Skip to main content
x
የታላቁ ሩጫ የክልል ጉዞ ከሐዋሳ ጀመረ

የታላቁ ሩጫ የክልል ጉዞ ከሐዋሳ ጀመረ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓልን በማስመልከት ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በክልሎች ሊያከናውን ካቀዳቸው የጎዳና ውድድሮች ቀዳሚውን በሐዋሳ አከናወነ፡፡

እሑድ ታኅሣሥ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ውድድሩን የጀመረው ታላቁ ሩጫ የተለያዩ የክለብ አትሌቶች የከተማዋ ነዋሪና የንግድ ባንኩ ደንበኞችን አሳትፏል፡፡

ከ3,000 በላይ በተሳተፉበት የ7.5 ኪሎ ሜትር ውድድር ለከተማው አዲስ ገጽታ የሰጠው ኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኛ የሆኑ የውጭ ዜጎችም ተካተውበታል፡፡ በሁለቱም ፆታ ታዋቂ አትሌቶችን ያሳተፈው የጎዳና ላይ ሩጫው በተለይ ትልቅ የልምድ ማብቂያ መድረክ እንደሆነ አትሌቶቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በወንዶቹ ጥላሁን ኃይሌ ሲያሸንፍ፣ ሐርቦ ሻኖና ዴቤኮ ዴኬሞ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነዋል፡፡ በሴቶች ከደብረ ብርሃን ማሠልጠኛ ተቋም የተገኘችው ይታይሽ መኮንን፣ ቢሾኬ እሙሽና ይታይሽ ግርማ ከአንድ እስከ ሦስት ወጥተዋል፡፡ በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ላሸነፉት አትሌቶች አሥር ሺሕ፣ አምስት ሺሕና ሦስት ሺሕ ብር ተሸልመዋል፡፡

በየክልሎች በሚደረጉት ውድድሮች የሽልማት መጠኑ ከአንድ እስከ አሥር ለሚወጡ አሸናፊዎች ከ10,000 እስከ 600 የሚደርስ ሽልማት ይበረከትላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አልማዝ ኢዮቤልዩ ታላቅ ሩጫ በቀጣይ በመቐለ፣ በባህርዳር እና አዳማ የሚከናወን ሲሆን፣ የማጠቃለያ ውድድሩም በአዲስ አበባ 7500 ተሳታፊዎች ባሉበት መጋቢት 23 ቀን ይጠናቀቃል፡፡