Skip to main content
x
አዲሱ የኢዴፓ አመራር በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር አቋሙን አለመቀየሩን አስታወቀ
ከግራ ወደ ቀኝ የኢዴፓ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ጽጌ ጥበቡ፣ ፕሬዚዳንቱ አቶ አዳነ ታደሰና የማኅበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ጋሹ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ

አዲሱ የኢዴፓ አመራር በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር አቋሙን አለመቀየሩን አስታወቀ

አዲሱ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አመራር በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ላይ ያለው አቋም አለመቀየሩን፣ በውስጡ መከፋፈል ተፈጥሯል የሚባለው ደግሞ ከእውነት የራቀ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ከሥልጣናቸው ዝቅ መደረጋቸውን፣ ፓርቲው በአሁኑ ጊዜ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ ድርድር በአዲስ ተወካዮች መወከሉን በገለጸ በሳምንቱ በሰጠው ይፋ መግለጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር መድረክ አዲሱን ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰንና እንደ አዲስ የተመረጡ ሌሎች አመራሮችን ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡

በበቅሎ ቤት በሚገኘው የኢዴፓ ዋና ጽሕፈት ቤት ሐሙስ ኅዳር 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ከምክትላቸው ወ/ሮ ጽጌ ጥበቡና ከፓርቲው የማኅበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ጋሹ ጋር በመሆን በሰጡት መግለጫ፣ የድርድር መድረኩ አዲሱን ተወካዮች ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆነ ፓርቲው በድርድሩ አሁንም የመቀጠል ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም በአሁኑ ወቅት የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ጨምሮ የፓርቲውን የቀድሞ የጥናትና ኅትመት ኃላፊ የነበሩትን አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ውክልናቸው ቢነሳም፣ አሁንም በድርድሩ ላይ በኢዴፓ ስም እየወሰኑ ነው ብለዋል፡፡

በተለይ አቶ ዋሲሁን በኢዴፓ ስም በድርድር መድረኩ ከመገኘታቸው በተጨማሪ፣ የድርድር መድረኩ ምክትል ኃላፊ ሆነው ቢሮ ተሰጥቷቸው እየሠሩ እንደሆነ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ከሥልጣናቸው ዝቅ እንዲሉ የተደረጉት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)  የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው የጥናትና ኅትመት ኃላፊ ሆነው እንዲሠሩ፣ እንዲሁም ምክትል ፕሬዚዳንቱና የቀድሞው የጥናትና ኅትመት ኃላፊ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል ሆነው እንዲቀጥሉ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በተጠራው የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ መወሰኑ በመግለጫው ወቅት ተገልጿል፡፡

በኢዴፓ ሕገ ደንብ መሠረት 25 አባላት እንዲኖሩት የሚጠበቀው ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ይመርጣል፡፡

ብሔራዊ ምክር ቤቱ የፓርቲው መሥራች አቶ ልደቱ አያሌው ጭምር የተካተቱበት ሲሆን፣ ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረገው ምርጫም 18 አባላት ተገኝተው 15 የቀድሞ አመራሮች እንዲወርዱ መወሰናቸውን አቶ አዳነ አስታውሰዋል፡፡

ለአመራሮቹ መውረድ ምክንያቱ በድርድር መድረኩ ኢዴፓን ወክለው እንዲደራደሩ ቢላኩም፣ የኢዴፓን ጥቅም የሚፃረሩ ውሳኔዎችን ስለሚያስተላልፉ እንዲሁም እንዲያማክራቸው ከተሰየመው አምስት አባላት ካሉት ኮሚቴ ውጪ በመንቀሳቀሳቸው እንደሆነ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንትም ሆኑ አቶ ዋሲሁን ከሳምንት በፊት ለሪፖርተር አዲሱ አመራር ሕገወጥ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ሁለቱን ግለሰቦች በመግለጫው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም፣ አቶ ዋሲሁን ለተደረገላቸው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ መልስ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ በተጨማሪ ጫኔ (ዶ/ር) ከስልክ ጥሪ በተጨማሪ ለተላከላቸው አጭር የስልክ መልዕክት ምላሽ አልሰጡም፡፡

ከአዲሱ አመራር ምርጫ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከብዙ ሙከራ በኋላ ደብዳቤያቸውን እንደተቀበለ አቶ አዳነ ተናግረዋል፡፡

‹‹አዎ ደብዳቤያቸውን ተቀብለናል፤›› ሲሉ የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተስፋለም ዓባይ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ በቀጣይ ምርጫ ቦርድ የአዲሱ አመራር ምርጫ በኢዴፓ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የተከናወነ መሆኑን አረጋግጦ ውሳኔ ይሰጣል ብለዋል፡፡