Skip to main content
x
የኮከብ ምደባ ከተካሄደባቸው 365 ሆቴሎች ውስጥ አስገዳጅ መሥፈርት ያሟሉት 167 ብቻ መሆናቸው ታወቀ
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ መዓዛ ገብረ ሕይወትና የቱሪስት መዳረሻና የደረጃ ምደባ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ማብራሪያ ሲሰጡ

የኮከብ ምደባ ከተካሄደባቸው 365 ሆቴሎች ውስጥ አስገዳጅ መሥፈርት ያሟሉት 167 ብቻ መሆናቸው ታወቀ

  • የፖለቲካ ቀውሱ የቱሪስት ፍሰቱን አልገታም ተብሏል

ከሦስት ዓመት በፊት በወጣውና ካቻምና በ365 ሆቴሎች ላይ በተደረገ የኮከብ ደረጃ ምደባ መሠረት ተገቢውን መሥፈርት በማሟላት ደረጃ ያገኙት ሆቴሎች 135 ብቻ እንደሆኑ ታወቀ፡፡ አብዛኞቹ የንፅህና፣ የአደጋ ጊዜ መውጫና ሌሎችም አስገዳጅ መሥፈርቶችን ማሟላት ባለመቻላቸው ነው ተብሏል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የዓለም ቱሪዝም ድርጅት በሰጠው ድጋፍ በስድስት የውጭ ባለሙያዎች ታግዞ በተካሄደው የኮከብ ደረጃ ምደባ መሠረት ከ400 በላይ ሆቴሎች እንደሚሳተፉ ቢጠበቅም፣ ምዘና የተካሄደባቸው በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራ፣ በትግራይና በሐረሪ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 365 ሆቴሎች ላይ እንደሆነ የገለጹት፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪስት አገልግሎት ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ናቸው፡፡

በሚቀጥለው ዓመት ዳግመኛ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የባለ ኮከብ ሆቴሎች ምደባን በማስመልከት በተጠራ ዓውደ ጥናት ወቅት በአዲስ አበባ ብቻ ምዘና የተደረገባቸው 139 ሆቴሎች ቢሆኑም፣ አስገዳጅ መሥፈርቶችን በማሟላት የኮከብ ደረጃ የወጣላቸው 80 ሆቴሎች ብቻ መሆናቸውን አቶ ቴዎድሮስ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም በኦሮሚያ የኮከብ ደረጃ ምዘና ከተደረገባቸው ከ75 ሆቴሎች 32፣ በአማራ ከ60 ሆቴሎች 19 ብቻ ደረጃቸው ይፋ ተደርጓል፡፡ በትግራይ ከ31 ሆቴሎች 11፣ በደቡብ 41 ሆቴሎች 20፣ በድሬዳዋ ከ16 አራቱ ብቻ የኮከብ ደረጃ ማግኘታቸው ይፋ ሲደረግ፣ በሐረሪ ክልል ከሦስት ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ የተሰጠው አንዱ ብቻ ነው፡፡

የኮከብ ደረጃ ምደባው ከወጣ ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላም አብዛኞቹ ሆቴሎች ለምን ደረጃ እንዳልወጣላቸው ሪፖርተር የጠየቃቸው አቶ ቴዎድሮስ፣ በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ አንደኛው የምግብ፣ የጤናና ተዛማጅ ጉዳዮችን የሚቆጣጠረው የፌዴራል የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ እንዲሁም የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር ኤጀንሲ የሚያደርጉት ክትትል መዳከምና ወቅታዊ አለመሆን ችግር ነው፡፡

እነዚህ ተቋማት አስገዳጅ የተባሉትን መሥፈርቶች በተለይም በምግብ ደኅንነት፣ በሳኒቴሽንና ኃይጂን፣ በእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ሥርዓት ውስጥ ሆቴሎች የሚከተሏቸውን አሠራሮች ፈትሸው የማረጋገጥ ግዴታ ቢጣልባቸውም፣ ይህንን በወቅቱ ተከታትለው እንደማይተገብሩ ተጠቁሟል፡፡ ለአብነት በክልሎች የሚገኙ ሆቴሎች የእሳት አደጋ ቢያጋጥማቸው በየክልሉ የእሳት አደጋ መከላከያዎች ባለመኖራቸው፣ ከአዲስ አበባ በውሰት በሚደረግ እንቅስቃሴ ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሞከር ተብራርቷል፡፡ ይህም አስገዳጅ መሥፈርቱ እንዳይሟላ ሳንካ ሆኗል ተብሏል፡፡ 

አቶ ቴዎድሮስ በሁለተኝነት የጠቀሱት የሆቴል ባለንብረቶች ያለባቸውን ችግር ነው፡፡ አብዛኞቹ ባለንብረቶች አስገዳጅ መሥፈርቶቹን በማሟላት ኮከብ ደረጃ ብቁ ሆኖ መገኘት ወጪ የሚያስከትልባቸው አድርገው ስለሚገምቱ ጭምር፣ አብዛኞቹ ሆቴሎች ደረጃ ሳያገኙ ለመቆየታቸው መንስዔ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም በመጪው ዓመት ዳግመኛ እንደሚካሄድ ለሚጠበቀው የኮከብ ሆቴሎች ደረጃ ምደባ የሚረዳ ሥርዓት መዘርጋቱን የጠቆሙት አቶ ቴዎድሮስ፣ ከዚህ ቀደም በዓለም የቱሪዝም ድርጅት ባለሙያዎች የተካሄደው ምደባ በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ ባለሙያዎች መደረግ የሚችልበት አቅም እንደተፈጠረ አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት 50 የአገር ውስጥ ባለሙያዎች ለሆቴል ምዘናና የደረጃ መስጠት ሥራ ብቁ ሆነው በመዘጋጀታቸውና ከዚህ ቀደም የነበረው አሠራርም ከፕሮጀክትነት ወደ ቋሚ ሥርዓትነት መሸጋገሩን ገልጸዋል፡፡

በአንፃሩ የሆቴል ባለንብረቶችና ኃላፊዎች ከመንግሥት ተገቢውን ድጋፍ እንደማያገኙ ሲያማርሩ ተደምጠዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረገው ምደባ ወቅት ሆቴሎች ሲፈተሹ አብዛኞቹ አገርን በሚያሳፍር ደረጃ የንፅህና ችግሮች እንደታየባቸው አቶ ቴዎድሮስ ቢገልጹም፣ የሆቴል ባለንብረቶችና ኃላፊዎች ግን በሆቴል ባለሙያዎች ችግር እንደሚሰቃዩና ተገቢውን ድጋፍ ከመንግሥት እንደማያገኙ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ባለሙያዎች የተከተሉት የደረጃ ምደባ እነሱ ከሄዱ በኋላ ‹‹ጠለፋ›› ተፈጽሞበታል ያሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ የማይገባቸውን ደረጃ እንዲያገኙ የተደረጉና የሚገባቸውን የተነፈጉ እንዳሉ በመግለጽ ‹‹በእውነት እየተሠራ አይደለም፡፡ ሒልተን ያንን ደረጃ ካገኘማ እኛ ምን ይዋጠን ብለን ዝም ብለናል፤›› በማለት ሚኒስቴሩን የወረፉት አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹እናንተ በስብሰባ ጅራፋችሁን ታጮኃላችሁ እኛም ነገ እንዲህ ይሉናል በማለት እናንተን ፈርተን ዝም እንላለን፡፡ ለአገር መሥራት አለባችሁ፤›› የሚሉ ወቀሳዎች በተሳታፊዎች ሲሰነዘሩ ተደምጠዋል፡፡

በሌላ በኩል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ መዓዛ ገብረ መድኅን፣ ሆቴሎች የሚያስክፈሉት የአገልግሎት ዋጋ እጅግ የተጋነነ በመሆኑ እንዲያስቡበት አስጠንቅቀዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ቅሬታውን እየገለጸ የሚገኘው በዚህ ጉዳይ እንደሆነ፣ የአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤትን ወደ ሌላ አገር ለመውሰድ ከሚቀርቡ ምክንያቶች አንዱ የሆቴሎች ዋጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አስጎብኚዎችም የአገሪቱ ሆቴሎች ከአውሮፓ አገሮች ከፍተኛ ዋጋ እየጠየቁ ስለመሆኑ የገለጹትም፣ አንዳንድ ቱሪስቶች ግብፅን ሁለት ጊዜ ለመጎብኘት የሚያበቃ ሒሳብ በኢትዮጵያ ሆቴሎች እንደሚጠየቁ በማስታከክ ነበር፡፡

በአገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የተፈራውን ያህል ተፅዕኖ እንዳላደረሰ ወ/ሮ መዓዛ ገልጸዋል፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ ሪፖርተር ጠይቋቸው በሰጡት ምላሽ በአገሪቱ አለመረጋጋት ቢኖርም፣ የአገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎች ከዓምናውም የበለጠ ቁጥር ያለው ቱሪስት እያስተናገዱ እንደሚገኙ የሰሜን ተራሮችና የባሌ ብሔራዊ ፓርኮችን፣ እንዲሁም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን እንቅስቃሴ ዋቢ አድርገዋል፡፡

‹‹ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ሰሜን ተራሮችን በየቀኑ የሚጎበኙ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር ሦስት ወይም አራት ነበሩ፡፡ አሁን 30 እና 40 ሰው በየቀኑ እየጎበኘ ነው፡፡ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን ዘንድሮ ካለው ቀውስ በተቃራኒው ዘርፉ ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በዚህ ዓመት 1.2 ሚሊዮን ቱሪስቶች እንደሚመጡ የታሰበው ሊሳካ እንደሚችልም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ መዓዛ ይህን ይበሉ እንጂ ከአሜሪካ ባሻገር የጀርመንና የእንግሊዝ መንግሥታት የጉዞ ማስጠንቀቂያዎችን በማውጣት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲያጤኑት አስታውቀዋል፡፡ በተለይም በቅርቡ ጀርመናዊ ቱሪስት በመገደላቸው አዳዲስ የጉዞ ማስጠንቀቂያዎች እንዲወጡ ሰበብ እየሆነ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ወ/ሮ መዓዛ ቱሪስቱ እንደሚፈለገው መጠን መምጣቱን እንዳላቆመ ከመግለጽ አልቦዘኑም፡፡