Skip to main content
x
ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ላይ ከግብፅ ጋር ብቻ የሁለትዮሽ ምክክር አይደረግም አለች
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ከግብፅ አቻቸው ሳሜህ ሽኩሪ ጋር ማክሰኞ ታኅሳስ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ላይ ከግብፅ ጋር ብቻ የሁለትዮሽ ምክክር አይደረግም አለች

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ከግብፅ አቻቸው ሳሜህ ሹክሪ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው ሲወያዩ፣ ኢትዮጵያ ሱዳን ያልተካተተችበት የሁለትዮሽ ምክክር በህዳሴ ግድቡ ላይ እንደማታደርግ አስታወቁ፡፡

ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተለይ በሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ላይ በስፋት መወያየታቸውን ማክሰኞ ታኅሳስ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ፣ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም መሠረት ሁለቱ ሚኒስትሮች በኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ፣ በሰው ኃይል ልማትና አቅም ግንባታ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ የሁለቱ አገሮች የጋራ ተጠቃሚነት የሚጠናከሩበትና የሚረጋገጡበት ሐሳቦች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን ይኼ የሁለቱ ሚኒስትሮች ውይይት ዋነኛ ትኩረቱ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ የነበረ ቢሆንም፣ ሁለቱ ሚኒስትሮች በግንባታ ላይ በሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይም ተወያይተዋል፡፡

ግድቡን በተመለከተ ከግብፅ በኩል ምንም ዓይነት ጥርጣሬና የሥጋት አመለካከት ሊኖር እንደማይገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለግብፅ አቻቸው ገልጸውላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው ፍጹም ግልጽ በሆነ መንገድና የመርህ ስምምነቱን መሠረት ባደረገ መንገድ መሆኑንም  አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረግ ውይይት በሁለትዮሽ ደረጃ ሳይሆን፣ ራሱን ችሎ በሦስትዮሽ ማለትም ኢትዮጵያን ሱዳንንና ግብፅን በማሳተፍ መሆኑን በመግለጽ፣ የሁለቱ ውይይት በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ ግንባታ በግብፅ ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንደማይኖረው በተደጋጋሚ ስትገልጽ የቆየችው ኢትዮጵያ፣ በጋዜጣዊ መግለጫውም ይኼንኑ አቋሟን አንፀባርቃለች፡፡

ዶ/ር ወርቅነህ የታላቁ የህዳሴ ግድብ በግብፅ ላይ የጎላ ተፅዕኖ ይኖረዋል አይኖረውም የሚለው የሚወሰነው በሳይንሳዊ መንገድ ነው ብለዋል፡፡

ይኼ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ የተደረገው ውይይት፣ በዋነኛነት የሁለቱን አገሮች የጋራ ጥቅሞች ሊያጠናክሩና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በሚችሉ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩበትና አቅጣጫ የሚያስቀምጡበት፣ በየሁለት ወሩ የሚካሄድ የሁለትዮሽ ውይይት አካል ነው፡፡