Skip to main content
x
ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ ያተረፈው ደቡብ ግሎባል ባንክ የተከፈለ ካፒታሉን ለማሟላት እንደሚሠራ ገለጸ
አቶ አዲሱ ሃባ የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት

ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ ያተረፈው ደቡብ ግሎባል ባንክ የተከፈለ ካፒታሉን ለማሟላት እንደሚሠራ ገለጸ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ዘግይቶ የተቀላቀለው ደቡብ ግሎባል ባንክ፣ በ2009 ዓ.ም. ከታክስ በፊት 67.7 ሚሊዮን ብር አተረፈ፡፡ የተከፈለ ካፒታሉ ግማሽ ቢሊዮን ብር እንደሚያደርስ አስታወቀ፡፡

ቅዳሜ ታህሳስ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ባንኩ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት፣ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ ከ2008 ዓ.ም. አኳያ ከ253 ሺሕ ብር በላይ ወይም የ0.4 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በቀደመው ዓመት ባንኩ ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ 67.9 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህም ትርፍ ቢሆን ከሌሎች ባንኮች አንፃር አነስተኛ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል፡፡

የደቡብ ግሎባል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኑረዲን አወል፣ የ2009 ዓ.ም. የባንኩን ክንውን በማስመልከት ባቀረቡት ሪፖርት፣ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 1.4 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ጠቅሰዋል፡፡ ከ2008 ዓ.ም. አንፃር በ64.2 በመቶ ወይም በ559.8 ሚሊዮን ብር እንደጨመረም አስታውቀዋል፡፡

የባንኩ አስቀማጮች ቁጥር በ68.3 በመቶ በማደግ 61,630 መድረሳቸውን ያመለከቱት ሰብሳቢው፣ ጠቅላላ የሀብት መጠኑም 2.1 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ገልጸዋል፡፡ ባንኩ ካቻምና ያስመዘገበው ጠቅላላ የሀብት መጠን 1.3 ቢሊዮን ብር እንደነበር በማስታወስ፣ በዓምናው አፈጻጸሙ የ60 በመቶ ጭማሪ እንደታየበት  አስታውቀዋል፡፡  

በ2009 ዓ.ም. ለንግድ እንቅስቃሴዎች የብድርና የቅድሚያ ክፍያዎች የዋለው የገንዘብ መጠን 794.3 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ለዘርፉ የዋለው የብድር ሥርጭት መጠን ካቻምና ከተሰጠው የ559.3 ሚሊዮን ብር አኳያ የ32.5 በመቶ ዕድገት እንደታየበት የባንኩ ሪፖርት ያሳያል፡፡

የባንኩ የብድር ሥርጭት በየክፍለ ኢኮኖሚው ሲታይም፣ የአገር ውስጥ ንግድ 54.9 በመቶውን ብድር በማግኘት ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፍ 11.1 በመቶ፣ ሌሎችም እንደ ወጪና ገቢ ንግድ ያሉትን ጨምሮ በአጠቃላይ 34 በመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡

የዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት የሥራ አፈጻጸሙ ግን ቅናሽ እንደታበት ታውቋል፡፡ የዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎትን በተመለከተ አቶ ኑረዲን ሲጠቅሱ፣ ‹‹ከወጪ ንግዱ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ የተጠበቀውን ያህል ያልተመዘገበበት ዓመት ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ይህ በመሆኑም በ2009 ዓ.ም. ከወጪ ንግድ፣ ከዓለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊዎችና ከተለያዩ ምንጮች 26.5 ሚሊዮን ዶላር ቢሰበሰብም፣ ከካቻምናው ጋር ሲነፃፀር የ37.9 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት የተገኘው ገቢ የቀነሰበት ዋናው ምክንያትም ከዘርፉ ለማግኘት የታሰበው ገቢ በወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ ሳቢያ በመቀነሱ እንደሆነ አቶ ኑረዲን ጠቅሰዋል፡፡

ከባንኩ ጠቅላላ እንቅስቃሴ የተገኘው ገቢ 241 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከካቻምናው አኳያ የ24.2 በመቶ ወይም 46.9 ሚሊዮን ብር ብልጫ ታይቶበታል፡፡ በአንፃሩ የባንኩ ዓመታዊ ወጪ 173.2 ሚሊዮን ብር በመድረሱና ይህም ወጪ ከካቻምናው ጋር ሲነፃፀር የ47.1 ሚሊዮን ብር ወይም 37.4 በመቶ ጭማሪ ያሳየ በመሆኑ ጭምር ከፍ እያለ የመጣ ወጪ ማስተናገዱን ባንኩ አስታውቋል፡፡ ለወጪው መጨመር ምክንያት የሆኑት የአስተዳደራዊ ወጪዎች፣ የወለድ ክፍያ፣ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ወጪዎች ጭማሪ በማስመዝገባቸው እንደሆነ ቦርድ ሰብሳቢው ባቀረቡት ሪፖርት አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 351.2 ሚሊዮን ብር መድረሱ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ቢሆንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ፣ የባንኮች የተከፈለ ዝቅተኛው ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር መሆን እንዳለበት ካሳለፈው መመርያ አኳያ ባንኩ ዝቅተኛውን የተከፈለ ካፒታል ለማሟላት 150 ሚሊዮን ብር ገደማ ይቀረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከሰኔ 2009 ዓ.ም. በኋላ በተደረገ ጥረት የባንኩን ካፒታል ከ504 ሚሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን የመጀመሪያ ዙር የ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማሟላታችን ባለአክሲዮኖቹም ያስደሰተ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡

ስለባንኩ የካፒታል መጠን የቦርድ ሰብሳቢው በሪፖርታቸው፤ ‹‹በአሁኑ ወቅት እልህ አስጨራሽ በሆነ መልኩ የቦርድ አባላት፣ ማኔጅመንትና ሠራተኞች ባደረጉት ርብርብ ሪቴንድ ኧርኒንግ [ካልተከፋፈለ ትርፍ] ጋር ተዳምሮ በአሁኑ ወቅት የባንኩን የተከፈለ ካፒታል የሚሟላ ይሆናል፤›› በማለት ባንኩ የገዥው ባንክን ግዴታ ለማሟላት እንደቻለ ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ሆኖ ብሔራዊ ባንክ የ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ጣሪያ እንዲሟላ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ነሐሴ 2009 ዓ.ም. እንደሆነ ቢታወቅም፣ ደቡብ ግሎባል ባንክ በጠቅላላ ጉባዔው ወቅት እንዳስታወቀው፣ በዚህ በጀት ዓመት የተፈረመ ካፒታሉን ወደ 620 ሚሊዮን ብር የማድረስ ዕቅድ እንደያዘ የጠቆሙት አቶ አዲሱ፣ ወደፊትም አክሲዮኖችን በመሸጥ የባንኩን ካፒታል የማሳደግ ሥራ ይካሄዳል ብለዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም. በባንኩ የተመዘገበው የ351.2 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል መጠን ከ2008 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር፣ የ89.2 ሚሊዮን ብር ወይንም የ34.1 በመቶ ጭማሪ ታይቶበታል፡፡

ባንኩን ተወዳዳሪና ውጤታማ ሊያደርጉ የሚያስችሉ ጥናቶችን በማካሄድ በዚህ ዓመት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት፣ የወኪል ባንክና የሞባይል ባንክ አገልግሎቶችን ለማስጀመር ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡