀሰቀሰው ብጥብጥና ሁከት ጨዋታው ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ አወዳዳሪው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ጨዋታው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑን አስታውቋል፡፡ የዲሲፕሊን ጥሰቱን አስመልክቶ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በፌዴሬሽኑ የተላለፈ ውሳኔ የለም፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው እንደ አንዳንድ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ከሆነ፣ ጉዳዩ ከሜዳ ውጪ የተፈጸመ በመሆኑ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ጭምር ዝርዝር ነገሮችን መመልከት ያስፈልጋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እየሄደበት ያለውን አካሄድ የሚቃወሙና ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የሕግ ባለሙያዎች በበኩላቸው የአገሪቱ እግር ኳስ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያስተናገደ ለሚገኘው ሁከትና ብጥብጥ በመንስዔነት ሊነሳ የሚገባው ተቋሙ የሚተዳደርበትን ደንብና መመርያ መሠረት ያደረገ ወጥ የሆነ የዲሲፕሊን ውሳኔ ማስተላለፍ አለመቻል እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡

እንደ ሕግ ባለሙያዎች ከወልድያ ከተማና ከመቐለ ከተማ ጨዋታ አስቀድሞ በተለያዩ የክልል ከተሞች ጨዋታዎች ተደርገው፣ የጥፋቱ የመጠን ጉዳይ ካልሆነ ተመሳሳይ የዲሲፕሊን ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡ ለመጥቀስ ያህልም የ2010 ዓ.ም. የፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብ ዓዲግራት ላይ ወልዋሎ ዓዲግራትና ፋሲል ከተማ መካከል በተደረገው  ጨዋታ በደጋፊዎች አማካይነት በተፈጠረ አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ በሁለቱም በኩል ጉዳት መድረሱ ይታወቃል፡፡

ይሁንና አወዳዳሪው አካል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወደፊቱን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ አጥፊውን አካል በመለየት አስተማሪ የሆነ የዲሲፕሊን ዕርምጃ መውሰድ ሲኖርበት፣ ነገር ግን ዝምታን መርጦ ቆይቷል፡፡ አሁንም የጥፋቱ የመጠን ጉዳይ ካልሆነ የአዲስ አበባ ስታዲየምን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች በተደረጉ ጨዋታዎች እግር ኳሳዊ ባልሆኑ ምክንያቶች የዲሲፕሊን ጥሰቶች ሲፈጸሙ ታይቷል፡፡ የዲሲፕሊን ጥሰቶች ሲከሰቱ ጉዳዩን ተከታትሎ ውሳኔ የሚሰጠው የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ፣ ውሳኔ ሲያሳልፍ፤ አንዳንዱ ውሳኔ በፌዴሬሽኑ አመራሮች መልካም ፈቃደኝነት እንዲሻር ሲደረግ፣ አንዳንዱ ደግሞ የውሳኔው አፈጻጸም ግማሽ ላይ እንኳ ሳይደርስ ውሳኔ በውሳኔ እንዲሻር የሚደረግበት አሠራር ስለመኖሩ ጭምር የሕግ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡

ብዙዎቹ ክለቦችም ሆነ የክለብ አመራሮች ተፈጻሚ የማይሆን የገንዘብ ቅጣት ሲጣልባቸው ቆይቷል፡፡ ይሁንና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በቅርቡ በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ፣ የተቋሙ የፋይናንስ ሪፖርት በውጪ ኦዲተር ይፋ በሆነበት ወቅት፣ ፌዴሬሽኑ ካስተላለፈው የገንዘብ ቅጣት ገቢ የሆነው ኢምንት እንደነበር  ተገልጿል፡፡ በዚህም ከጉባዔው አባላት አንዳንዶቹ ከሪፖርቱ መረዳት እንደሚቻለው ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የማስፈጸም አቅም ውስንነት እንዳለበት ጭምር ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› ሲሉ አስተያየታቸውን የሚቀጥሉት እነዚህ የሕግ ባለሙያዎች፣ እንዲህ ዝርክርኩ በወጣ የእግር ኳስ አስተዳደር እምነት ሊጣል እንደማይገባና የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታ ያለበት መንግሥት ቸል ማለት እንደሌለበት ይናገራሉ፡፡ ምክንያት የሚሉት ደግሞ የአገሪቱ ዜጎች መሠረታዊ የሚባሉ መሠረተ ልማቶች ማለትም ጤና፣ ትምህርትና መንገድ የመሳሰሉ ሙሉ በሙሉ ባልተሟሉበት 99 በመቶ የመንግሥትን ቋት በሚጠይቀው እግር ኳስ ውድቀቱ አንሶ ክቡር የሆነው የሰው ሕይወትና ንብረት መጥፋትና መውደም ምክንያት ሲሆን መመልከት እንደሚያሳፍር ነው ያብራሩት፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ከሆነ፣ እግር ኳሱን መነሻ በማድረግ እየተከሰተ ያለው ሁከትና ብጥብጥ ከጥፋቱም አልፎ ታዳጊ ወጣቶች በቀጣይ ለሚኖራቸው አገራዊ ፋይዳ ትርጉም እንዳይኖራቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጭምር ይሠጋሉ፡፡ ለዚህ በማሳያነት የሚያነሱት በስፖርት ሜዳዎች ግርግርና ሁከት ሲፈጠር በአብዛኛው ከፊት ቀድመው የሚታዩት እነዚሁ ታዳጊ ወጣቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም ፌደሬሽኑም ሆነ መንግሥት ችግሩ ተከስቶ የዚህን ያህል የሰው ሕይወትና ንብረት ጠፍቷል፣ ወድሟል የሚለውን ሪፖርት ከማድረጋቸው በፊት፣ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ከመነሻው በመመልከት ጥፋቱንና ሥጋቱን ሙሉ በሙሉ እንኳ ባይሆን አደጋ በማይኖረው መልኩ ለመቀነስ መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸውም ይገልጻሉ፡፡