Skip to main content
x
የአይኤምኤፍ ዳይሬክተር የኢትዮጵያ የገንዘብ ፖሊሲ እንዲላላ ጠየቁ
የአይኤምኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ቆይታ አድርገዋል

የአይኤምኤፍ ዳይሬክተር የኢትዮጵያ የገንዘብ ፖሊሲ እንዲላላ ጠየቁ

  • ለግሉ ዘርፍ በሩን መክፍቱ የሉዓላዊነት ችግር አያመጣበትም ብለዋል

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድ በኢትዮጵያ ባደረጉት የሁለት ቀናት ቆይታ፣ መንግሥት የገንዘብ ፖሊሲውን ማላላት እንዳለበት ጠየቁ፡፡ የተደረገውን የምንዛሪ ማሻሻያ እንደሚደግፉም አስታውቀዋል፡፡

ከታኅሳስ 4 ቀን ጀምሮ እስከ ዓርብ ታኅሳስ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በመገኘት ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ ከግሉ ዘርፍ ተዋናዮችና ከሌሎችም ጋር የተነጋገሩት ላጋርድ፣ በኢትዮጵያ የሚታዩ ለውጦችን በአዎንታዊነት እንደሚመለከቱ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የወሰደው የምንዛሪ ማስተካከያ ተገቢ እንደሆነ የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፣ ይህም ሆኖ መንግሥት የሚከተለውን የገንዘብ ፖሊሲ በማላላት በተለይ በምንዛሪ ለውጥ ረገድ ገበያ መር ሥርዓትን ሊተገብር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በተመለከተ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ላጋርድ፣ ተቋማቸው በአገሮች ርዕዮተ ዓለማዊ አመለካከት ውስጥ እንደማይገባ ቢገልጹም የኢትዮጵያ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ በሩን ክፍት ማድረግ እንደሚገባውም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመንግሥት ባለቤትነት ከሚተዳደሩ ስኬታማ ተቋማት አንዱ ቢሆንም፣ ሁሉም መንግሥታዊ ድርጅቶች ግን የአየር መንገዱን ያህል ስኬታማ ናቸው ማለት እንዳልሆነ ያብራሩት ላጋርድ፣ የግሉ ዘርፍ የሚሳተፍባቸው ዕድሎች ቢሰጡት መንግሥት ለልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች ሊያውለው የሚችለው ተጨማሪ ሀብት ማግኘት የሚችልበትን አማራጭ ሊፈጥርለት እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

መንግሥት ለግሉ ዘርፍ በሩን ቢከፍት በሉዓላዊነቱ ላይ ችግር ይመጣበታል ማለት እንዳልሆነም ለማስገንዘብ ሞክረዋል፡፡ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል የአይኤምኤፍ የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት መዘጋትን የተመለከተው ይገኝበታል፡፡ ተቋማቸው በኢትዮጵያ ያለውን ጽሕፈት ቤት እንዳልዘጋ በመግለጽ፣ አስፈላጊውን አገልግሎት የሚሰጡና መረጃ የሚያቀርቡለት ባለሙያዎችን ከኢትዮጵያ ውጪ በመመደብ እየተጠቀመ እንደሚገኝ አስታውቀው፣ ይሁንና ጽሕፈት ቤቱን የሚመሩ ከአሜሪካ የተመደቡ ሰዎች እንደሌሉ አስረድተዋል፡፡ በአይኤምኤፍ አፍሪካ ክፍል ዳይሬክተር በመሆን እንዲገለግሉ ኢትዮጵያዊውን አቶ አበበ አዕምሮ ሥላሴን ባለፈው ዓመት መሾማቸው የሚታወስ ነው፡፡

ታሪካዊ በተባለው አጋጣሚ አንድ የአይኤምኤፍ ከፍተኛ ኃላፊ ኢትዮጵያን ሲጎበኝ ክርስቲን ላጋርድ የመጀመሪያዋ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አነጋግረዋቸዋል፡፡ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሯ፣ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንደሚበረታቱ አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት የሚያከናውናቸውን ተግባራትና የሚከተላቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እንደሚደግፉ ያስታወቁት ላጋርድ፣ መንግሥት የወጪ ንግዱን ለማሳደግ ከምንዛሪ ለውጡ በተጓዳኝ ሌሎች የወጪ ንግዱን የሚያስፋፉ፣ ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን የሚያሳድጉ ዕርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባውም መክረዋል፡፡ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ወቅት የቻይና ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞንን ጎብኝተዋል፡፡ የመንግሥት ብድር እየጨመረ ስለመሆኑ ተጠይቀውም፣ አገሪቱ በርካታ የመሠረተ ልማት አውታሮች ስለሚያስፈልጓት መንግሥት ተበድሮ ለዚህ ተግባር ማዋሉ የሚደገፍ ነው ብለዋል፡፡

ይሁንና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዘጋጅነትና ጋባዥነት ባሰሙት ንግግር ወቅት 15 የአፍሪካ አገሮች ከጠቅላላ ኢኮኖሚያቸው (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የብድር ዕዳ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ በአፍሪካ በየጊዜው የሚታየው የኢኮኖሚ ዕድገት የነፍስ ወከፍ ገቢን በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ ባለመቻሉም፣ 17 አገሮች የነፍስ ወከፍ ገቢ ቅናሽ ለማስመዝገብ መገደዳቸውን በመጥቀስ ይህ ለአፍሪካ መጥፎ ዜና ነው ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ቬራ ሶንግዌም በአፍሪካ የሚታዩ ችግሮች መጠነ ሰፊ በመሆናቸው ሳቢያ፣ አይኤምፍና ተቋማቸው በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ በማቅረብ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንን ለመጀመሪያ ጊዜ ለጎበኙት ለክሪስቲን ላጋርድ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት የተመሠረተውን አይኤምኤፍ ከመሠረቱና ቀዳሚ ፈራሚ ከነበሩ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በወቅቱ የብሬተን ውድስ ተቋማት እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ መቀመጫቸውን በአሜሪካ በማድረግ በአሁኑ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ አገሮችን በአባልነት ያቀፉ ግዙፍ አበዳሪ ተቋማት ለመሆን ከመብቃታቸውም ባሻገር፣ ባላደጉትና ከምዕራባውያን የተለየ ርዕዮት ዓለም በሚከተሉ አገሮች ዘንድ ሁለቱ ተቋማት ክፉኛ የሚብጠለጠሉ የፖሊሲ መጠምዘዣ መሣሪያዎች በመሆን የሚንቀሳቀሱ ተደርገው ይታያሉ፡፡ በተለይም እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ መተግበር የጀመረው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ፕሮግራም (Structural Adjustment Program) ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገሮች ዘንድ ውድቀትን ማስከተሉ አይዘነጋም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የቡድን 20 አባል አገሮች በሆኑት በእነ ቻይናና በሌሎችም አገሮች በአይኤምኤፍ ላይ የሰላ ትችትና ወቀሳ ሲቀርብ ይመጣል፡፡ ተቋሙ ለውጥ ያስፈልገዋል፣ መታደስ ይገባዋል የሚሉ ጥሪዎችም ሲስተጋቡ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት በቻይና አዝማችነት የእስያ የመሠረተ ልማትና የኢንቨስትመንት ባንክ የተሰኘ ግዙፍ ባንክ በ100 ቢሊዮን ዶላር መዋጮ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮች አባል የሆኑበት የገንዘብ ተቋም የተመሠረተው የአይኤምኤፍን ጫና ለመቋቋም በመፈለግ ይመስላል፡፡