Skip to main content
x

የዓለም ባንክ በስድስት ወራት የ1.8 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ

  • በተያዘው ዓመት ብቻ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንደለቀቀ ገልጿል

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ካሮሊን ተርክ ሐሙስ ታኅሳስ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ጋር የ470 ሚሊዮን ዶላር ብድር ስምምነቶችን ሲፈርሙ እንደገለጹት፣ ባንኩ በተቻለው ፍጥነት የፋይናንስ ድጋፎችን ለማድረግ ካለው ፍላጎት በመነሳት እ.ኤ.አ. በ2017 ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ የ1.8 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለመስጠት ቃል ከገባ በኋላ ተግባራዊ አድርጓል፡፡

በመሆኑም ባንኩ ቃል የገባባቸውን የፋይናንስ ስምምነቶች በመጠበቅ የተሰጠው ድጋፍ ለታለመለት ሥራ እንዲውል ከሥር ከሥር እንደሚለቅ ሚስስ ተርክ ተናግረዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ለመንግሥት ቃል ከተገባው ከ1.8 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ በተጨማሪ፣ ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ ባሉት ጊዜያት ውስጥም አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ መልቀቁን ባንኩ በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡

ባንኩ በኢትዮጵያ የሚያደርገው ተሳትፎና እየሰጠ ያለው ድጋፍ ከአፍሪካ ከፍተኛው እየሆነ መምጣቱ ሲገለጽ፣ በዚህ ዓመት ከለቀቀው ገንዘብ ውስጥ 3.87 ቢሊዮን ዶላር በብድር የቀረበ ሲሆን፣ 78 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ደግሞ በዕርዳታ መልክ እንደተሰጠ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ዓመት በጠቅላላው ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር እንደሚለቅ ሲጠቅስ፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ድርሻ እንደሚሆንም ይፋ አድርጓል፡፡

ባለፈው ሳምንት በተካሄደ ሥነ ሥርዓትም የ470 ሚሊዮን ዶላር የዕርዳታና የብድር ስምምነት ተፈርሟል፡፡ ከ470 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 300 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ለትምህርት ሚኒስቴር የ‹‹አጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም - ለትምህርት ፍትሐዊነት›› ለተሰኘው ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል ሲሆን፣ ቀሪው 170 ሚሊዮን ዶላር ለእስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር አዲስ ፕሮጀክት እንደሚውል ታውቋል፡፡

በመሆኑም የትምህርት ሚኒስቴር በአገሪቱ ከዜሮ ክፍል እስከ ሁለተኛ ደረጃ ለሚገኙ መደበኛ ተማሪዎችና የልዩ ፍላጎት ብሎም የሴት ተማሪዎች የትምህርት ፍትሐዊነትና የጥራት ተደራሽነትን እንደሚያሰፍንበት ለታመነበት ፕሮግራም በሚውለው ገንዘብ አማካይነት፣ 27 ሚሊዮን የሚደርሱ ተማሪዎችና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ መምህራን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሚስስ ተርክ ተናግረዋል፡፡ የልዩ ፍላጎት ትምህርት በአሁኑ ወቅት ተጠቃሚ ያደረጋቸው ሦስት ሺሕ ተማሪዎችን ቁጥር ወደ 20 ሺሕ ማሳደግም ባንኩ የሚጠባበቀው ውጤት ስለመሆኑ ዳይሬክተሯ አስውታውቀዋል፡፡ ሴት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት በሚያቀኑበት ጊዜ ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ማድረግ የመንግሥት ድርሻ እንደሆነ የጠቆሙት ሚስስ ተርክ፣ እንዲህ ያሉ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን በማስወገድ ሴቶች የእኩል ዕድል ተጠቃሚ እንደሆኑ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

እስካሁን ሲተገበር በቆየው የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ፕሮግራም፣ 250 ሚሊዮን መርጃ መጻፍሕት ለተማሪዎች እንዲሠራጩ መደረጋቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፣ 300 ሺሕ መምህራንም የክህሎትና የትምህርት ደረጃቸውን የሚያሻሽሉባቸውን ሥልጠናዎች እንዳገኙ አስታውቀዋል፡፡ ይህም ሆኖ በአጠቃላይ በትምህርት ዘርፉ በርካታ መሻሻሎች እንደሚያስፈልጉ አሳስበዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌጤ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሚኒስቴሩ እያንዳንዷን ሽራፊ ሳንቲም ለታለመላት ዓላማ በማዋል በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙትን በ20 ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አረጋግጥላችኋለሁ ብለዋል፡፡

ከትምህርት ሚኒስቴር በተጨማሪ፣ የእንስሳትና የዓሳ ሀብት ሚኒስቴር የ170 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከባንኩ ሲያገኝ የመጀመርያው እንደሆነ ሚኒስትሩ ፈቃዱ በየነ (ፕሮፌሰር) በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በትግራይ፣ በቤንሻጉል ጉምዝና በጋምቤላ ክልሎች በሚገኙ 58 ወረዳዎችን የሚያካትት የእንስሳትና የዓሳ ሀብትን በማምረትና ለገበያ በማዋል ተግባር ላይ ለሚሳተፉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አርቢዎችና በዘርፉ ለተሠማሩ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ የእንስሳት አርቢ ማኅበራት ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ የሥጋ ምርት፣ የዶሮ እርባታና የእንቁላል ምርት፣ የወተትና የወተት ተዋጽኦዎችን በብዛት በማምረት የሚሳተፉ 1.2 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ለሚጠበቀው ፕሮጀክት፣ ባንኩ ቃል የገባውን ብድር በቅርቡ እንደሚለቅ ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል፡፡

የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጋራ ለሚሠራቸው ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ በቅርቡ የአምስት ዓመት የአጋርነት ማዕቀፍ ሰነድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የሚውል የአምስት ቢሊዮን ዶላር ብድርና ዕርዳታ እንደሚሰጥ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡