Skip to main content
x

የሳምንቱ ገጠመኝ

የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ ከንጋቱ ሁለት ሰዓት ሲሆን የሞባይል ስልኬ ተንጫረረ፡፡ አንስቼ ሳየው ቁጥሩን አላውቀውም፡፡ ነገር ግን መልስ መስጠት ነበረብኝ፡፡  ‹‹ሃሎ ማን ልበል?›› አልኩ፡፡ ደስ የሚል የዜማ ቅኝት ያለው የአንዲት ሴት ድምፅ ተሰማኝ፡፡ ‹‹ሰላም ወንድም ያሬድ እኔ ራሔል እባላለሁ፡፡ ከአሜሪካ ለእረፍት ነው የመጣሁት፡፡ ወንድምህ ዮናስ ገንዘብ ስለላከልህ የት ተገናኝተን ልስጥህ?›› አለችኝ፡፡ ወንድሜን ከሦስት ቀናት በፊት በስልክ አግኝቼው ስለዚህ ጉዳይ አልነገረኝም፡፡ ከስልኩ በተጨማሪም በፌስቡክ መልዕክት ተለዋውጠናል፡፡ ገንዘብ ስለመላኩ አላነሳብኝም፡፡ ያም ሆነ ይህ ከድምፀ መረዋዋ ሴት ጋር የዚያኑ ዕለት ለመገናኘት ተቃጠርን፡፡

ምን እንደሆነ ባላውቀውም የሆነ ነገር ወንድሜን እንዳገኘው በጣም ውስጤን ስለገፋፋው፣ ስልኬን ከፍቼ በኢሜይል ወይም በፌስቡክ ላገኘው ስሞክር የኢንተርኔት አገልግሎት አይሠራም፡፡ ደጋግሜ ስሞክር አገልግሎቱ የለም፡፡ ሲሰለቸኝ ተውኩትና ሌሎች ተግባራትን ማከናወን ቀጠልኩ፡፡ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ሲሆን ወደ ልጅት ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ የቀጠርኳት ፒያሳ ከሲኒማ አምፔር አለፍ ብሎ የሚገኝ በጣም ዘመናዊ ካፌ ነው፡፡ ልክ ስምንት ሰዓት በቀጠሮው መሠረት ስደርስ ካፌው በወጣቶች ጢም ብሎ ሞልቷል፡፡ እንደ ምንም ብዬ ጥግ ላይ ቦታ አግኝቼ የአሜሪካዋን መልዕክተኛ መጠባበቅ ጀመርኩ፡፡

ወዲያው ከመቀመጤ ሁለት በሃያዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኙ ቆንጅዬዎች እኔ ያለሁበትን ጠረጴዛ ለመጋራት በፈገግታና በትህትና ጥያቄ ሲያቀርቡልኝ፣ በደስታ ውስጥ ሆኜ ፈቃደኝነቴን ገለጽኩላቸው፡፡ ጥሎብኝ ቆንጆ እወዳለሁ፡፡ ወይ አንዳንዱ ቀን? ድምፀ መረዋ በስልክ፣ እነዚህ ውቦች ደግሞ በአካል ሲከቡኝ ደስታው ሞቅታ ውስጥ ከቶኛል፡፡ ያቺ ድምፀ መረዋ አሥር ደቂቃ ያህል ዘግይታ አልመጣችም፡፡ ምነው ዘገየሽ ለማለት ስልኬን ከኪሴ አውጥቼ ለመደወል ስሞክር፣ የመልዕክት መቀበያና መላኪያ ማሳያው ገቢ መልዕክት እንዳለ ጠቆመኝ፡፡ ከፍቼ ሳነበው፣ ‹‹መንገዱ በትራፊክ ስለተጨናነቀ የተወሰኑ ደቂቃዎች ስለምዘገይ እባክህ ታገሰኝ፤›› ይላል፡፡ በዘንድሮ የመኪናና የኔትወርክ መጨናነቅ መታገስ ይነሰን?

ድምፀ መረዋዋ እስክትመጣ ማኪያቶ አዝዤ ያን የፈረደበትን የኢንተርኔት አገልግሎት ለማንቀሳቀስ ስሞክር አሁንም አይሠራም፡፡ ተስፋ ቆርጬ የመጣልኝን ማኪያቶ መጠጣት ስጀምር ከቆንጅዬዎቹ አንደኛዋ፣ ‹‹ወንድም ተጫወት፡፡ ብቸኝነትን መላመድ ጥሩ አይደለም…›› ብላ ግብዣ አቀረበችልኝ፡፡ ከሁለቱ ውቦች ጋር እየተሳሳቅን የባጥ የቆጡን መቀባጠር ጀመርን፡፡ ሁለቱ በነፍስ ወከፍ አንዳንድ ክለብ ሳንዱችና ጁስ አዘዋል፡፡ በተጨማሪ የልደት ኬክና ፓናቶኒ ‹‹ቴክ አዌይ›› እንዲዘጋጅ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

ክለብ ሳንዱቻቸው መጥቶ ጁሱ ከተከተለ በኋላ የተለመደው የ‹‹እንብላ›› ግብዣ ቀረበልኝ፡፡ ቁርሴንና ምሳዬን ረፋዱ ላይ ብበላም ከድምፀ መረዋዋ ጋር ምሣ ለመብላት ዕቅድ በመያዜ ‹‹የተባረከ ይሁን›› ብዬ ከግብዣው ራሴን አቀብኩ፡፡ እነ ውቢት በሚገርም ፍጥነትና የአበላል ቅልጥፍና ክለብ ሳንዱቻቸውንና ጁሳቸውን ካጣጣሙ በኋላ ማኪያቶ አዘዙ፡፡ ማኪያቶቻቸውን ካጋቡ በኋላ ‹‹ቴክ አዌይ›› ብለው ያዘዙትን የልደት ኬክና ፓናቶኒ አስመጡ፡፡ አስተናጋጁ ያመጣውን አንደኛዋ ተቀብላ መኪና ውስጥ ለማስገባት ብላ ሄደች፡፡ ሁለተኛዋ ቢሉን ተቀብላ በስልኳ ካልኩሌተር ካሰላች በኋላ ገንዘብ ለማውጣት ቦርሳዋን መደባበስ ጀመረች፡፡ በዚህ መሀል ስልኳ ጮኸ፡፡ ቦርሳዋን በእጇ እንደያዘች እየሳቀች ማውራት ጀመረች፡፡ በዓይኗ ጠቀስ አድርጋኝ ቢሉን አሳየችኝ፡፡ ግራ ገብቶኝ እየተቁለጨለጭኩ ሳያት ንግግሯን ገታ አድርጋ፣ ‹‹ሒሳቡን እንደገና አስላው፤›› አለችኝ፡፡ ቢሉን እያየሁ እኔም በስልኬ ካልኩሌተር ማስላቱን ተያያዝኩት፡፡

የበሉትን፣ የጠጡትንና ይዘው የሚሄዱትን ጭምር አስልቼ ሳጠናቅቅ ድምሩ 542 ብር መጣ፡፡ ከኪሴ ብዕር አውጥቼ ቢሉ ጀርባ ላይ 542 ብር ጽፌ ሪፖርት ላቀርብ ቀና ስል ውቢት የለችም፡፡ በስልክ እየተነጋገረች ስለነበር እስከምትመለስ የአሜሪካዋን ድምፀ መረዋ መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ ‹‹ቴክ አዌይ›› ይዛ የሄደችው አልተመለሰችም፡፡ በስልክ ስታወራ የነበረችው ጭራሹኑ ለዓይን አትታይም፡፡ የራሳቸው ጉዳይ ብዬ ወጪና ገቢውን ሳይ ሰዓቱ ነጎደ፡፡ አሁን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ሆኗል፡፡ ስልኬን አውጥቼ ድምፀ መረዋዋ ዘንድ ደወልኩ፡፡ ስልኳ ዝግ ነው፡፡ ልቤ የሆነ ነገር ጠረጠረ፡፡  እኔ ሁሌም ጠርጣሪ በመሆኔ የአሁኑ ሁኔታ አላስደሰተኝም፡፡ አስተናጋጁን በፍጥነት ጠርቼ የማኪያቶ ሒሳብ ለመክፈል ቢል አምጣ ስለው፣ የእነዚያን ቆነጃጅት ሒሳብ አንድ ላይ ደምሮ 554 ብር ክፈል አለኝ፡፡ ሳቅኩበት፡፡ የእኔ ሒሳብ አይደለማ!

አስተናጋጁ እንደ ወፈፌ እያየኝ፣ ‹‹ወንድሜ ሴቶቹ ሒሳቡን የሚዘጋው እሱ ነው ብለው ሄደዋል፡፡ በዚያ ላይ ሒሳቡን እንደ ራስህ አድርገህ ስትደምር ነበር፡፡ የማያገባህ ከሆነ ለምን ሒሳቡን ደመርክ? ጀርባው ላይስ ለምን ጻፍክ? አንድ ሰው የማይመለከተው ከሆነ የሰው ቢል የማየትም ሆነ የመንካት መብት የለውም…..›› እያለ ማብራሪያ ሲሰጠኝ ጥፋቴ ገባኝ፡፡ ማንም የማያታልለኝ አራዳ ጉድ ሆኛለሁ፡፡ ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ የተሸወድኩት ነገር እንዳለ ገባኝ፡፡ ወንድሜ ያልነገረኝ መልዕክተኛ ከአሜሪካ እንዴት መጣሁ አለች? ለምን ስልኳን አጠፋች? በቃ ተሸውጄያለሁ፡፡ ተናደድኩ፡፡ ሳላንገራግር ሒሳቡን ከነቲፑ ዘግቼ ራሴን እየረገምኩ ወደ ቤት ሄድኩ፡፡ ቤት ስደርስ ሁለት እህቶቼ በሳቅ ተቀበሉኝ፡፡ ‹‹ምን ሆናችኋል?›› ስላቸው፣ ‹‹እኔን ማንም ሊያታልለኝ ወይም ሊሸውደኝ አይችልም የምትለውን የጉራህን ልኬት ለማወቅ ነው፤›› ብለው በጓደኞቻቸው መቀለጃ መሆኔን አረዱኝ፡፡ በአራድነቴ አገር ያወቀኝን ጮካ አፈር አበሉኝ፡፡ እህቶቼ የተበላውን ገንዘቤን ቢመልሱልኝም ጉራዬ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተኖ ቀረ እላችኋለሁ፡፡ ‹‹ያራዳ ልጅ ድሮ ቀረ›› ብዬ ብቻዬን ማውራት ጀምሬያለሁ፡፡ ካለኛ ማን አለ ማለት አይደል እንዴ በየደረስንበት ሲያስቸግረን ኖሮ ይኼው አገርን ችግር ውስጥ እየከተተ ያለው፡፡

(ያሬድ ነቢያት፣ ከድል በር)