Skip to main content
x

ወቅቱ ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከር ይጠይቃል

በጥላሁን ጣሰው

መሰንበቻውን ኢኤንኤን ቴሌቪዥን ላይ የቀረቡ ዶ/ር መርሐዊ ጎሹ የሚባሉ ምሁር ስለትምህርትና ፈተና ሲናገሩ፣ ማመዛዘን የሚችለው በግንባራችን በኩል ያለው የአዕምሮ ክፍል ሙሉ አቅም የሚደርሰው ከሃያ አምስት ዓመት ዕድሜ በኋላ ነው ብለው ሲናገሩ ሰምቼ፣ 1950ዎቹ መጨረሻና በ60ዎቹ መጀመርያ የነበርን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከምናነባቸው መጽሐፎችና ከምንሰማቸው ወሬዎች ጋር በማመሳሰል ዘዴ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮችን ስንተረጉም የነበረው በጨቅላ አዕምሮ ለመመራመር ያህል እንጂ፣ ተመዝኖና እንከን የማይወጣለት የሃይማኖት ቀኖና ለመሰንዘር እንዳልነበር ለማሳየትም የሚያስችል አባባል ይሆናል የሚል ሐሳብ አጫረብኝ። ተከታትሎም ፕሮፈሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ለአቶ ለማ መገርሳና ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የጻፉትን ግልጽ ደብዳቤ አነበብኩ። አቶ በረከት ስምዖን በወቅቱ የሚታዩት ችግሮች ከፌዴራል ሥርዓቱ ተያያዥነት እንደሌላቸው ማብራሪያ ሲሰጡ በቴሌቪዥን ተመለከትኩ። እነዚህ ጉዳዮች በጊዜ ሒደት ወደ ኋላም ወደ ፊትም በመመልከት ይህን ጽሑፍ እንዳቀርብ ገፋፉኝ።

በ1960ዎቹ የከፍተኛ ትምህርት ቆይታዬ በማመሳሰል ታሪክ አጻጻፍና የፖለቲካ ማኒፌስቶ አወጣጥ የማስታውሳቸው ተማሪዎች ዋለልኝ መኮንንና ብርሃነ መስቀል ረዳ ናቸው። ሁለቱም በማርክሲዝም ሌኒኒዝም አተያይ እሳቤ ፈጥረናል ብለው በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦች፣ ሶቪየት ኅብረትን እንደመሠረቱት ብሔሮች መቆጠርና የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል ተከብሮላቸው አንድ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንደ አዲስ መመሥረት እንችላለን የሚል እሳቤ አራመዱ። የእነዚህ ወጣቶች አስተሳሰብ ከጣሊያን ወረራ በፊት ኢትዮጵያ ጥቁር ዘርን ነፃ ለማውጣት የምትሠራ ስለሆነ እንድትጠፋ የራስን ዕድል በራስ መወሰን በኢትዮጵያ ደቡብ ለሚገኙ ሕዝቦች እንዲሰጥና የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት እንዲዳከም መደረግ አለበት ሲል አውሮፓውያንን ይመክር የነበረው የኦስትሪያው ፋሺስት ሮማን ፕሮቻዛክ አካሄድ ጋር ማነፃፀሩ አስፈላጊ ነው።

ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ የኦስትሪያ ኤምባሲ ሠራተኛ የነበረው የፋሺዝም አቀንቃኝ ሮማን ፕሮቻዝካ፣ ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ቀደም ባለው ጊዜ ስለነበረችው ኢትዮጵያ አንድ የፕሮፓጋንዳ ጽሑፍ አውጥቶ በቢቢሲ በኩል ተሠራጭቶለት ነበር። በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ አካባቢ ያሉት ቅኝ ገዥዎች (ጣሊያን፣ እንግሊዝና ፈረንሣይ) ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝብን በማስተባበር ቅኝ ግዛትን ለማስወገድ ትሠራለች የሚል ሥጋት ስለነበራቸው፣ ሮማን ፕሮቻዝካ የዘመኑ የአውሮፓ ዘመናዊ አስተሳሰብ የሚባሉትን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ውድሮው ዊልሰን የራስን ዕድል በራስ መወሰን እሳቤና የሌኒን የብሔር ጥያቄን ማመሳሰያ በማድረግ፣ ‹‹አማሮች›› የሚላቸው ትግራዮች፣ ጎጃሜዎችና ኦሮሞዎች በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙትን ሕዝቦች ይጨቁናሉ የሚል እሳቤ አራመደ። ከዚያም በደቡብ ያሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት ቢሰጣቸው ከኢትዮጵያ በፈቃዳቸው ስለሚገነጠሉ፣ የቅኝ ገዥዎች ጠላት የሆነችው ኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግሥት እንዲዳከም በማድረግ የቅኝ ገዥዎች ሐሳብ እንዲሳካላቸው ማድረግ ይቻላል የሚል መጽሐፍ ጻፈ። ሮማን ፕሮቻዛካ የሌኒንን ከካፒታሊስት ዕድገት ጋር የአገር ምሥረታን ማያያዝን ስላልተጠቀመ ሌላው ቢቀር አማራ ብሎ የሰየማቸው ትግራዮች፣ ጎጃሜዎችና ኦሮሞዎች ኢትዮጵያ የምትባል አገር ሰዎች መሆናቸውን አልካደም። ጣሊያን ኢትዮጵያን ይዛ በቆየችባቸው አምስት ዓመታት (1928-1933) የጣሊያን መንግሥት ፕሮቻዝካ ትግራዮች፣ ጎጃሜዎች፣ ኦሮሞዎች ብሎ በአማራነት ያጠቃለላቸውን እንደገና በመሸንሸን ትግራዮችን በኤርትራ ውስጥ ጠቅልሎ ኦሮሞዎችን ከሲዳማ ጋር አድርጎ አማርኛ ተናጋሪ ጎጃም፣ ጎንደርና ወሎን ‹‹አማራ›› ብሎ በካርታ አስፍሮ ለከፋፍለህ ግዛ ዓላማ ‹‹የጣሊያን የምሥራቅ አፍሪካ ኢምፓየር›› በሚል መጠሪያ ተግብሮት ነበር።

ዋለልኝ መኰንን ግን በማርክሲዝም ሌኒኒዝም ሽፋን የኢትዮጵያን አገርነት በመካድ ሮማን ፕሮቻዝካ ትግራዮችን፣ ጎጃሞችንና ኦሮሞዎችን በአንድ ላይ ‹‹አማራ›› ብሎ የጠራቸውን በቋንቋ ላይ በመመሥረት አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሞ፣ ሐረሪ፣ ሶማሌ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ በማለት ነጣጥሎና ከፋፍሎ ብሔራዊ አገር የሚፈጠረው እነዚህ በእኩል የሚሳተፉበትና በኢኮኖሚና በባህል አንዱ ሌላውን በማይጨቁንበት ነው ሲል ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን በጥራዝ ነጠቅነት በማጣቀስ፣ እያንዳንዱም እሱ ብሔር ብሎ የሰየማቸው ጎሳዎች የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል ለሁሉም መብት መሰጠት አለበት ሲል፣ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መጽሔት ላይ የመወያያ ሐሳብ አድርጎ አቀረበው። የዋለልኝና የብርሃነ መስቀል ጽሑፎች አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግራይ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ወዘተ ሲሉ በጥልቅ የተመራመሩበት ስላልሆነ በደምሳሳው እንጂ እንደ ጣሊያኑ በካርታ ላይ የተቀመጠ በታሪክ የሚታወቅ ወይም እነሱ እንዲህ ነው ብለው የፈረጁት ጆግራፊያዊ ክልሎች ወይም ብሔራዊ መንግሥታት አልነበሩም። ዋለልኝ ሮማን ፕሮቻዝካ አማራ ብሎ ካጠቃለላቸው ትግራዮች፣ ጎጃሜዎችና ኦሮሞዎች ውስጥ ጣሊያኖቹ እንዳደረጉት ኦሮሞዎችን ነጥሎ በማውጣት ጎጃሞችን ከሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች በመደመር የአማራና ትግራይ ገዥ የነፍጠኛ ሥርዓት የሚለውን እሳቤ አራመደ። ዋለልኝ በግልብ አስተሳሰብ ሶሻሊስት ኤርትራና ሶሻሊስት ባሌ በማለትም በየጠቅላይ ግዛቱ የሚመሠረቱ ሶሻሊስት አገሮች ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሁሉ ለመጻፍ አላወላዳም።

በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረችው ኤርትራ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ያላት ጠቅላይ ግዛት ብትሆንም፣ ዋለልኝ እያንዳንዱ በኤርትራ ውስጥ የራሱ ቋንቋ ያለው ብሔር ነው ለማለት አልደፈረም። ምክንያቱም በዚያን ወቅት የኮሮኮዳይል አባላት የሆኑት ዋለልኝም ሆነ ብርሃነ መስቀል ከጀብሃ ጋር ይሠሩ ስለነበር ነው። ከጀብሃ ከራሱ ታሪክ መጣጥፍ እንደምናየው ብርሃነ መስቀልና ዋለልኝ አውሮፕላን እንዲጠልፉ ያስተባብር የነበረው የጀብሃ አባል አንዳንድ ጊዜ አማኑኤል ዮሐንስ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ  መሐመድ ተብሎ የሚጠራ የዋህ መሳይ ሰው ነበር። እሱ የጀብሃ እንቅስቃሴ ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም የሚተርፍ ተራማጅ እንቅስቃሴ እንደሆነ ይሰብካቸው እንደነበር ተጽፏል።

በዚህ የማመሳሰል ታሪክ ሮማን ፕሮቻዝካ በትግራዮች፣ ጎጃሜዎችና ኦሮሞዎች የተጨቆኑት የደቡብ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ መወሰን ዕድል ቢሰጣቸው ከኢትዮጵያ ነፃ መውጣትን ይፈልጋሉ ብሎ ሲከራከር የነበረውን፣ ዋለልኝ ኢትዮጵያን ከሶቪየት ኅብረት ጋር  በማመሳሰልና የኢትዮጵያን አገርነት በመካድ አዲስ ብሔራዊ አገር መመሥረት ያስፈልጋል ሲል ተከራከረ። ሮማን ፕሮቻዝካ በግልጽ ኢትዮጵያን ለማዳከም የራስን ዕድል በራስ መወሰን አስፈላጊ ነው ያለውን የጠላት ፕሮፓጋንዳ በሚያስንቅ መልኩ፣ ዋለልኝ ኢትዮጵያ የምትባል ብሔራዊ አገር የለችም በማለት ህልውናዋንም የካደ ጽሑፍ አቀረበ።

ወቅቱም የአፍሪካ አንድነት እንዲፈጠር በአፄ ኃይለ ሥላሴ አስተባባሪነት የአፍሪካ መሪዎች ደፋ ቀና የሚሉበት ጊዜ ስለነበር፣ ተገንጣይ ቡድኖችና ኢምፔሪያሊስቶች ይህንን የአፄ ኃይለ ሥላሴን የአፍሪካ አንድነት ጥረት ለማጥላላት ‹‹እንኳን አፍሪካን አንድ ማድረግ ቀርቶ ኢትዮጵያም አንድ አይደለችም፤›› የሚል አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ የሚያስተላልፉበት ወቅት ነበር። የአፍሪካ አገሮችም ‹ትራይባሊዝም›ን እንደ አደጋ ይቆጥሩ ነበር። ይህ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳም ቅድመ ጣሊያን ወረራ ቅኝ ገዥዎች ሲሉት ከነበረው ጋር ተያያዥ እንደሆነ ማስታወሱ ይበጃል።

ብርሃነ መስቀል ረዳ ምንም እንኳን እሱም ከጀብሃ ጋር በመሥራት አውሮፕላን ጠልፎ አልጄሪያ ቢያከትምም የዋለልኝ ሐሳብን በሌላ የማመሳሰል ዘዴ በማስተካከል፣ ትክክለኛው የኮሙኒስት አስተሳሰብ የሶቪየት ኅብረት አባል አገሮች የሆኑት በዋናው ኮሙኒስት ፓርቲ መሪነት የተሰባሰቡ የየብሔሩ የኮሙኒስት ፓርቲዎች ጥምረት ነው በማለት፣ በኢትዮጵያም ኮሙኒስቶች በየብሔራቸው ተደራጅተው በኢትዮጵያ ኮሙኒስት ፓርቲ መሪነት የኢትዮጵያ ሶቪየት ኅብረትን ይመሠርታሉ በማለት ማኒፌስቶውን አወጣ። የዚህ አፈራረጅ ጉዳይ ደጋፊና ባለቅሬታ ኮሙኒስቶች ያደረጉት ትግል በኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ) እና መኢሶን (የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ) ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ የታዘበው ነው።

ይህ ከሁለትና ከሦስት መቶ ዓመታት በፊት በአውሮፓ ውስጥ ያሉ አገሮች ከተመሠረቱበት ሒደትና ከሶቪየት ኅብረት ጋር ኢትዮጵያን ያላግባብ በማመሳሰል ‹‹ኢትዮጵያ ገና የምትመሠረት ናት›› የሚለው አስተሳሰብ እንዴት እንደመጣ ወደፊት የታሪክ ጸሐፊዎች የሚመራመሩበት ነው። ኢትዮጵያ እንደ ጃፓን፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ቱርክ፣ ኢራን የመሳሰሉ አገሮች የረዥም ዘመን ህልውና ያላትና ከአውሮፓ ጋር የማወዳደር አስፈላጊነት የማይታሰብ ሊባል ይችላል። ጣሊያን ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ትንሽ ቀደም ብሎ አሁን ያሉዋትን ክፍሎች በማዋሀድ የተፈጠረች ነበረች። የጀርመንም ውህደት እንደዚሁ ነው። የሶቪየት ኅብረት ከሩሲያ አብዮት በኋላ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አሁን ነፃ የሆኑትን ላቲቪያ፣ ሉቲንያ፣ ዩክሬን፣  ወዘተ የመሳሰሉትን በማስተባበር የተቋቋመች ናት። የትኛቸውም ከኢትዮጵያ ጋር የሚያመሳስላቸው የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አወቃቀር የላቸውም።

ከላይ ያለውን ማስተዋል የሚጠቅመው፣ አንድ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በተማሪዎች ማኅበር መጽሔት ላይ ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን ኢትዮጵያን በሚመስል አገር ላይ ያለውን አንድምታ በመጻፉ ይህ ጽሑፍ በምሁራን ተመርምሮ በምርምር መጽሔቶች ላይ የወጣ ያህል፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በጥቂቶች እየተሰበከ ቆይቶ በቀዝቃዛው ጦርነት ማለቅ ወቅት የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል ወሳኝ ሆኖ ብቅ ማለቱ ነው።

የኢሕአዴግ (የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር) ከሥልጣን ላይ መውጣትን በሰሜን ኢትዮጵያ ካካሄደው ትግልና ከቀዝቃዛው ጦርነት ማለቅ አዲስ የዓለም ሥርዓት መመሥረት ጋር አያይዞ ማየቱ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንዴት እንደተመሠረተ ለማየት ያስችላል። የሶቪየት ኅብረት መዳከምና ከኢትዮጵያ የወጣችበት ወቅት የትግራይ ሕዝብ የደርግን የአፈናና የኮሙኒስት ሥርዓት አውድሞ ነፃ የወጣበት ወቅት ነው። በዚህ ወቅት ከሌሎች ወንድሞቹ እንዳይቃቃር አስተዋዩ የትግራይ ሕዝብ ራሳችንን ከደርግ ነፃ ካወጣን ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ ሌላውም ራሱን ነፃ ያውጣ ብሎ የወሰነበትና ሕወሓት (ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) እና ኢሕዲን (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ችግር ውስጥ የገቡበት ነው። መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም ከሕወሓት የቀረበለትን የሽግግር መንግሥት ማቋቋምን ተቀብሎ የተኩስ ማቆም ሐሳብ፣ በትግራይና በሌሎች ሕዝቦች መካከል መጋጨቱ እንዲፈጠር ሲል እንቢ አለ። አሜሪካም ሕወሓትን ደግፋ አዲስ አበባም ደም ሳይፋሰስ በሰላም ለማሸጋገር መሥራቷን ቀጠለች። የዚህን ጊዜ ነው የዋለልኝ መኰንን ሐሳብ የተንሰራፋውና ወደ መሀል ኢትዮጵያ ዘመቻውም ‹‹ዘመቻ ዋለልኝ›› ተብሎ የተሰየመው። እንደ ዋለልኝ መጣጥፍ ባሌና ኤርትራ ባይሆኑም ትግራይ ሶሻሊስት ሆናለች።

ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን የመጣው ሶቪየት ኅብረት እየፈራረሰች በነበረበት ወቅት በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ የየብሔሩን ኮሙኒስቶች በማስተባበር በሩሲያ ይመራ እንደነበረው ሶቪየት ኅብረት  ትመሠረታለች ለማለት ዘመኑም ስለማይፈቅድ የዋለልኝና የብርሃነ መስቀል እሳቤዎችን ማስተካከል ያስፈልግ ነበር። ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ከሶቪየት ኅብረት ሳይሆን ከአውሮፓ ኅብረት ማመሳሰል መጀመሩን ያወቅኩት ኒዜርላንድ ሳለሁ፣ በኋላ አፈ ጉባዔ ሆነው የነበሩት አቶ ዳዊት ዮሐንስ በኔዘርላንድ አይኤስኤስ ትምህርት ቤት መጥተው ሲናገሩ ነው። የኢሕአዴግ ዓላማ በአውሮፓ ኅብረት  እንደምናየው በኢትዮጵያም አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው ሲሉ ንግግር አደረጉልን። ይህ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ  ለመመሥረት እሠራለሁ ሲል ከማርክሲዝም ሌኒኒዝም ጋር በጥራዝ ነጠቅነት ኢትዮጵያን ከሶቪየት ኅብረት አመሠራረት ጋር ማመሳሰሉን አለመተውን የሚያመለክት ነበር። ኢሕአዴግ ቆየት ብሎ የሶሻሊዝም ህልሙን ትቶ ነጭ ካፒታሊዝም እገነባለሁ ባለበት ወቅትም የብሔር ጥያቄን ለብቻው አንጠልጥሎ ለመቀጠል ያስቻለው የአውሮፓ ኅብረትን ምሳሌ አድርጎ ነው።

ብርሃነ መስቀል የዋለልኝን ሐሳብ ያስተካከለበትና ኢሕአዴግ የብርሃነ መስቀልን እሳቤ ያስተካከለበት አካሄድ ሁለቱም በአገር ፍቅርና የመጀመርያው ጀብሃን ለማርገብ፣ ሁለተኛው ሻዕቢያን ለማርገብ ሊሆን ይችላል። ጀብሃ ከፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት ጋር ባለው ግንኙነት ማሸበርና አውሮፕላን ጠለፋን አባላቱ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን እየመለመሉ እንዲያከናውኑ ሲያደርግ፣ ለዚህም የሚያገለግለውን ርዕዮት የሮማን ፕሮቻዛክ ፋሺስታዊ ርዕዮትን ከሶቪየት ኅብረትና ከሶሻሊዝም ጋር በትንሹ ማቀናጀቱ ጠቀሜታው ታይቶታል። ጀብሃ የብርሃነ መስቀል ረዳን የብሔር ጥያቄ ኤርትራም ውስጥ የኤርትራ ኮሙኒስት ፓርቲ መመሥረትን የሚደግፍ አካሄድ በመሆኑ የማይስማማበት ቢሆንም፣ አደገኛነቱ ግልጽ አልሆነለትም ነበር። የብርሃነ መስቀል አተረጓጎም ውሎ አድሮ ኤርትራውያን ተከታዮችን በማፍራቱ ጀብሃን የተካው ሻዕቢያ ይህ አካሄድ ስላላማረው፣ ትግሉ የብሔር ጥያቄ ሳይሆን ከቅኝ ግዛት ነፃ የመውጣት ነው ብሎ ደንግጎ ይህንን ኤርትራ በኢትዮጵያ የተያዘች ቅኝ ተገዥነት ያልተቀበለ ተማሪና ተራማጅ አድሃሪ መሆኑን አስነገረ። ከሶቪየት ኅብረት መፍረስ በኋላ ኢሕአዴግ በአዲስ አበባ፣ ሻቢያ በአስመራ ሥልጣን ሲይዙ ኢሕአዴግ የብሔር ጥያቄ አተረጓጎምን እንደ አውሮፓ ኅብረት አንድ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማኅበረሰብ የመፍጠር ሒደት ሲያደርገው ሻዕቢያ የሚቀበለው አልነበረም። እንዲያውም በጋራ አገር እንገንባ የሚል የሻዕቢያን የነፃነት ጥያቄ ለማጣጣል የታሰበ ተደርጎ ተወሰደ። በቋንቋ ላይ የተመሠረተው አከላለልና ይህም አከላለል መፈረካከስና ዕልቂትን ሳይሆን አንድነትና ፍቅርን ያመጣል የሚለው ትንታኔም፣ በአሃዳዊ መንግሥት ሥርዓት ለተፈጠረችው ኤርትራ ምሳሌነቱ ለሻዕቢያ አላስፈላጊ ነበር።

ሻዕቢያም ኢሕአዴግ የአውሮፓ ኅብረትን እንደ ሞዴል መውሰዱ ደስ ስላላለው፣ የአማራ ገዥ መደብ የሚለውም ወደፊት የሚፈጥርበትን ችግር በማሰብ በፕሮፌሰር ጆርዳን ገብረ መድኅን በኩል ‹‹የአንኮበራይት ቲስስ›› የሚል አውጥቶ የአማራ ገዥ መደብ የሚለው ቀርቶ በአ ምኒልክ ትውልድ መንደር ላይ ማነጣጠር ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ኢሕዲን ተለውጦ ብአዴን ሆነ። በዚህም ምክንያት የፕሮፌሰር ጆርዳንን እሳቤ ውኃ በላው። ውሎ አድሮም ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ጦርነት ውስጥ ገቡ።

ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊም የብሔር አተረጓጐምን ለመለወጥ ቆየት ብለው ጀመሩ። በተለይ አዲሱ ሚሌኒየም በሚከበርበት ወቅት የኢትዮጵያን ጥንታዊነት በይፋ ተናገሩ። በአዲሱ የአቶ መለስ እሳቤ መሠረት የብሔር ጥያቄ የራስን ቋንቋ መጠቀም፣ ባህልን ማዳበርና የሥልጣን ወደ ታችኛው አካል ማሸጋሸግ (ዲሴንትራላይዜሽን) ሆነ። ይህም አቶ መለስ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ባደረጉት ውይይት የአሁኑ የፌዴራሊዝም አደረጃጀት አደጋዎች ታይተዋቸው ለማስተካከል የተደረገ ካለዚያም በምርምር የደረሱበት ሊሆን ይችላል።

የአቶ መለስ እሳቤ አሁን ያሉትን የክልል አሰያየሞች በማስተካከልና ኢሕአዴግን ወደ አንድ ፓርቲ በመቀየር በቀላሉ ሊሳካ የሚችል መሆኑ ተሰምቶኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል የአማራ ክልል ስንል አማርኛ ተናጋሪ ብቻ ያለበት ሳይሆን አገውኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ወዘተ የሚናገሩ በብዛት ሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት ስለሆነ ቀድሞ ሰጥተውት የነበረው ክልል 3 ወይም ሌላ ቋንቋ ተኮር ያልሆነ አደረጃጀት ሊስማማው ይችላል። ትግራይም ቢሆን እንደዚሁ ነው። ኦሮሚያም ቢሆን ሸዋ በሦስት በኩል ተሸንሽኖ በሦስት ክልሎች ሥር መደራጀቱ የአማራው ቁጥር አንሷል ካላልንና አዲስ አበባም የሸዋ ክፍል መሆኑን ከተቀበልን የኦሮሚያ ክልል ኦሮሚኛ ተናጋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ጉራጊኛ፣ ወዘተ የሚናገሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት ነው። ምናልባት ክልል አራት የሚሉት ወይም ሌላ ቋንቋ ተኮር ያልሆነ አደረጃጀት ሊስማማው ይችላል። ለሌሎቹም ክልሎች ይህ ያስኬዳል። እያንዳንዱም ክልል በውስጡ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች ስላሉት የየክልሉ መሪዎች ኃላፊነት በክልላቸው ለሚኖረው ሁሉም ሕዝብ እንጂ፣ ለራሳቸው ቋንቋ ተናጋሪ እንዳልሆነ ማረጋገጥ ይገባቸዋል። ይህ ከሆነ በኋላ የእያንዳንዱ ዜጋ መብት በሕግና በእኩልነት ከታየ ከሃያ አምስት ዓመት ዕድሜ በታች የሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያቀነቀኑትን ሐሳብ እንደ ሃይማኖት ከማነብነብ ሊገላግል ይችላል።

የአቶ መለስ ሐሳብ ግን በመታመማቸው፣ ከዚያም በመሞታቸው ሳይተገበር ቀረ። በአሁኑ ጊዜ የብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣትና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች በአውሮፓ ኅብረት ላይ ሲጋፈጡበት፣ “አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመፍጠር” የሚለውን የፕሮቻዛካ - ዋለልኝ - ብርሃነ መስቀል አካሄድ ጋር ተጋምዶ የተሠራውን ኢትዮጵያን ከአውሮፓ ኅብረት የማመሳሰል እሳቤን አደጋ ላይ ጣለው። ኢሕአዴግም የመለስን ሐሳብ ከመተግበር ይልቅ “በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያዊነት” የሚል እሳቤ ማራመድ ጀመረ። ይህ እሳቤ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ተብሎ ያስከተለውን ለሚያውቅ ሰው በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያዊነት የሚለው ጊዜው ያለፈበት ስለሆነ እምብዛም ሊጻፍበት አይገባ ይሆናል። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሶቪየት ኅብረት የየፌዴሬሽኑ ዜጎች ለሶቪየት ኅብረት ፍቅራቸውን የሚገልጹበት የነበረ ከኢትዮጵያ ጋር እንደ ብሔር ጥያቄ ሁሉ አግባብ የሌለው ነው። (በዘመናዊው የዩኒቨርሲቲ መመረቂያ ጽሑፎች ጥራዝ ነጠቅነት ሊኳኳል ቢችልም)።

ስለዚህ ሌላው ቢቀር የፌዴራል አደረጃጀቱ ማስተካከያ እንደሚያስፈልገው ከዚህ በላይ የጠቀስናቸው ጉዳዮች ያመለክታሉ። ከላይ የተመለከትነው የማመሳሰል ታሪክ አጻጻፍና የፖለቲካ ማኒፌስቶ መክሸፍ በጀመረበት ወቅት ነው፣ አቶ ለማ መገርሳ በማመሳሰል ሳይሆን በቀደመው የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የተመሠረተ እሳቤ ያራመዱት። ቀደም ባሉት ሃያ አምስት ዓመታት ኢሕአዴግ የመሠረታቸው ክልሎች የጂኦግራፊ ካርታ ይዘው አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መመሥረት በሚል አንድ ትውልድ ስለቀረፁ ለውጡ ከፍተኛ ትግል ይጠይቃል። ሐሳቡ ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መምጣቱ ግን ተስፋ የሚሰጥ ነው። ለዚህ እሳቤ መሳካት የመጀመርያው ዕርምጃ መሆን ያለበት አማርኛና ኦሮሚኛ ኦፊሲየል ቋንቋ መሆናቸውን መቀበል ሲሆን፣ ይህም ሁሉንም የኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶችን ሰፊ ልቦና ሊጠይቅ ይችላል። አቶ ደጉ አንዳርጋቸው በሚመሩት ክልል አማርኛና ኦሮሚኛን ኦፊሲየል ቋንቋ አድርገው አንድ ጸሐፊ በአዲስ አድማስ ላይ እንደጠቆሙት ኦሮሚኛ በክልላቸው በግዕዝ ፊደል እንዲሰጥ ቢያደርጉ ለወደፊት ቀና መንገድ ይከፍታል። ብአዴንና ኦሕዴድም በሚያስተዳድሯቸው ክልሎች የተለያዩ ብዙ ሕዝቦች የሚኖሩባቸው ስለሆነ፣ የየክልላቸው አጠራር ቋንቋን ያላማከለ በማድረግና የየክልሉ ኃላፊዎችም በክልላቸው ለሚኖር ማናቸውም ሰው የግለሰብ ነፃነትና አብሮነትን መረጋገጥ ቃለ መሐላ በመፈጸምና በማረጋገጥ እንዲቻል ማድረግ ይችላሉ።

ኢሕአዴግም የአሁኑ ችግር ከፌዴራሊዝም አደረጃጀቱ ጋር ግንኙነት የለውም የሚለውን ደጋግሞ በመናገር ውጤት ሊያመጣ ስለማይችል፣ የቀድሞ አሁን ባሉት ክልሎች ውስጥ በእያንዳንዳቸው ውስጥ ብዙ ቋንቋ የሚናገሩ ስላሉ የእነሱም መብት መከበርና የክልል ኃላፊዎችም በክልላቸው ለሚኖረው ሁሉም ሰው ተጠያቂ መሆናቸውን ማመንና ማስተካከል ያስፈልገዋል።

የኢሕአዴግም ትግል ዴሞክራሲን ለማስፈንና ድህነትን ለመዋጋት በሚለው ጠበብ ያለ ግን ታላቅ አስተዋጽኦ ሊደመደም ይችላል። የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊም የኢሕአዴግና መሰል የ1950ዎቹና 60ዎች ለውጥ አራማጅ ተማሪዎች ጥቅል ሰብዕናን የሚወክሉ በመሆኑ፣ በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ትልቅ የሚሉት አስተዋጽኦዋቸው/የድርጅቱንም ሲገልጹ ‹‹ኢትዮጵያን ከመበታተን ማዳኑ›› መሆኑን ስላስረገጡ፣ ከታላላቆቹ የኢትዮጵያ መሪዎች አንዱ እንዲሆን ያበቃቸዋል። ሻዕቢያን ያህል ጠላት ያለበት ኢሕአዴግ በራሱ መንገድ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ መታገሉንና በጀብሃም ዘመን የተንቀሳቀሰው ትውልድ በኢትዮጵያዊነት ፍቅር መራመዱን መካድ አይቻልም። በዚህ ማንም በማይከስርበት ሁሉም በሚያተርፍበት ጎዳና ለመጓዝ ኢሕአዴግ የአቶ ለማ መገርሳን አስተሳሰብ ተቀብሎ ራሱን ወደ ፓርቲነት በመቀየር፣ ማኅበራዊና ግለሰባዊ መብቶች በምልዓት ለማክበር ተሟጋች ሆኖ መውጣቱ አስፈላጊ ይሆናል። በእርግጥ መናገር የሚቻለው ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያዊነት ትንሣኤ ተበስሯል። ወቅቱም ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከር የግድ ይላል።

    ከአዘጋጁ፡-  ጸሐፊው ደራሲና አማካሪ ሲሆኑ፣ በ1969 ዓ.ም. ኢምፔሪያሊዝም፣ በ1975 ዓ.ም. አዳባይ፣ በ2004 ዓ.ም. Trying Times፣ በ2008 ዓ.ም. ፍትሕና ርትዕ የሚባሉ መጽሐፎች አሳትመዋል። በቅርቡም የኢትዮጵያና የጣሊያን ሁለተኛው ጦርነት ታሪክ (2010 ዓ.ም.) የሚባል መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል። ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል።