Skip to main content
x
ለችግሩም ለመፍትሔውም መልስ የሌለው የአስመራጭ ኮሚቴው መግለጫ
የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት

ለችግሩም ለመፍትሔውም መልስ የሌለው የአስመራጭ ኮሚቴው መግለጫ

  • ‹‹መቻቻል›› የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ?

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ቀጣይ ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ፣ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማኅበር (ፊፋ) በጠየቀው የግልጸኝነት የአካሄድ ሥርዓት በተነሳ በታቀደለት ጊዜ መከናወን ሳይችል ቀርቶ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ ፌዴሬሽኑ ለሁለተኛ ጊዜ ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ የአስመራጭ ኮሚቴ ምርጫ አከናውኖ መበተኑም አይዘነጋም፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑንና ጠቅላላ ጉባዔውን ለዚህ ሁሉ የዳረገው የፊፋ የግልጸኝነትና የሥርዓት ጥያቄን መሠረት በማድረግ የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ፣ ሒደቱን በሕግና ሥርዓት አጣጥሞ መሄድ ይችል ዘንድ፣ በተለይም የዕጩ ተወዳዳሪዎችን ግለ ታሪክና ለምርጫው የሚያስፈልጉ መሰናዶዎችን አጠናቆ ዓርብ ታኅሣሥ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል መግለጫ ሰጥቷል፡፡ መግለጫውን የሰጠው አስመራጭ ኮሚቴ በመርሕና ሥርዓት ከመሄድ ይልቅ በአብዛኛው በመቻቻል ላይ የተመሠረተ አካሄድ መከተሉ ተንፀባርቋል፡፡

በመግለጫው ከታደሙት እንደ ብዙዎቹ እምነት፣ የጠቅላላ ጉባዔውን አደራ ተቀብሎ ሥራውን የጀመረው አስመራጭ ኮሚቴው፣ እግር ኳሱን ለመምራት ለውድድር በቀረቡት ግለሰቦች ምርጫ ላይ ከማተኮር ይልቅ ሌሎች ከጀርባ ለሚከናወኑ አላስፈላጊ፣ በዋናነትም እግር ኳሱን ለማሳደግ ምንም ፋይዳ በሌለው መጠላለፍ ውስጥ ተዘፍቀው ብዙውን ጊዜያቸውን ያሳለፉ ለመሆናቸው ይናገራሉ፡፡

ለዚህም ማሳያ ከአስመራጭ ኮሚቴው ሒደት ሌላው መታዘብ የሚቻለው፣ ለምርጫው የቀረቡ ዕጩ ተወዳዳሪዎች አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ የሚገኘውን እግር ኳስ ለማሳደግና ለውጥ ለማምጣት ያላቸውን ዝርዝር ዕቅድና ፍኖተ ካርታ በመለየት ለሚመለከተው አካል አቅርበው በሐሳብ የበላይነት ወደ ጉባዔው ከማምጣት ይልቅ፣ ዘመን ባስቆጠሩ እንቶፈንቶ የመነቋቆሪያ፣ የመካሰስና የእግር ኳሱ ባህሪ ባልሆነ ፖለቲካ ላይ ያተኮሩ አስመስሏቸው ታይቷል፡፡

በመግለጫው የታደሙም ሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎችና አስተያየት ሰጪዎች እንደሚገልጹት ከሆነ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ለመምራት እየተፎካከሩ ያሉት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ሙሉ አትኩሮቶቻቸው፣ በዚህም በዚያም ብለው የኃላፊነቱን ወንበር እንዲይዙ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር፣ ዕጩዎቹ በቀጣይ ስለሚያከናውኑት ዕቅድና ዝርዝር የሚጨነቅ እንዳልነበረም ይስማማሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የፊፋን ደንብና መመርያ መነሻ በማድረግ መንግሥት በስፖርቱ ውስጥ ጣልቃ ‹‹መግባት አለበት፣ የለበትም›› በሚል ምክንያት እግር ኳሱ በሥርዓትና በዕቅድ ከመመራት ይልቅ፣ ኮሚቴው የግለሰቦችን ፍላጎትና ክብር ለማስጠበቅ መድረኩን እንደተጠቀሙበት ጭምር ሲነገር ቆይቷል፡፡

እንደ እግር ኳስ ቤተሰቡ እምነት፣ ከሁሉም በላይ በቀጣይ ፌዴሬሽኑን ለማስተዳደር የሚመጡት ሰዎች ተቋሙ ከሚታወቅበት በባለሙያ አለመመራትና ሥርዓት አልበኝነት ተላቆ ዘርፉን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ዝርዝር ዕቅዶችን ከግምት እንዲያስገቡ በተለይ ዕጩ ተወዳዳሪዎች መድረክ ተመቻችቶላቸው እንዲከራከሩ ማድረግ ይገባ እንደነበርም ያምናሉ፡፡

ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ኃላፊነቱን በይፋ የጀመረው የፌዴሬሽኑ አስመራጭ ኮሚቴ፣ ከተለያየ ቦታ የሚመጣ በመሆኑ የኮሚቴውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡ እንዲያውቀው በማድረግ ረገድ ክፍተት እንደነበረበት ሰብሳቢው አቶ ዘሪሁን መኰንን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ሆኖ ግን አስመራጭ ኮሚቴው የተቻለውን ሁሉ አድርጎ በተለይም የዕጩ ተወዳዳሪዎች ግለ ታሪክ በዝርዝር ለመመልከት እንደሞከረ፣ ውሳኔዎችን በሚመለከት ግን በአብዛኛው በእጅ ብልጫ የሆነበትን የመቻቻል አካሄድንም አስረድተዋል፡፡

አስመራጭ ኮሚቴው የጊዜ እጥረትን ምክንያት በማድረግ የየዕለቱን እንቅስቃሴ መግለጽ እንዳልቻለ ቢገልጽም፣ ኮሚቴው ተሟልቶም ይሁን ሳይሟላ ሲያሳልፋቸው የቆዩ ውሳኔዎች ይፋ የሚሆኑበት አጋጣሚም እንደነበር አቶ ዘሪሁን አልሸሸጉም፡፡ ይህም ኮሚቴው እርስ በርሱ እንዳይተማመን ግልጽ ጫና ሲያደርግ መቆየቱን ጭምር ተናግረዋል፡፡

አስመራጭ ኮሚቴ ሥራውን አንድ ብሎ ሲጀምር ሰፊ ጊዜ ወስዶ ውይይት ያደረገው፣ የአስመራጭ ኮሚቴውን የተገቢነት ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው፣ የተገቢነት ጥያቄው የቀረበባቸው ከድሬዳዋ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተመረጡት አቶ መኰንን ደስታ እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ዘሪሁን፣ የአቶ መኰንን ደስታ የተገቢነት ጉዳይ ሰፊ ጊዜ ተወስዶ ቢያከራክርም፣ ነገር ግን ደንብና መመርያን መነሻ አድርጎ ሊያሠራ የሚችል ከፌዴሬሽኑም ይሁን ከሌላ አካል ማግኘት ባለመቻሉ በድምፅ ብልጫ ተወስኖ በኃላፊነታቸው እንዲቆዩ መደረጉን ጭምር አስረድተዋል፡፡

ታኅሣሥ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በአፋር ሰመራ ሊደረግ በዕቅድ ተይዞ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ፣ ምንም እንኳ አስመራጭ ኮሚቴው ውሳኔ ባያሳልፍበትም በፈረንጆች ገና ምክንያት ወደ ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲተላለፍ መደረጉ ታውቋል፡፡ ይህንኑ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ሲያብራሩ፣ መረጃው በእነማን በኩል እንደወጣ ለጊዜው ባያውቁም፣ የታኅሣሥ 16 ምርጫ የሚራዘም ስለመሆኑ አምነዋል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ይፋዊ ውሳኔ በቅርቡ እንደሚያሳልፍ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫና ለሥራ አስፈጻሚ ምርጫ በአጠቃላይ 21 ዕጩ ተወዳዳሪዎች እንደቀረቡ፣ ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ማለትም የደቡብ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለፕሬዚዳንትነት ያቀረባቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎች አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በተያያዘ የተገቢነታቸው ጉዳይ አከራካሪ እንደነበር፣ ይህም ቢሆን ከተለያዩ አካላት በቀረቡ አስተያየቶችና ማብራሪያዎች ተወስደው በድምፅ ብልጫ ዶክተሩ ዕጩ ተወዳዳሪ ከመሆን እንደማያግዳቸው ታምኖበት ውሳኔ ማግኘቱን አብራርተዋል፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ ሲያክሉም፣ የአስመራጭ ኮሚቴውም ሆነ የዕጩ ተወዳዳሪዎች ጉዳይ በአንድም ሆነ በሌላ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲቀርብ እንደተደመጠው እያንዳንዱን ነገር በዝርዝር ተመልክቶ አሳማኝ የሆነ ውሳኔ ማስተላለፍ የሚያስችል የፊፋንም ሆነ የካፍ ደንብና መመርያ እንደሌሉ ነው ያስረዱት፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ውሳኔዎች በመርሕ ላይ ከመመሥረት ይልቅ በመቻቻል ዓይነት አካሄድ በድምፅ ብልጫ እንዲወሰኑ ምክንያት መሆኑን ጭምር ሲያብራሩ ተደምጠዋል፡፡

የፌዴሬሽኑ የምርጫ ዜና ከተሰማበት ዕለት አንስቶ በርካታ አከራካሪ ጉዳዮች ሲደመጡ ቆይቷል፡፡ ከእግር ኳሳዊ ይልቅ ፖለቲካ ይዘት ያላቸው የክልሎች የእርስ በርስ ሽኩቻና ፍትጊያ በግልፅ ሲንፀባረቅም ቆይቷል፡፡ ይህንኑ መነሻ የሚያደርጉ ነገር ግን ገለልተኛ የሆኑ ወገኖች፣ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ለአገሪቱ እግር ኳስ አንዳች የሚፈይደው እንደሌለ ነው የሚያስረዱት፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ፣ እግር ኳሱን ለዚህ ሁሉ ትርምስና ውዝግብ እየዳረገ ከሚገኘው ከአስመራጭ ኮሚቴው ጀምሮ ምክንያቱ፣ ‹‹የክልል ውክልና ሆኖብኝ እንጂ ምን የማገኘው ነገር አለ?›› የሚል እንደሆነ፣ ይሁንና የክልል ውክልና ብቻ ለዚህ ሁሉ የሚያደርስ እንዳልሆነ ጭምር የሥጋታቸውን ምንጭ ያስረዳሉ፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ መኰንን ደስታ፣ ስለ ተገቢነታቸው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹በግሌ ለዚህ ኃላፊነት በመብቃቴ ለእግር ኳሱ የድርሻዬን ለማበርከት ካልሆነ የተለየ ጥቅም ፍለጋ አልመጣሁም፡፡ የነገሮች አካሄድና አመጣጥ ካልሆነ በስተቀር አሁንም ከዚህ ኃላፊነት ብነሳ ጉዳዬ አይደለም፤›› ነበር ያሉት፡፡

አቶ መኮንን የተገቢነታቸውን ጉዳይ ከደንብና መመርያ አኳያ እንዴት እንደሚመለከቱት ሲያብራሩ፣ ‹‹በአስመራጭ ኮሚቴነት ለማገልገል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ሲመርጠኝ፣ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ስለሆነ ተገቢ ነው፣ አይደለም በሚል ውክልናዬን ማንሳት አልነበረበትም ወይ? ፌዴሬሽኑስ እንዲህ የሚል መመርያና ደንብ ካለ ጉባዔው ግንዛቤ እንዲያገኝ ለምን አላደረገም? አስመራጭ ኮሚቴው የጉባዔውን ውሳኔ የመሻር መብትስ አለ ወይ? በማለት ነበር ያብራሩት፡፡ እያከሉም ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እንጂ እሳቸውን እንደማይመለከትም አስረድተዋል፡፡

ሌላው ለአስመራጭ ኮሚቴው የቀረበው ጥያቄ፣ ለሥራ አስፈጻሚ ምርጫ የቀረቡት ዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ የአመራርነት ሚናቸው የሚወሰነው ጉባዔው በሚሰጣቸው ድምፅ ነው አይደለም? የሚል ሲሆን፣ ሰብሳቢው ለዚህ የሰጡት መልስ ‹‹ገና ውሳኔ አላገኝም›› የሚል ነው፡፡