Skip to main content
x
ሕፃናት የተሻለ እንዲኖሩ የማድረግ ስንቅ
ከግራ ዴቪድ ራይት፣ ሳም ውድ፣ ሕይወት እምሻው፣ ኤኪን ኦጉቶጉላሪና ሮባ ሃላኬ

ሕፃናት የተሻለ እንዲኖሩ የማድረግ ስንቅ

የሕፃናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ችልድረን) በዓለም ላይ ያሉ ሕፃናት የተሻለ የመኖር ዕድል እንዲያገኙ መሥራት ከጀመረ ከ60 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ በየአገሮቹ በተቋቋሙ የሕፃናት አድን ድርጅቶች ሥራዎች ሲከናወኑ  ቢቆዩም፣ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰባቱ ድርጅቶች ተዋህደው በአንድ ጥላ ሥር ሆነዋል፡፡ ድርጅቱ ሕፃናት በተለይም ለችግር የተጋለጡ ከችግራቸው እንዲወጡና የተሻለ ሕይወትን እንዲኖሩ ይሠራል፡፡ ከድርጅቶቹ ውህደት በኋላም የተሻለ ውጤት እንደተመዘገበ የድርጅቱ ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡ ድርጅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች የሚገኙና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሕፃናት በጤንነት እንዲያድጉ፣ ትምህርት እንዲያገኙና ከጥቃት እንዲጠበቁ እየሠራም ይገኛል፡፡ ድርጅቶቹ ከተዋሃዱ በኋላ በተለይም እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2017 ድረስ በኢትዮጵያ ያከናወናቸውን በተመለከተ ታኅሣሥ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ መግለጫውን የሰጡት የሕፃናት አድን ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር ሚስተር ኤኪን ኦጉቶጉላሪ፣ ሒዩማኒቴሪያን ዳይሬክተሩ ሳም ውድ፣ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ዴቪድ ራይት፣ በኢትዮጵያ የድርጅቱ የኮሙዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ኃላፊ ወ/ሮ ሕይወት እምሻውና ከፍተኛ የሒውማኒቴሪያን ማናጀሩ አቶ ሮባ ሃላኬ ናቸው፡፡ መግለጫውን የተከታተለችው ምሕረት ሞገስ ድርጅቱ እያደረገ ያለውን ሥራና ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጠውን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርባዋለች፡፡

በዚህ ጉዳይ፡- በኢትዮጵያ ካለፉት ሦስት ዓመታት በፊት የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ የድርጅቱ ምላሽ ምን ነበር?

የሕፃናት አድን ድርጅት፡- ኢትዮጵያ ባለፉት 50 ዓመታት ገጥሟት የሚያውቅ ዓይነት ድርቅ ከሦስት ዓመታት በፊት ገጥሟታል፡፡ በ2015 ከ1960ዎቹ ወዲህ ያልተመዘገበን ዝቅተኛ የዝናብ መጠን አስመዝግባለች፡፡ የዝናብ መጠን መቀነስ ያስከተለውን ድርቅ ለመታደግ መንግሥታትና አጋሮች ተባብረው ሰብዓዊ ዕርዳታ አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለድርቁ ምላሽ ለመስጠት የነበሩ ዕድሎችን በማጣመር በ2015/16 በነበረው ድርቅ የተጎዱና ወሳኝ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን 10.2 ሚሊዮን ሰዎች ለመርዳት 700 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል፡፡ የሕፃናት አድን ድርጅት ደግሞ 6.5 ሚሊዮን ዶላር ከራሱ በማውጣት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የ100 ሚሊዮን ዶላር የዕርዳታ ፕሮግራሞችን በማከናወንም ሁለት ሚሊዮን ሕፃናትን ደርሷል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ዕርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር 12.6 ሚሊዮን ሲደርስም፣ ድርጅቱ በተለይ ድርቅ ክፉኛ ባጠቃቸው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እንዲሁም በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች አንዳንድ ሥፍራዎች ዕርዳታውን ለግሷል፡፡ ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ከሌሎች አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞችን የጤና፣ የተመጣጠነ ምግብና የትምህርት ፍላጎታቸውን ለመሙላት እየሠራም ነው፡፡ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ድርቅ በጣም በጎዳቸው አካባቢዎች ምላሽ ለመስጠት ከመንግሥት ጎን ለጎን የጀመረውን ሥራ ለማጠናከርም በጥር 2017 ላይ የሒዩማኒቴሪያን ሪስፖንስ ስትራቴጂ ነድፏል፡፡ በስትራቴጂው 500 ሺሕ ተረጂዎችን ለመድረስ 50 ሚሊዮን ዶላር ያስፈለገ ሲሆን፣ በቅርቡ ስትራቴጂውን በመከለስም 1.5 ሚሊዮን ተረጂዎችን ለመድረስ 101 ሚሊዮን ዶላር በጀት ይዟል፡፡

በዚህ ጉዳይ፡- ድርጅቱ የድርቅ ተጎጂዎችን በሚረዳበት ፕሮግራሙ የትኞቹን አካባቢዎችና ምን ያህል ሰዎችን ደርሷል? 

የሕፃናት አድን ድርጅት፡- የሕፃናት አድን ድርጅት 53 ወረዳዎችን የደረሰ ሲሆን፣ ከነዚህም 39ኙ በሶማሌ፣ ዘጠኝ በደቡብና አምስት በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ ናቸው፡፡ የድርቅ ተጎጂዎችን ለመድረስ በስትራቴጂው ተሻሽሎ የቀረበው 900 ሺሕ ሕፃናትን ጨምሮ 1.5 ሚሊዮን ሰዎችን ለመድረስ ሲሆን፣ እስካሁንም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን ጨምሮ 998 ሺሕ የድርቅ ተጎጂዎችን መድረስ ተችሏል፡፡ የተሰጠው አገልግሎትም በጤናና በተመጣጠነ ምግብ፣ በሕፃናት ጥበቃ፣ በትምህርት፣ በአካባቢና በግል ንፅህና ሲሆን፣ በገንዘብ ለሥራ ፕሮግራሙ የተጠቀሙም አሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ፡- ድርጅቱ በትምህርት ዘርፍ ምን አስተዋጽኦ አድርጓል?

የሕፃናት አድን ድርጅት፡- ድርቁ ባየለባቸው አካባቢዎች ሕፃናት ከትምህርት እንዳይስተጓጎሉ ለ7,115 ተማሪዎች የትምህርት መርጃ ተከፋፍሏል፡፡ በሶማሌ ክልል እዚያው ለተፈናቀሉ ልጆች ሁለት የመማሪያ ሥፍራዎች ተቋቁመዋል፡፡ ድርጅቱ በሚሠራባቸው አካባቢዎች 114 የውኃ ማጠራቀሚያ ጋኖች የተተከሉ ሲሆን፣ በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሙም በጊዜያዊነት በተሠሩ የመማሪያ ሥፍራዎች የሚማሩ 2,309 ልጆች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በየትምህርት ቤቶች ንፁህ የመጠጥ ውኃ በቦቴ በማድረስም ወደ 7,470 ተማሪዎችና 96 መምህራንን መድረስ ተችሏል፡፡

በዚህ ጉዳይ፡- የአካባቢና ግል ንፅህና መስተጓጎል እንዲሁም የንፁህ ውኃ አቅርቦት እጥረት በተለይ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የሚታይና የበሽታም መንስዔ ነው፡፡ እዚህ ላይ ድርጅቱ ምን አበርክቷል?

የሕፃናት አድን ድርጅት፡- ድርጅቱ በውኃ አቅርቦት ፕሮግራሙ 118,515 አዋቂዎችና 126,571 ሕፃናትን ደርሷል፡፡ የውኃ ማከሚያ ኬሚካሎች የተሠራጩ ሲሆን፣ የውኃ አስተዳደሩን ለማጠናከርም ለማኅበረሰቡ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ከ200 በላይ በጎ ፈቃደኞች በአካባቢና ግል ንፅህና አጠባበቅ ዙሪያ ሥልጠና የወሰዱ ሲሆን፣ ለግል ንፅህና የሚውሉ ቁሳቁሶችም ተሰጥቷል፡፡

በዚህ ጉዳይ፡-  በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ ሕፃናት ጥበቃ ላይ ድርጅቱ ምን ሠርቷል?

የሕፃናት አድን ድርጅት፡- ድርጅቱ በሚሠራባቸው በጤና፣ በተመጣጠነ ምግብ፣ በትምህርትና በሌሎችም ዘርፎች ውስጥ የሕፃናት ጥበቃ ሥራን አጣምሮታል፡፡ ለሕፃናትም አካባቢያቸውንና ያሉበትን ሁኔታ እንዲለማመዱትና እንዲረዱት የሥነ ልቦና ድጋፍ ተደርጓል፡፡

በዚህ ጉዳይ፡-  ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስደተኞችን ከሚያስተናግዱ አገሮች አንዷ ናት፡፡ ከስደተኞቹ መካከልም ግማሽ ያህሉ ሕፃናት ናቸው፡፡ ስደተኛ ሕፃናትን አስመልክቶ የድርጅቱ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

የሕፃናት አድን ድርጅት፡- ኢትዮጵያ ከ20 አገሮች የተሰደዱና የፖለቲካ ጥገኝነት የሚሹ 494,578 ሕፃናትን ጨምሮ 852,721 ስደተኞችን በ27 ካምፖች አስጠልላለች፡፡ ይህም አገሪቷ ስደተኞችን በማስተናገድ በአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ እንድትሰፍር አድርጓታል፡፡ ከጥር 2017 በኋላ ብቻ 100,034 ስደተኞች ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡

47 በመቶ ስደተኛ ሕፃናት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት የሚያገኙ ቢሆንም ይህ አገሪቱ በብሔራዊ ደረጃ ከደረሰችበት የ90 በመቶ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የስደተኛ ካምፖች የሥነ አዕምሮ ድጋፍ የላቸውም፡፡

ኢትዮጵያ ከአጋር ድርጀቶች ጋር በመሆን የስደተኞች ሕይወት እንዲሻሻል እየሠራች ነው፡፡ የሕፃናት አድን ድርጅት ደግሞ ከ27ቱ የስደተኛ ካምፖች በ13ቱ ውስጥ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም 260,000 ሕፃናትን ጨምሮ 461,240 ስደተኞችን እየደረሰ ነው፡፡

ከ72 ሺሕ በላይ ስደተኛ ሕፃናት ድርጅቱ በሚረዳቸው 78 አማራጭ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብተዋል፡፡ 783 መምህራንና 516 የወላጅ መምህር አባላት የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን አግኝተዋል፡፡ ተማሪዎችም በመማሪያ ቁሳቁስና በመጫወቻ ዕቃዎች እየተደገፉ ነው፡፡ 78 ጊዜያዊ የመማሪያ ቦታዎችና 37 ጊዜያዊ የመማሪያ ክፍሎችም ተሠርተዋል፡፡ በሕፃናት ጥበቃ ዙሪያም የግንዛቤ ማስጨበጫዎችና ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ፡- ድርጀቱ ከሚሠራቸው በጎ ሥራዎች ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ባህል ያልሆኑ አመለካከቶችን ያንፀባርቃል እየተባለ ይታማል፡፡ በተለይ ግብረ ሰዶማዊነትን ያበረታታል እየተባለ ነው፡፡ ለዚህ ምን ምላሽ አላችሁ?

የሕፃናት አድን ድርጅት፡- ድርጅቱ በሕፃናት ላይ አተኩሮ ሕፃናት እንዳይሞቱ፣ እንዲማሩ፣ እንዲጠበቁና የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው እየሠራ ይገኛል፡፡ የ2030 ዕቅዱም ሁሉም ሕፃናት ከየአገልግሎቱ ተጠቃሚና መልካም ዜጋ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ስለሚባለው ጉዳይ የምናውቀው ነገር የለም፡፡

በዚህ ጉዳይ፡- ከዚህ በኋላ ያላች ዕቅድ ምንድነው? ከኢትዮጵያ መንግሥትስ ምን ትጠብቃላችሁ?

የሕፃናት አድን ድርጅት፡- ድርጅቱ ሥራውን ይቀጥላል፡፡ ከ2015 ወዲህ የ134 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ አድርገናል፡፡ በ2017/18 ምላሽ ለመስጠትም ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ በተለያዩ አደጋዎች የሚጎዱ ማኅበረሰቦች ችግሮችን የሚቋቋሙበትን አቅም እንገነባለን፡፡ የልማት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታትም እንሠራለን፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አብረን እየሠራን ሲሆን፣ ወደፊትም ይህ እንዲቀጥል እንፈልጋለን፡፡ ሥራዎቻችን በሙሉ ዓላማ ያደረጉት በ2030 ሕፃናት በሙሉ የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ ማድረግ ላይ ነው፡፡