Skip to main content
x
ለክቡር ሚኒስትሩ የድሮ ጎረቤታቸው ይደውሉላቸዋል

ለክቡር ሚኒስትሩ የድሮ ጎረቤታቸው ይደውሉላቸዋል

[ክቡር ሚኒስትሩ  ከውጭ አገር እንደተመለሱ የፋይናንስ ኃላፊውን አስጠሩት]

 • እንኳን ደህና መጡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንኳን ደህና ቆየኸኝ፡፡
 • ፈለጉኝ እንዴ?
 • በመጀመርያ እንኳን አደረሰህ?
 • ለምኑ? በዓል አለ እንዴ?
 • በጣም የምትገርም ሰው ሆነሃል፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼን ያህል ዓመት ስናከብረው የነበረውን በዓል ረሳኸው?
 • የበዓታን ክብረ በዓል ነው?
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ያው የገብርኤል በዓልም ገና ሁለት ሳምንት ይቀረዋል፡፡
 • አንተ ሰውዬ ልትመንን አስበሃል እንዴ?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • እንኳን አደረሰህ ስልህ አንዴ በዓታ አንዴ ገብርኤል ትለኛለህ፡፡
 • እንዲህማ ሊሉኝ አይችሉም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • ሕገ መንግሥቱ ካጐናፀፈኝ አንደኛው መብት እኮ የፈለግኩትን ሃይማኖት መከተል መቻሌ ነው፡፡
 • እኔም የምልህ እኮ እሱን ነው፡፡
 • ምንድነው የሚያወሩት?
 • ሕገ መንግሥቱ ያመጣልህን ሌላኛውን ክብረ በዓል ረስተሃል፡፡
 • የትኛው ነው?
 • አብዮታዊ ዴሞክራሲ፡፡
 • እሱን እናንተው ተከተሉት፡፡
 • ታዲያ እንዲህ እንድትፈነጭ ያስቻለህ ሕገ መንግሥት ያጐናፀፈህን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ረስተኸዋል?
 • እንኳን አደረሰህ ያሉኝ ለዚያ ነው እንዴ?
 • በዓሉን እንዲህ አቅልለህ ነው እንዴ የምታየው?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ በብሔር ብሔረሰቦች በዓል የብሔረሰቦችን እኩልነት ሳይሆን ያየሁት የሕዝቦችን ውዝግብ ነው፡፡
 • ምንድነው ያልከው?
 • የብሔር ብሔረሰቦችን ውዝግብ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ይኸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሳይቀሩ አይደለም እንዴ በብሔር ተከፋፍለው የሚጋጩት?
 • እንደ አንተ ዓይነቱ ናቸው እኮ ለሥርዓቱ እንቅፋት የሚሆኑት፡፡
 • እንደፈለጉ ማሰብ ይችላሉ፡፡
 • ለማንኛውም ለበዓሉ ያለህ አመለካከት ሊቀየር ይገባል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የበዓሉ አከባበር ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ቀዝቅዟል፡፡
 • ለምንድነው የሚቀዘቅዘው?
 • እንደ ድሮው ቲሸርት ማሳተም አይቻል፣ ኮፍያ ማሠራት አይቻል፣ አበሉም ቢሆን ትንሽ ነው፡፡
 • ማን ነው ያስቀረው?
 • ባለፈው የወጣውን መመርያ ረሱት እንዴ?
 • ዛሬ የፈለግኩህ ስለዚህ ጉዳይ ላወራህ ነው፡፡
 • ስለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ ውጭ ብዙ ሥራ ስሠራ ነበር፡፡
 • እሱማ ለሥራ እንደሄዱ አውቃለሁ፡፡
 • ከተሰጠኝ ዋና ሥራ ውጪ በራሴ ተነሳሽነት የሠራሁት ሥራ አለ፡፡
 • የምን ሥራ?
 • በነበርኩበት አገር የነበሩ ኢትዮጵያዊያን በብሔራቸው ተከፋፍለው ነው ያሉት፡፡
 • እሺ?
 • የክፍፍላቸው መነሻ ደግሞ የብሔሮች እኩልነት የለም የሚል ነው፡፡
 • ታዲያ እርስዎ ምን አደረጉ?
 • ልክ አገራችን እንደተከበረው የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት ለማስፈን በዓሉ እዚያም እንዲከበር አድርጌያለሁ፡፡
 • በጣም አሪፍ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በዓሉም ሲከበርም የፓናል ውይይት፣ ባህላዊ ትርዒቶችና የሻይ ቡና ፕሮግራምም ነበር፡፡
 • ምን እያሉኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ለዚህ ሁሉ ወጪ ደረሰኙን ይዤ መጥቻለሁ፡፡
 • የምን ደረሰኝ?
 • ለፓናሊስቶች፣ ለባህላዊ ተወዛዋዦች፣ ለሻይ ቡናና ለአዳራሽ ወጪ የተከፈለ፡፡
 • እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን ቀልድ ነው የምታወራው?
 • አሁን የሚነግሩኝን ነዋ፡፡
 • ስማ አሁን በአስቸኳይ ደረሰኙን ወስደህ ሒሳቡን አወራርድልኝ፡፡
 • እንዲህ ዓይነት ነገር ውስጥ እኔ አልገባም፡፡
 • አላወራርድም እያልከኝ ነው?
 • አዲሱ መመርያ ይከለክለኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለዚህ ሥራዬ እኔ እኮ የምሥጋና ደብዳቤ ነበር የሚገባኝ፡፡
 • እኔ እንዲያውም ሌላ ደብዳቤ እንዳይሰጥዎት ነው የምፈራው?
 • የምን ደብዳቤ?
 • የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ!

[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ይደውላሉ]

 • ምንድነው እዚህ አገር ላይ እየተሠራ ያለው?
 • እዚህ አገር ላይ እየተሠራ ያለውን ነገር ደጋግሜ ነግሬሻለሁ፡፡
 • እኮ ምንድነው?
 • አሁንም ልማት፣ ነገም ልማት፣ ወደፊትም ልማት ነው፡፡
 • ይኼ ቀልድህ መቼ እንደሚቆም ነው ያልገባኝ?
 • መቀለጃ ጊዜ የለንም ሴትዮ?
 • ዜጎች ሠርተው መለወጥ አይችሉም እያልከኝ ነው?
 • ዜጎች ሠርተውም ሰርቀውም መበልፀግ የሚችሉባት አገር እንደሆነች በሚገባ ጠንቅቀሽ ታውቂያለሽ፡፡
 • አሁን ግን መስረቅም መሥራትም አልተቻለም፡፡
 • ምን ተፈጠረ?
 • እኔ መኪና እያስመጣሁ እሸጣለሁ፡፡
 • አታስመጪ ተባልሽ?
 • እኔ ያው አፕ ዳውን እያልኩ ነበር የማስመጣው፡፡
 • የምን አፕ ዳውን ነው የምታወሪው?
 • የመኪናው ሒሳብና የሚቆረጠው ደረሰኝ እኩል አይደለማ?
 • Under Invoice እና Over Invoice ለማለት ፈልገሽ ነው?
 • እኔ ስሙ በደንብ ስለማይገባኝ ነው፡፡
 • ምን ሆነ ታዲያ?
 • እኔ ያው ዳውን እያደረግኩ ነበር የምጠቀመው፡፡
 • Under Invoice ማለትሽ ነው?
 • አዎን፡፡
 • እሺ፡፡
 • አሁን እሱ ተከልክሎ ባንኮች የመኪናውን ትክክለኛ ዋጋ አስቀምጠውልናል፡፡
 • ምን ማለት ነው እሱ?
 • ሌላ ዶላር ከብላክ ማርኬት ገዝቼ መሄድ አልችልማ፡፡
 • ምን እያልሽ ነው?
 • በፊት ባንኮቹ በሚፈቅዱልኝ ዶላር አሥር መኪና አስጭኜ እመጣ ነበር፡፡
 • አሁንስ?
 • ከአንድ በላይ ማስጫን አልችልም፡፡
 • ለምን ተብሎ?
 • ይኸው መንግሥት ይኼን ሁላ መንገድ እየሠራና ስንትና ስንት ሰው መኪና እየፈለገ እኔ ግን ማስመጣት አልቻልኩም፡፡
 • በአሁኑ ወቅት ግን አገሪቱ ውስጥ ብዙ ችግር ስላለ የአንቺ ጉዳይ አስቸኳይ አይመስለኝም፡፡
 • መልስህ ይኼ ነው?
 • አዎን፡፡
 • እንደዚያ ከሆነ የማደርገውን አውቃለሁ፡፡
 • ምን ልታደርጊ?
 • እገለብጠዋለሁ፡፡
 • መኪናሽን ነው?
 • አይደለም፡፡
 • ታዲያ ማንን ነው የምትገለብጪው?
 • መንግሥትን!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የድሮ ጎረቤታቸው ይደውሉላቸዋል]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ልበል?
 • የቀድሞ ጎረቤትዎ ነኝ፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • አለን ክቡር ሚኒስትር ያው ከተሾሙ በኋላ ተገናኝተን አናውቅም፡፡
 • ሁሉ ነገር ሰላም ነው?
 • ያው ሰላም ነው ለማለት እንኳን ይከብደኛል፡፡
 • ምን ተፈጠረ?
 • አገሪቱ ውስጥ ያለውን ነገር ያያሉ አይደል ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሆነ?
 • ከአዲስ አበባ ውጪ የሚሰማው ነገር እኮ ደስ አይልም፡፡
 • ከአዲስ አበባ ውጪ ምን ተፈጠረ?
 • ይኸው በየዩኒቨርሲቲዎቹ አካባቢ የሚሰማው ግጭት በጣም አሥጊ ሆኗል፡፡
 • ኧረ ሁሉም ሰላም ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ግን የደወልኩት የዩኒቨርሲቲዎቹ ጉዳይ በጣም አሳስቦኝ ነው፡፡
 • ምኑ ነው የሚያሳስብህ?
 • የመጀመርያ ልጄ ዩኒቨርሲቲ ገብታለች፡፡
 • እንኳን ደስ አለህ፡፡
 • ደስ የሚያሰኘው በፊት ነበር አሁን የተረፈኝ ሥጋትና ሰቆቃ ነው፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ይኸው በየዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በብሔር ተከፋፍለው እየተጋጩ ተማሪዎች እየሞቱ እኮ ነው፡፡
 • ይኼ እኮ ፀረ ሰላም ኃይሎች የሚያናፍሱት ወሬ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼ ወሬ ሳይሆን የአሁኒቷ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት እውነታ ነው፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • እኔ የምፈራው ልጄ አገሪቷ የደረሰችበት የብሔርተኝነት ፖለቲካ ሰለባ እንዳትሆን ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው የብሔር ፖለቲካው ጦዞ ጦዞ ተማሪዎቻችን ዘንድ ደርሷል፡፡
 • ይኼ እኮ በዕድገት ላይ ያለች አገር ከሚገጥሟት ፈተናዎች አንዱ ስለሆነ ብዙ መጨነቅ የለብህም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎማ ልጅዎን ውጭ ልከው ስለሚያስተምሩ ምንም ላይመስልዎት ይችላል፡፡
 • ምን እያልክ ነው ታዲያ?
 • አገሪቱ ውስጥ ባለው የብሔር ፖለቲካ ሳቢያ መፍትሔው አንድና አንድ ነው፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ልጆቻችን አጠገባችን ሆነው ይማሩልን፡፡
 • ምንድነው የምትለው?
 • ዩኒቨርሲቲ እዚሁ ይሠራልን፡፡
 • የት?
 • በየቀበሌያችን!

[ክቡር ሚኒስትሩ አገሪቱ በገባችበት ቀውስ ላይ ፓርቲያቸው ባደረገው ስብሰባ አስተያየት እየሰጡ ነው]

 • እኔ የሚታየኝ አንድና አንድ ነገር ነው፡፡
 • ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አገሪቱ በየቀኑ እየባሰባት እየመጣ ነው፡፡
 • በደንብ ያብራሩት እስቲ ?
 • የብሔር ፖለቲካው ተለጥጦ ሄዶ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሳይቀሩ እየተገዳደሉበት ነው፡፡
 • ምን ማድረግ እንችላለን ታዲያ?
 • እሱማ 26 ዓመት የዘራነውን እያጨድን ነው፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼ የብሔር ፖለቲካ ለአገሪቷ ችግር አዋጪ አይደለም ብዬ ነው የማስበው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ብሔር ብሔረሰቦች እኩል የሆኑት እኛ በፈጠርነው የፖለቲካ ሥርዓት ነው፡፡
 • አገሪቷ ለገባችበት ቀውስ ግን መፍትሔ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡
 • ሕዝቡ በቋንቋው እንዲማር ተደረገ፣ በቋንቋው እንዲዳኝ ተደረገ፣ ከዚህ በላይ እኩልነት እንዴት ይመጣል?
 • ሕዝቡ ፌዴራሊዝሙን የተረዳው በዚህ መልክ አይመስለኝም፡፡
 • እንዴት ነው የተረዳው?
 • አንድ ብሔር የበላይ፣ ሌላው ደግሞ ተጎጂ፣ እንዲሁም ሌላው ደግሞ ጥገኛ ነው ብሎ ነው የሚያስበው፡፡
 • እ…
 • ለማንኛውም አሁን የእናንተን ትንተናና ዲስኩር ለመስማት ፍላጎቱ ቢኖረኝም ጊዜው ግን የለኝም፡፡
 • የት ሊሄዱ ነው?
 • መሥሪያ ቤት ጋዜጠኞች እየጠበቁኝ ነው፣ የተያዘልኝ ፕሮግራም አለ፡፡
 • የምን ፕሮግራም ነው?
 • ሰሞኑን የከተማ አስተዳደሩ ለጀመረው የፅዳት ዘመቻ አርዓያ ለመሆን የአካባቢዬን ቆሻሻ አፀዳለሁ፡፡
 • አሁን መፅዳት ያለበት የጎዳና ቆሻሻ ሳይሆን ሌላ ቆሻሻ ነው፡፡
 • የምን ቆሻሻ?
 • የፓርቲያችን!