Skip to main content
x

ትንፋሽ አጠረን እኮ?

ሰላም! ሰላም! ባሻዬ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት በትዊተር እንደሚጀመር ታይቶኛል ብለው አካውንት ከፈቱና አረፉት፡፡ “በአርበኝነቱ ዘመን ቢሆን ዝናር እንታጠቅ ነበር፡፡ ጊዜው ግን በቃላት መራገጥ ሆኗል። ታዲያ ማን ተራግጦ ማን ይቀራል?” አሉኝ መደነቄን ዓይተው፡፡ ‹‹እየሩሳሌምን ሳላይ ሞት አይቀድመኝም፤›› የሚሉት ባሻዬ፣ የትራምፕን ፈለግ መከተል ከጀመሩ እንግዲህ ማን ቀረ አትሉም? ወይ ፍልስጤም ያልሰማችው ጉድ እያልኩ አሥር ጊዜ ሳጉረመርም ማንጠግቦሽ ሰምታኝ፣ “በል ለእኔም ትዊተር አካውንት ክፈትልኝ” አትለኝ መሰላችሁ? “ማን እንደሚዘጋው የማላውቀውን በር እኔ የምከፍተው ምን በወጣኝ ነው?” ብዬ ፈትልክ አልኩኝ፡፡ “ሐሜት ‹ዲጂታላይዝድ› በሆነበት ጊዜ፣ ትልቅ ትንሹ ሳይተዋወቅ ሳይከባበር በቻት በሚንጫጫበት በዚህ ጊዜ፣ አንተ ስለአዘጋጉ ምን አገባህ? ክፈት ስትባል መክፈት ነው፤” ብሎ ደግሞ ማን ይወቅሰኛል የባሻዬ ልጅ፡፡

ኧረ የት አገር ልድረስ አለ አሉ ኤሊ። መሬት ዝርግ ናት ብሉ ጉዞ ጀምሮ ነው አሉ፡፡ ልክ እንደ እኔ ማለት ነው፡፡ “እና የተረፈኝ ድካም ብቻ ሆነ፤” ብሎ ምሬቱን ለንስር ቢያጫውተው፣ “ድንጋይ ተሸክመህ ማንን ታማለህ?” ብሎ ተርቦት በረረ፡፡ አሁን ይኼ ንግርት ከዲጂታሉ ዓለም ጋር በምን ይገናኛል ካላችሁ እግዲህ፣ ያ ንስር አሞራ የብዙ ኤሊዎችን አድካሚ ጉዞ ለመግታት ወጥኖ ከደመና በላይ ከባህር በታች የሚጓዝ መረብ ለኤሊ ልጆች ገልጦላቸው ታገኙታላችሁ፡፡ መቼም በቅኔ በተጠመቀ አገር የንስርን ፍቺ የኤሊን ትርጓሜ ልግለጥ ብል ስድብ ነው፡፡ እና ይኼው ሰው ሳንሮጥ እየደከመው ሳይበር እያላበው እንዲያው በቁጭታ የተፈጥሮን ገጽታ አጥፍቶ የማይዳሰስ የቃላት ማኅበር ሲሳተፍ ውሎ ለማደር ባለአካውንት መሆን ጀመረ እላችኋለሁ፡፡ ታሪኬን መልሱ አካውንት ክፈቱ ለማለት ነው ባጭሩ!

እንግዲህ ዘመኑ የቻትም አይደል? እንጫወተው እስኪ፡፡ አንድ አይሱዙ ያሻሻጥኩለት ደንበኛዬ በድንገት፣ “የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች ልምምድ ከምን ደረሰ?” ብሎ ጠየቀ፡፡ “እኔ ምን አውቃለሁ ብለህ ነው?” ብዬ ደንግጨ መለስኩለት፡፡ እኔ እምለው ግን ቆይ መቼ ነው እኛ መኖርን የምንለማመደው? የጠገበና ያልጠገበ እኩል ይዘላል እንዴ? አዳሜ በኑክሌር ሒሳብ ትከሻ ለትከሻ ተገፋፋ ተብሎ ወሬው ሁሉ ጦርነት ሆነ እኮ፡፡ አላዩማ የእኛን ጦርነት፡፡ አሁን ማን ይሙት እኛ ዘንድሮ ከኑሮ ጋር የምናደርገው እልህ አስጨራሽ ግብግብ አንደኛውንም ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ጠቅሎ አይጎርሰውም? የምሬን እኮ ነው፡፡ እናላችሁ እኔ በኑሮ ግብግብ በሁለት ተፃራሪ ዕይታዎች እየተማታ ባሳደገኝ፣ አሁንም የገቢ ምንጭ ሆኖኝ እንድኖር በፈቀልኝ ወገኔ መሀል ግራና ቀኝ በትዝብት እየተላጋሁ ቢዝነሴን አጧጡፋለሁ፡፡ አንድ ከጀርመን የመጣ ወዳጄ ከሦስት ዓመት በፊት አከራይቶ ሊሸቅልበት አስቦ ያመጣውን ዶዘር ለመሸጥ ነግሮን ሳምንት ሳይፈጅ አሻሻጥኩለት፡፡ እና ኮሚሽኔን ሊሰጠኝ በዚያውም ለአንድ ጉዳይ ክፍለ ከተማ አብረን እንሄዳለን ብሎኝ ወደ እሱ እየሄድኩ ነው፡፡

እስካሁን ድረስ ታክሲ ተጠቃሚ መሆኔ የሚያንገበግባቸውን ዘልዛዮቼን እያሰብኩ ነበር በታክሲ የምጓዘው፡፡ አሁን እስኪ ቢኖረኝ እኔ ለምነዳው መኪና፣ ባይኖረኝ እኔ ለሚቀርብኝ የእኔ እንዲህ ቢያንስ ለአቅም ቪትዝ አለመድረስ ያንገበግባል? የሚያንገበግብ ነገር ጠፍቶ ማለት ነዋ፡፡ ሆሆ! ግርምት ፈገግ እያሰኘኝ እንደ እብድ ብቻዬን እየሳቅኩ በሐሳብ ጭልጥ ብያለሁ፡፡ የሌላው ተሳፋሪ ስሜት ከእኔ በተቃራኒ መሆኑን ልብ ስል ግን ቅፅበት አልፈጀብኝም፡፡ ብቻ ለብቻ መቆዘሙን ትቶ እርስ በእሱ ለከንፈር መጠጣ ይረዳዳል። ‹‹ምነው?›› አልኩት አጠገቤ የተቀመጠውን፡፡ ‹‹አትሰማም እንዴ ሬዲዮኑን?›› አቶ ትራምፕ እኮ ሊያጫርሱን ነው፡፡ ካልጠፋ ነገር እስኪ አሁን የእየሩሳሌምን እሳት ታራግባለህ? ነውር አይደለም? ስንት ሕፃናት ሊሞቱ ነው? ስንት ወጣቶች ሊቀጩ ነው? ስንት አዛውንቶች መቀበሪያ ሊያጡ ነው?›› ብሎ፣ ‹‹ማሰብ ማንን ገደለ? ግን ነውር አይደለም?›› እያለ ሲጨቀጭቀኝ ወራጅ ብዬ ወረድኩ፡፡ እኔን ማነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው ያለው?

ብቻ ከሚታየውና ከሚሰማው ሁሉ ውስጠ ሚስጥሩን መበለት እያቃተን የመጣነው በዝተናል፡፡ እንዲያው ከሁሉ ከሁሉ የገረመኝ ለሚታየውና ለማይታየው ነገር የሚሰጠው የነገር ክብደት፣ እያደር እንደ ኑሮ ክብደት ኪሎ እየጨመረ የመምጣቱ ነገር ነው፡፡ ማለት ስንቱ በሕይወት ጣና ውስጥ በሥውር የበደል ማዕበል ህልውናውን እየተነጠቀ እንዳለ እያወቅን፣ የምናወራውና የምናስወራው በዓይን የምናየውን ብቻ ነዋ፡፡ እውነቴን እኮ ነው፡፡ የህሊና ካሳና የሞራል ስብራትን እውነት በአሁን ዘመን ማን ነው አክብዶ የሚያያቸው፡፡ አሁን በቀደም ዕለት ምን ሆነ መሰላችሁ? አንድ ደንበኛዬ የቶርኖ ማሽን ገዝቶ አስመጥቶ ለመሸጥ ያስባል፡፡ ወንድሙ በደህና ጊዜ አንገቱን ያስገባ ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ሰው ስለሆነ የማስጫኑን ነገር በእሱ በኩል እጨርሳለሁ ብሎ ሙሉ እምነቱን ጥሎ፣ ከተማው ውስጥ አሉ የሚባሉትን ማሽኖች እየዞርን አብረን አየን፡፡ ማስመጣት ስላለበት ማሽን ዓይነትና ሞዴል በቂ መረጃ አሰባሰበን ስንጨርስ ገንዘቡን በወንድሙ የባንክ ሒሳብ አስገብቶ መጠባበቅ ያዘ፡፡

በጣም እኮ ነው የሚገርማችሁ ወንድምዬው አላየሁም አልሰማሁም ብሎ ክዶት አያርፍ መሰላችሁ? ቢባል ቢሠራ ‹ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ› አለ አሉ፡፡ ውል የለ ማስረጃ የለ ሕግስ ምን ብሎ መሀል ይግባ? ይኼው ከትናንት ወዲያ የተለመደችዋ መደገፊያዬ ላይ ተደግፌ አላፊ አግዳሚውን ሳስተውል መለመላውን አብዶ ሲሮጥ አየሁት፡፡ “የማይታይ የማይታየውንማ ለፈጣሪ መተው ነው አንበርብር፡፡ ወይ ጉድ አስኪ መጀመሪያ ማየት የቻልነውንም በደንብ እናፅዳው፤” ያሉኝ ባሻዬ ናቸው፡፡ ‹‹ከአቅም በላይ የሆነን ነገር ምን ማድረግ ይቻላል?›› ሲሉ፣ ሳስበው ባሻዬ የተናገሩት በጣም እውነት ነው፡፡ አጠገባችን ዓይን ያወጣ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕ መጓደል፣ ሕይወት እያስመረረን አራግፈን ሳንጨርስ ስለማይታዩት የህሊናና የሞራል ወንጀሎች ልናወራ እንደማንችል ገባኝ፡፡ አሁን ይኼን ሁሉ በጣና አይደል ማንሳታችን? ታዲያ አንድ ወዳጃችን ምን አለን መሰላችሁ?  “ይገርማል ለመጠጥ የሚሆን ውኃ በወጉ በቧንቧ ማግኘት የሚያቅተን ሰዎች በውኃ ስንሞት ምን ይባላል?” ሲለን ስለእኛ ‹አብስትራክት› የኑሮ ቋጠሮ ማንም ምንም ማለት እንደማይችል ገባኝ! ባለቀ ሰዓት እየገባን ተቸገርን እንጂ!

ደግሞ የቱንም ያህል ያሰብነው ቢሳካ የወጠንነው ቢሰምር ያለጤና ስታስቡት ነገር ዓለሙ ጭው አይልባችሁም? ስንቱ ነው ጤነኛ ብሎ መጠየቅም እኮ ለኢኮኖሚው ዕድገት የግል አስተዋጽኦን እንደ ማበርከት የሚቆጠር ነበር። የሚሰማ ቢኖር ማለቴ ነው። ጤነኛ ቢኖር ብትሉትም ያስኬዳል። ‘እያዩት ከማይበሉት ሰዎች ተርታ አያስቆጥራችሁ!’ ነው አሉ የሚባለው። አይ እኛ መቼም ‹አሉ› ስንወድ እኮ! ባሻዬ ባለፈው ሰሞን ከዕድር ስብሰባቸው ሲመለሱ ሳገኛቸው፣ “አቤት! እግዚኦ አንተ ፈጣሪ!” እያሉ ነበር፡፡ እጆቻቸውን ወደ ሰማይ አንስተው ረቂቅ ትዝብታቸውን ለአምላካቸው ይኸው ብለው እንደ ንድፍ የሚያሳዩት ይመስላሉ፡፡ “ምነው ባሻዬ?” ስል እንደ ልማዴ፣ “እንዲያው ማን ይሆን ጤነኛ ዘንድሮ አንበርብር? ሰው ሁሉ ጉዱን ከኋላው ቀብሮ ነው ለካ የሚኖር?!” ሲሉኝ ምን ሰምተው እንደሆነ አልጠየቅኳቸውም፡፡ ምድረ ሙሰኛ እንደ ቀበሮ ካለበት ጉድጓድ እየታደነ ለሕግ መቅረብ በሚገባው ጊዜ የምን ጥያቄ ማብዛት ነው እሱ? ይልቅ የገረመኝ የእኛ የሰው ልጆች ባህሪ ነው፡፡ በስርቆትና በሕገወጥ መንገድ ዘመናችንን በሙሉ ለምን የተደላደለ ነገር ይዘን ለመኖር እንደ ምንደክም ሳስበው ብቻዬን ገርሞኝ እስቅ ጀመር። ወደው አይስቁ እኮ ነው!

በሉ እንሰነባበት። ነገር ላሳጥርና ኮሚሽኔን ተቀባብዬ ከባሻዬ ልጅ ጋር አንድ አንድ ልንል ወደ ግሮሰሪያችን አዘገምን፡፡ የሰሞኑ ንፋስ ደግሞ ንፋስ አይደለም፡፡ እና ውስጡ ሞልቶ ደጅ ተቀምጠን ስንቀጠቀጥ ሴትና ወንድ አዝማሪዎች መጡና ‘እንደ የሩሳሌም እንደ አክሱም ጽዮን’ ማለት ጀመሩ፡፡ ሰው ወዲያ ጭቅጭቅ ጀመረ፡፡ አንዱ “እስኪ አረጋጉት፡፡ እየሩሳሌም የትራምፕ ትሁን፣ የአይሁድ ትሁን፣ ወይም እንደ ቀድሞው የሁለቱ ታላቅ እምነቶች ቅዱስ ሥፍራ. . . ምንም የምናውቀው ነገር ስለሌለ እንደ እየሩሳሌም የሚለው ትታችሁ ሌላ ተጫወቱ፤” ብሎ ሲቀመጥ ሌላው ተነስቶ፣ “ማን ባቀናው ማን ሊያዝበት? ማን ባፀናው ማን ሊመሰገን? ትራምፕ ብሎ ስም ያወቅነው ትናንት፣ እየሩሳሌም የሚባለው ስም የጥንት የጠዋት፤” ሲለው ግሮሰሪዋ በጭብጨባ ተናጋች፡፡ ወደ ባሻዬ ልጅ ዞሬ፣ “ምንድነው ጉዱ?” ስለው፣ “ገና ምኑን ዓይተህ? ሰውዬው እኮ የሚሠራውን የሚያውቅም አይመስለኝም፡፡ ክርስቲያኑ፣ ሙስሊሙ፣ ይሁዳው፣ ሁሉም የእኔ ናት የሚላትን ከተማ እንዲህ በአቦ ሰጡኝ መናገርስ ምን ያስፈልጋል? የደም ጥማት ካልሆነ በስተቀር?” ሲለኝ ብርክ ያዘኝ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ እኛ ውኃ ጥማችንን ሳንቆርጥ ዓለም እንዲህ ደም ደም ያላት ግን? ትንፋሽ አጠረን እኮ? መልካም ሰንበት!