Skip to main content
x
ለ100 ሺዎች የሥራ ዕድል የመፍጠር ጅማሮ በአዲስ አበባ

ለ100 ሺዎች የሥራ ዕድል የመፍጠር ጅማሮ በአዲስ አበባ

በአዲስ አበባ ከመሬት አቅርቦት፣ ከግንባታ ፈቃድ፣ ከገንዘብ እጥረትና ከቴክኖሎጂ ኋላቀርነት ጋር የተያያዙ ችግሮች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዳይፈጠር ምክንያት ሆነዋል፡፡ የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎችም ቢሆኑ የከተማዋን ነዋሪ ጨምሮ በየዕለቱ ከየክልሉ እየፈለሱ ከተማዋን መኖሪያቸው ያደረጉ ወጣቶችና ሴቶችን ማስተናገድ አልቻሉም፡፡ በመሆኑም እንደ አንድ ማስተንፈሻ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች መደበኛ ባልሆኑ ንግዶች ተጨናንቀው ይታያሉ፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ለወንጀልና ለአደጋ መንስኤ እየሆኑ ያሉትን መደበኛ ያልሆኑ የጎዳና ንግዶች ፈር ለማስያዝ መመርያ ቢወጣም እምብዛም ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም፡፡ ተግባራዊ ለማድረግ አንዱ ማነቆ ደግሞ፣ ተግባራዊ በማድረጉ ሒደት የሚፈጠረው የበለጠ የሥራ አጦች ቁጥር መብዛት ነው፡፡

ከተማዋ እንደ ሌሎች ክልሎች በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፎች ኢንተርፕራይዞችን ወደ ሥራ ብታስገባም ዛሬም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችና ሴቶች ሥራ አጥ ናቸው፡፡ የዓለም ባንክ ዓምና በአዲስ አበባ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋፋት ያለመ ጥናት መጀመሩን ይፋ ሲያደርግ፣ ከተማዋ እ.ኤ.አ. በ2030፣ የ5.8 ሚሊዮን ሕዝብ ባለቤት እንደምትሆንና በዚህ ጊዜም 1.5 ሚሊዮን ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚጠበቅበት ገልጾ ነበር፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራው ደግሞ ከመንግሥት ብቻ የሚጠበቅ ሳይሆን የግሉን ዘርፍ ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር ማተሳሰሩ የጎላ ሚና እንደሚኖረው አሳውቆ ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በከተማዋ የሚታየውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎችን ጨምሮ ሥራ አጦችን በጥቃቅንና አነስተኛ በማደራጀት የሥራ ዕድል እየፈጠረ ነው፡፡ ሆኖም ዘርፉ ከቴክኖሎጂ፣ ከቦታ፣ እንዲሁም ከገበያ ትስስር ጋር ተያይዞ ተግዳሮቶች አሉበት፡፡

በከተማዋ አስተዳደር በኩልም ቢሆን የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ሥራ አሳልጦ በመሄዱ በኩል ችግሮች ይታያሉ፡፡ በአዲስ አበባ ሥራ አጥ ወጣቶችና ያለውን በጀት እንኳን አሟጦ ወደ ሥራ ማስገባቱ ላይ ችግር ስለመኖሩ አንዱ ማሳያውም በ2009 ዓ.ም. በየክልሉ ከተሠራጨውና አዳዲስ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል ከተባለው የአሥር ቢሊዮኑ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር በቅጡ መጠቀም አለመቻሉ ነው፡፡

አዲስ አበባ ከአሥር ቢሊዮኑ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር በ2009 ዓ.ም. ለሥራ አጦች ሥራ እንዲፈጠርበት የ123 ሚሊዮን ብር ድርሻ ብትቋደስም፣ ከዚህ ውስጥ የተጠቀመችው 21 ሚሊዮን 100 ሺሕ ብቻ እንደነበር የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በጥቅምት 2010 ዓ.ም. ያቀናጀው የአሥር ቢሊዮኑ የተዘዋዋሪ ብድር ሪፖርት ያሳያል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ተቀናጅቶ የመሥራት ችግር እንደሆነም ታውቋል፡፡

ተቀናጅቶ የመሥራትንና መሰል ችግሮችን በመቅረፍ ለአዲስ አበባ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ወሳኝ በመሆኑም ከተማው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ የሥራ ዕድል የሚፈጠሩባቸው መስኮች ላይ ጥናት አስጠንቷል፡፡

የከተማው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያስጠናው ‹‹የሥራ ዕድል የሚፈጠሩባቸው መስኮች›› ጥናት ታኅሣሥ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ለውይይትም ቀርቧል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩና የጥናት ቡድኑ አባል አቶ አብርሃም ሥዩም እንደሚሉት፣ በጥናቱ መሠረት በአዲስ አበባ ለ113 ሺሕ 627 ሰዎች የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ መስኮች ተለይተዋል፡፡

አሁን እየተሠራበት ካለው በተለየ መልኩ መሬት ማቅረብ ወይም ብዙ ቢሮክራሲዎችን ሳይፈልግ በከተማዋ ውስጥ የባከኑ ቦታዎችን በመጠቀም ምን ያህል የሥራ ዕድል ሊፈጠር ይችላል? በሚል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጠናው ጥናትም ቆሻሻ ሥፍራዎች፣ አገልግሎት ሊሰጡ ይችላሉ ተብለው የማይገመቱ እንደ ማሳለጫ መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ በየመንገዱ ያሉ ክፍት ሥፍራዎች፣ የባከኑ ቦታዎችና ያላግባብ ጥቅም ላይ የዋሉ ሥፍራዎችን ያለምንም ማፈናቀል በመጠቀም የሥራ ዕድሉ የሚፈጠርበትን አቅጣጫም አመላክቷል፡፡

ጥናቱ እስካሁን ከተለመደው አሠራር ወጣ ብሎ ብዙ የሼድ ግንባታዎችን የማይፈልጉ፣ በከተማዋ ውስጥ ጥቃቅንና አነስተኛ ለሚያመርቷቸው ምርቶች ያሉባቸውን የገበያ ችግሮች፣ የፅዳት፣ የውበትና የወንጀል ችግሮችን ሊፈታ የሚችል የተቀናጀ አሠራርን የሚያመጣ አሠራርንም አስቀምጧል፡፡

በአጠቃላይ የሥራ ዕድል ከሚፈጠርባቸው በጥቅሉ ከ113 ሺሕ በላይ የሥራ ዕድሎች 34,205ቱ በግል ድርጅቶችና በመንግሥት በቅጥር ሊፈጠሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሥራዎችን ለሌሎች በመስጠት፣ የገበያ ሰንሰለት በመሥራትና ከነባር ኢንተርፕራይዞች ጋር ትስስር የሚፈጥሩና አዲሶቹን ከነባር ጋር የሚያስተሳስሩ የሥራ ዓይነቶችም ተለይተዋል፡፡

በማምረት፣ በግንባታ፣ በንግድ፣ በአገልግሎትና የከተማ ግብርና አሁንም እየተሠራባቸው ያሉ ዘርፎች ሲሆኑ፣ ማምረት፣ ግንባታና የከተማ ግብርና ሰፊ ሥፍራ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ እነዚህን ወደ መሀል ማምጣት የማይቻል በመሆኑም በጥናቱ የተሰጠው ምክረ ሐሳብ በከተማው ግርጌ ያሉ ሥራዎች ወደ መሀል ከተማ የሚመጡበት፣ ትስስር የሚፈጠርበት አቅጣጫም ተቀምጧል፡፡

የሥራ አጥ ቁጥሩ ከፍተኛና ብዙ ወጣቶችም ከዩኒቨርሲቲዎችና ከትምህርት ተቋማት ሠልጥነው እየወጡ በመሆኑ፡፡ ኢኮኖሚው የሚፈጥረው የሥራ ዕድል ለሁሉም ይዳረሳል ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ሁሉም ተቀጥሮ ሊሠራም አይችልም፡፡ ስለሆነም ወጣቶችና ሴቶች በራሳቸው ሥራ እንዲፈጥሩ፣ በምን ሥራ ሊሰማሩ እንደሚችሉም ጥናቱ አመላክቷል፡፡

መደበኛ ያልሆነው የሥራ ዘርፍ ለኢኮኖሚው ያለው አስተዋጽኦ ቀላል ስላልሆነም ቅርፅ ማስያዝ እንደሚያስፈልግ፣ ማፈናቀል እንደማይኖር የተሻለ እንዲተዳደሩ የሚያደርግ ሥርዓት እንዲዘረጋ የመፍትሔ ሐሳብ ያቀረበ መሆኑም ተነግሯል፡፡

በጥናቱ የቀረቡት የሥራ ዓይነቶችም ትኩረት ያደረጉት በጥቃቅንና አነስተኛ ምርት በመሆኑ፣ ከውጭ የሚገቡትንም ሆነ በትላልቅ ፋብሪካዎች የሚመረቱትን አያካትትም፡፡ ይህ ዘርፍን ለማበረታታት፣ የተሻሉ ምርቶች ወደ ገበያው እንዲገቡና ኅብረተሰቡም ወደ አገር ውስጥ ምርት ፊቱን እንዲያዞር ለማስቻል ነው፡፡

ጥናቱ ከዚህ ቀደም ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ቢሮ የቀረበ ሲሆን፣ በተሰጠ ግብዓት መሠረትም ሁለተኛው በዕለቱ ቀርቧል፡፡ በአጥኚዎቹ በኩል ያለው ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ወደ ተግባር መለወጡ ደግሞ የአስተዳደሩ የቤት ሥራ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ በመሩት የውይይት መድረክም የተለያዩ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ጥናቶ በመሥሪያ ቤትም ሆነ በትምህርት ተቋማት የተሠሩ ቢሆንም፣ የመጻሕፍት መደርደሪያ ጌጥ ሆነው ቀርተዋል፡፡ አሁን የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተጠናው መልካምና አጓጊ ጥናትም፣ ወረቀት ላይ እንዳይቀር አስተዳደሩ ትኩረት እንዲሰጠውና እንዲተገብረው የሚለው ከተሰጡት አስተያየቶች ይገኙበታል፡፡

ጥናቱን ለመተግበር መሬት አስተዳደር፣ ደንብ ማስከበር፣ ግንባታና ሌሎች የሥራ ዘርፎችን አቀናጅቶ መሄድ ስላለበት የየዘርፉ መሥሪያ ቤቶች መቀናጀት ወሳኝ እንደሆነና ይህ ካልሆነ ግን በየመሥሪያ ቤቱ ያለውን ቢሮክራሲ ሰብሮ ጥናቱን ዕውን ማድረግ እንደሚያስቸግርም ተነግሯል፡፡

ጥናቱ ሲተገበር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂውን ታሳቢ እንዲያደርግ፣ በጥናቱ ምክንያት ከተማዋ ያላትን የወረደ አረንጓዴ ሽፋን ማለትም 0.3 ካሬ ሜትር በሰው እንዳታጣው ትኩረት እንዲቸርም ተብሏል፡፡

ይህ በትስስር 6,523፣ በተቋራጭ 4,055፣ በዋና መንገዶች፣ አካፋዮች፣ ድልድዮች፣ ክፍትና ጥቅም ያልሰጡ ቦታዎችን በመጠቀም ለ17,790 ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥረውን ጨምሮ ለ113 ሺሕ 627 ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል የተባለውን ጥናት በእክል ምክንያት እንዳይስተጓጎል እነዚህንና ሌሎች የተሰጡ አስተያየቶችን ከግምት በማስገባት ጥናቱ ወደ ተግባር እንደሚለወጥ ከመድረኩ ተነግሯል፡፡