Skip to main content
x
የኢትዮጵያና የኬንያ ንግድ ምክር ቤቶች የዓለም ንግድ ምክር ቤቶችን ጉባዔ ለማስተናገድ ተፋጠዋል
ከቀኝ ወደ ግራ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) እና የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ ከኬንያ ንግድ ምክር ቤት ኃላፊዎች ጋር በተነጋገሩበት ወቅት

የኢትዮጵያና የኬንያ ንግድ ምክር ቤቶች የዓለም ንግድ ምክር ቤቶችን ጉባዔ ለማስተናገድ ተፋጠዋል

የዓለም ንግድ ምክር ቤቶች አባል የሆኑበትና በየሁለት ዓመቱ በተለያዩ አባል አገሮች እየተዘዋወረ የሚካሔደውን የዓለም የንግድ ምክር ቤቶች ኮንግረስ በአፍሪካ ደረጃ ለማዘጋጀት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ከኬንያ አቻው ጋር ተፋጧል፡፡

በመስረከም ወር ገደማ በጥንታዊው የአውስትራሊያ ንግድ ምክር ቤት አስተናጋጅነት በሲድኒ በተካሄደው ኮንግረስ ወቅት የተሳተፉት ንግድ ምክር ቤቶች፣ ወደፊት የሚካሔዱትን ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ለማዘጋጀት ጥያቄያቸውን አቅርበው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2019 የሚካሄደውን ጉባዔ እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ብራዚል ነች፡፡

ይሁንና ከብራዚል የሚረከበው አገር የቱ እንደሚሆን ለመወሰን በቀረበቀው ጥሪ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትን ጨምሮ ከ20 በላይ አገሮች ጥያቄ ማቅረባቸውን ለሪፖርተር የገለጹት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ ናቸው፡፡

አቶ እንዳልካቸው ከአዲሱ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) ጋር በመሆን በጂቡቲው ዓለም አቀፍ ንግድ ትርዒትና የቀጣናው የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር ላይ ባተኮረው መድረክ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ከዚህ ዝግጅት ጎን ለጎን ግን በመጪው የዓለም ንግድ ምክር ቤቶች ጉባዔን አፍሪካ የማዘጋጀት ዕድል እንድታገኝ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ማድረጓን የገለጹት አቶ እንዳልካቸው፣ በሲዲኒው ጉባዔ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት የአፍሪካና የእስያ አገሮች ከሦስት ዓመት በኋላ እንደሚካሄድ ለሚጠበቀው ዓለም አቀፍ ጉባዔ በዕጩነት ቀርበዋል፡፡

አፍሪካን ከሚያሠጉ ተወዳዳሪዎች መካከል ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ ትገኛለች፡፡ ዱባይ ለዚህ ውድድር ከብቁ በላይ መሆኗ ቢታመንም፣ የማዘጋጀት ዕድሉን ላታገኝ የምትችልባቸው ዕድሎች እንዳሉ አቶ እንዳልካቸው ያስረዳሉ፡፡ ይኸውም ዱባይ ከዚህ ቀደም ጉባዔውን ማስተናገዷ አንደኛው ምክንያት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በዱባይ የሚካሄደው ግዙፉ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ሲሆን፣ ይህም ጉባዔውን እንዳይሸፍነው ስለሚገመት ነው፡፡ በዚህ ወቅት የዓለም ንግድ ምክር ቤቶችን ጉባዔ አብሮ የማስኬድ ውጥን ያላት ዱባይ፣ ከቀረቡት ምክንያቶች ባሻገር ግን ለአፍሪካ ንግድ ምክር ቤቶች ትልቅ ሥጋት መሆኗ አልቀረም፡፡

 ከዚህ በተጨማሪ በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለው የእርስ በርስ ፉክክርም ኢትዮጵያ የማዘጋጀት ዕድሉን ለማግኘት ደንቃራ የሆኑባት ይመስላል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ለሌሎች አገሮች ባቀረባቸው ሐሳቦች አማካይነት፣ በአፍሪካ አገሮች መካከል የእርስ በርስ ውድድር ከሚደረግ ይልቅ በጋራ አሊያም በአንድ ተወካይ አገር አማካይነት ጉባዔው በአፍሪካ እንዲካሔድ ለማድረግ ምክር ቤቱ እንቅስቃሴ ማድረጉን አቶ እንዳልካቸው አብራርተዋል፡፡

ከሦስት ዓመታት በኋላ የሚካሔደውን ዓለም አቀፍ የንግድ ምክር ቤቶች ጉባዔ በተመለከተ፣ የኢትዮጵያና የኬንያ ንግድ ምክር ቤቶች ኃላፊዎች በጂቡቲ ተነጋግረዋል፡፡ ሁለቱም አገሮች በየራሳቸው ጉባዔውን የማዘጋጀት ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ኅብረት መገኛነቷ ብቻም ሳይሆን ካላት ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማኅብሰረብ ውክልና እንዲሁም ከሌሎች መከራከሪያዎች አኳያ ለጉባዔው እኔ እሻላለሁ እያለች ትገኛለች፡፡

ሆኖም አንድ ቀን ሙሉ በፈጀው የኢትዮጵያና የኬንያ ንግድ ምክር ቤቶች አመራሮች ድርድር ሒደት ሁለቱ ወገን ያለ ስምምነት በቀጠሮ ተለያይተዋል፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከሁለቱ አገሮች አንደኛው ለአዘጋጅነት ዕጩ ሆኖ የመቅረብ ግዴታ እንጂ አንዱ የሌላኛው ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረብ እንደማይገባው የኢትዮጵያ አቋም በመሆኑ ላይ ኬንያን እየተጫነች የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ጉዳዩን በ30 ቀናት ውስጥ እልባት ለመስጠት ከኬንያ ንግድ ምክር ቤት ጋር ቀጠሮ ብትይዝም፣ እስከዚያው ግን በየጊዜው በስልክ እየተነጋገሩ መረጃና ሐሳብ ለመለዋወጥ ወስነው መሰነባበታቸውን አቶ እንዳልካቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

100 በላይ አገሮችን በአባልነት ያቀፈው ዓለም አቀፉ ንግድ ምክር ቤት፣ የዓለም ንግድ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን በመሆን ይንቀሳቀሳል፡፡