Skip to main content
x
ባቲና ሰንበቴ …
የባቲና የሰንበቴ ገበያ አገሬውን ብቻ ሳይሆን ባሕር አቋርጠው የሚመጡ ቱሪስቶችን ቀልብ ይገዛሉ፤ ቱሪስቶች በሰንበቴ ከግመል ነጋዴዎች ጋር

ባቲና ሰንበቴ …

ባቲ የሚለው ቃል ብዙኃኑን የሚያስተሳስር፣ በተለይ ከሙዚቃ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ከቅኝቶች አንዱ መሆኑ ነው፡፡ ከወሎ የመነጨ፣ የባህላዊ ሙዚቃ ድርሳኖች እንደሚያመለክቱት ከትዝታ፣ አምባሰልና አንቺ ሆዬ ጋር የሚሰለፈው ባቲ ቅኝት ‹‹በዘፈን ጨዋታ በቀረርቶና በሽለላ ጦርነትን በድል የመወጣ መንፈስና መንገድ ያለው ዜማ ነው›› ይሉታል፡፡፡ ኀዘንና ደስታ ሲፈራረቅ በየመልኩ የባቲው ቅኝት እንደሚስማማው አድርጎ ይቀምረዋል፡፡

‹‹ባቲ›› የሚለው መጠሪያ በሙዚቃ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ሌላውም ሙያ አለው፡፡ አገሬውን ብቻ ሳይሆን ባሕር አቋርጠው፣ ድንበር ተሻግረው የሚመጡ ቱሪስቶችን ቀልብ የሚገዛው የባቲ ገበያ ተጠቃሽ ነው፡፡ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና ከተማ ከሚሴ 92 ኪሎ ሜትር ላይ በሚገኘው የባቲ ገበያ የሚገበያዩት በዋናነት በከተማው ውስጥ በጋራ የሚኖሩት አምስት ብሔረሰቦች ኦሮሞ፣ አማራ፣ አፋር፣ አርጎባና ትግራይ ናቸው፡፡ ገበያውን ከእነዚህ ብሔረሰቦች ባለፈ በዙሪያው ያሉ አጎራባች ከተሞችና አካባቢዎች እንደ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ወልዲያ የመሳሰሉት በመምጣት ይገበያዩበታል፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በክልሉ ባካሄደው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ምዝገባ ኅትመት ላይ እንደተመለከተው፣ የባቲ ገበያ ኅብረተሰቡ በሰላምና በፍቅር የሚገበያይበት ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉም የየአካባቢውን ምርቶችና ሀብቶች ለገበያው በማዋል እርስ በርስ የባህል ልውውጥ የሚያደርግበትም ጭምር ነው፡፡

በባቲ ገበያ ከአፋር የቀንድ ከብቶች እንደ ፍየል፣ በጎችና ግመሎች፣ ከጋማ ከብቶች አህያ ይመጣሉ፡፡ ከምግብ ዘሮች የወተት ተዋጽኦ የሆነው ቅቤ ይመጣል፡፡ ከአርጎባ አካባቢ የባህል ዕቃዎች፣ ጌጣጌጦች፣ አልባሳት በተለይ የሽመና ውጤቶች ይመጣሉ፡፡

ባቲና ሰንበቴ …
አብሮነት በባቲ ገበያ

 

ከአማራ አካባቢ የተለያዩ ዘመናዊና ባህላዊ የልብስ ዓይነቶች፣ ጥራጥሬና ሸንኮራ አገዳ የመሳሰሉት ይመጣሉ፡፡ የባቲ ገበያ ከምትታወቅበት የውቦች አካባቢና ትልቁ ገበያነቷ ባሻገር በገበያዋ መሀል በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት (1923-1967) የተሠራውና ቀደም ሲል ጨለማን ተገን በማድረግ የሰው ሕይወት ያጠፉና ንብረት የዘረፉ የነበሩ ሽፍቶች ለፈጸሙት ወንጀል በስቅላት ይቀጡበት የነበረው የሰው መስቀያ ብረት በገበያው መሀል ቆሞ ይታያል፡፡

ከኦሮሞ አካባቢ ለገበያ የሚቀርቡት በአብዛኛው የአገዳ እህሎች በዋናነት ማሽላና በቆሎ ሲሆኑ፣ ማሽላ በባቲ የተለያዩ ስሞች አሉ፡፡ እነዚህም አባኢሬ/ሙካኬ፣ ደንገለኢ፣ ጅራጊቴ/ነጭ ማሽላ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ከቅባት እህሎች ሙሾ፣ ሰሊጥ፣ ለውዝ የመሳሰሉት ይመጣሉ፡፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ባቲ ተለይታ የምትታወቅበት በፍራፍሬ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ብርቱካን፣ መንደሪን፣ ሎሚ፣ ትርንጎ፣ ሙዝ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ከትግራይ አካባቢ ነዋሪዎችም ወርቅ፣ ብርና ነሐስ ለገበያ ይቀርባሉ፡፡፡ እንደ ቅርሱ ድርሳን አገላለጽ፣ የጋራ መገበያያ የሆነው የባቲ ገበያ ከትንሽ እስከ ትልቅ በህብረ ቀለማት አሸብርቀው በተለያየ አለባበስና አጊያጌጥ የሚመጡበት፣ ጎረምሳዎችና ሳዱላዎች የሚተጫጩበት/የሚመራረጡበት ትልቅ የመገናኛ መድረክ ሲሆን፣ በአለባበስና በአጊያጌጥ ረገድ የታጨች/ያልታጨች ሳዱላ/ልጃገረድ፣ ጎረምሳዎችና አዋቂዎች በየደረጃው በተለያየ አለባበስና ጌጣጌጥ ተውበው ወደ ገበያ የሚመጡ ናቸው፡፡

የታጨች ሳዱላ/ልጃገረድ በአለባበስ ረገድ በህብረ ቀለማት ያሸበረቀ ወጥ ቀሚስ የምትለብስ ሲሆን፣ ይህ ልብስ በአካባቢው አጠራር ‹‹ገመሌ›› ይባላል፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ሶርዲያና ጎንቢሶ (በጥጥ የሚሠራ ባህላዊ ልብስ) በወገቧ ላይ መቀነት ታጥቃበት ትለብሳለች፡፡ በጫማ ረገድ ከከብት ቆዳ የተሠራ ጫማ አልፎ አልፎ የላስቲክ ጫማ (ኮንጎ) ትጫማለች፡፡

ከጌጣጌጥ አኳያ በአካባቢው አጠራር ሲቃብር/ብርና የብር ወለባ ፀጉሯ ላይ ትሰካለች፡፡ ከብር የተሠሩ አምባሮች እጇ ላይ፣ አምስት ቀለበቶችን አንገቷ ላይ ታስራለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከብር የተሠራ እንጥልጥል አንገቷ ላይ ታደርጋለች፡፡ ጆሮዋ ላይ ‹‹ጃሂ›› የተባለ ስድስት ፍሬ ያለው የጆሮ ጌጥ ታደርጋለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለይ በባቲ ውስጥ ገርፋ ቀበሌ ብርብስ የተባለ ጌጥ አንገቷ ላይ ታደርጋለች፡፡

ሰንበቴ ሌላው የገበያ ማዕከል ነው፡፡ በዞኑ በጅሌ ጡሙጋ ወረዳ ከከሚሴ ከተማ 63 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የገበያው መጠሪያ የሆነው ሰንበቴ የሚለው ቃል ስያሜውን ያገኘው ከዕለተ ሰንበት/ከእሑድ በኦሮሚኛው ‹‹ሰንበተ ጉዳ›› ከተባለው መሆኑን የቅርሱ ድርሳን ያወሳል፡፡ የሰንበቴ ገበያ ይህንን ስያሜ ከማግኘቱ በፊት ገበያው ሰኞ ዕለት ይውል እንደነበርና ቀቢ/ያዝ የሚል ስያሜ እንደነበረው ሲናገሩ፣ ቦታው ሲቀየር ስያሜውም አብሮ ተቀይሮ ሰንበቴ እንደተባለ አያይዘው ይናገራሉ፡፡ የሰንበቴ ገበያ የተመሠረተው በልጅ ኢያሱ ዘመን (1906-1909) እንደሆነና ለዚህም እንደማስረጃ በሰንበቴ ገበያ በስማቸው የተሰየመ ኢያሱ ባህር ዛፍ (ጤና ኢያሱ ዛፍ) መኖሩን ይናገራሉ፡፡

የሰንበቴ ገበያ እንደ ባቲ የተለያዩ የኦሮሞ፣ አማራ፣ አፋርና አርጎባ ብሔረሰቦች ከትልቅነቱ ይገበያዩበታል፡፡ ከትልቅነቱ አኳያ ‹‹ትንሿ መርካቶ›› የሚል ስያሜን አግኝቷል፡፡ ገበያው በዋናነት በአካባቢው የሚገኙ በገበያው የሚፈለጉት ምርቶች ከእህልም፣ ከእንሰሳትም አይታጣበትም፡፡

ለምሳሌ ከኦሮሞ አካባቢ ግመል፣ የቀንድ ከብቶች ፍየል፣ በግ፣ በሬ፣ ላም፣ ጥጃ ወዘተ ከጋማ ከብቶች አህያ፣ ፈረስ፣ አልፎ አልፎ በቅሎ ይዘው ከመምጣታቸው በተጨማሪ ከጨፋ ሮቢት/አርጡማ ፉርሲ  ወረዳ ጎጀባ/ወገብ ላይ የሚደረግ እንደጌጥም እንደ መሣሪያም የሚያገለግል ቁሳቁስም እንደዚሁም ማርና ቅቤም ያመጣሉ፡፡ ከአማራ አካባቢ ደግሞ ቦታው ደጋማ በመሆኑ የጥራጥሬ እህሎች እንደ ምስር፣ አተር፣ ባቄላ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ጤፍ እንደዚሁም ከአገዳ እህሎች እንደ በቆሎ፣ ማሽላ የመሳሰሉት ይመጣሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማርም ለገበያ ያቀርባሉ፡፡

ከአርጎባ አካባቢ የተለያዩ የሽመና ውጤቶች የሆኑ ልዩ ልዩ አልባሳት፣ እንዲሁም ጌጣጌጦች ለምሳሌ የጆሮ ጌጥ፣ የእጅ አምባር፣ እግር አልቦ፣ ወዘተ ይመጣል፡፡ በአጠቃላይ ከሁሉም አካባቢዎች የተለያዩ አካባቢያዊ አልባሳት፣ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ የእርሻ መሣሪያዎች እንደ ወገል፣ ማረሻ… የመሳሰሉት ገበያ ላይ ይመጣሉ፡፡፡ ሰንበቴ ገበያ መጥቶ የሚፈልገውን አጥቶ የሚመለስ የለምም ይባላል፡፡

በሰንበቴ ገበያ ሁሉም ወገን የሚገበያይበት በመሆኑ የፍቅር ተምሳሌት ገበያ እንደሆነ መረጃ ሰጪዎች ጠቅሶ የቅርሱ ድርሳን ይገልጻል፡፡ ሰንበቴ ገበያ ከገበያነቷ ባሻገር ወንዶች የወደዷትን ሳዱላ/ልጃገረድ የሚመርጡበትና ለማግባት ቀን የተቆረጠላቸው ልጃገረዶችም በዚህ የገበያ ቀን ጓደኞቻቸውን በመሰብሰብና በማምጣት ከዘመድ አዝማድ፣ ከጓደኛ እንደዚሁም ከሚተዋወቁት ሰዎች በሙሉ ሲያገቡ የሚደራጁበትን ገንዘብ እንደየአቅም ሁኔታ የሚሰበሰቡበትም ትልቅ የመገናኛ ቀን በኦሮምኛ ‹‹ደኺ›› ይባላል፡፡

የሰንበቴ ገበያ በዳስ የተሸፈነ በመሆኑ በአንድ በኩል ገብተው ገበያተኛው ብዙም ፀሐይ ሳያገኘው በጥላ የሚገበያይበትና ምቹ መሆኑን የሚያሳይ ብሂልም ተጠቃሽ ነው፡፡

በኦሮምኛ፡- ‹‹ሰንበቴን ጋዲዱ ከሚስ አዱኬሳ›› (ሰንበቴ ጥላ ነው፣ የሐሙሱ ገበያ ግን ፀሐይ ነው) ማለቱ የሰንበቴ ገበያ ለግብይት ምቹና ፀሐይ የማያስነካ መሆኑን ለመግለጽ የተገለገሉበት መሆኑን ለማሳየት የቀረበ ነው፡፡

በሰንበቴ ገበያ ለግብይት የሚመጡት በተለያዩ ሕብረ ቀለማት ባሸበረቁ አልባሳትና ጌጣጌጦች ተውበው ነው፡፡ በአለባበስ ረገድ የታጨች ያልታጨች ልጃገረድ የምትለይበት፣ እንዲሁም ወንዶች የየራሳቸው የአለባበስ ሥርዓት አላቸው፡፡

ያልታጨች ልጃገረድ በአለባበስ ረገድ በአካባቢው ባህል መሠረት ወደ ገበያ ስትሄድ ለትዳር የምትመረጥበት በመሆኑ ጉፍታ/ጥቁር ሻሽ/ሻርፕ አትለብስም፡፡ እንድትታይና እንድትመረጥ በሹሩባ ተውባ ትሄዳለች፡፡ በወገቧ ላይ ደግሞ አለማግባቷን ለማሳየት ቶርቢ/ነጭ ብስ ያለው ቀበቶ ታደርጋለች፡፡ ይህን ማድረጓ ሁለት ጠቀሜታ አለው፡፡ ይኸውም አንዱ ያለማግባቷን የምትገልጽበት ምልክት ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የወገቧን ቅርጽ ለመጠበቅ የሚያገለግላት ነው፡፡ ከጌጣጌጥ አኳያ ጆሮዋ ላይ ጭልጭሌ፣ አንገቷ ላይ ደግሞ ሂጢንጢላ ታደርጋለች፡፡ የታጨች ከሆነች ደግሞ በአለባበስ ረገድ ካልታጨችው ተመሳሳይ ሆኖ፣ በጤጣጌጥ ረገድ ሀመርቲና ብርብስ የተባሉ ጌጣጌጦችን ታደርጋለች፡፡ እጇ ላይ ዳቢ ጉሜ አምባር ታደርጋለች፡፡ ወንዶቹን በተመለከተ ወጣቶቹም ሆኑ አዋቂዎቹ እንደየመጠናቸው ከታች ሸርጥ ከላይ ደግሞ ከጥጥ የተሠራ ሸሚዝ ይለብሳሉ፡፡ ጫማቸውን በተመለከተ ሴቶቹም ሆኑ ወንዶቹ የላስቲክ ጫማ (ኮንጎ) ይጫማሉ፡፡ አልፎ አልፎ ከግመል ቆዳ የሚሠራ ‹‹ጡመሮ›› የተባለ ጫማን ተጫምተው ወደ ገበያ እንደሚሄዱ ይገለጻል፡፡