Skip to main content
x

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያጋጠሙ ችግሮችን እንዴት እንፍታቸው?

በአሳምነው ጎርፉ  

በ1980ዎቹ መጨረሻ አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ በምንማርበት ወቅት ከምናከብራቸው አንጋፋ ምሁራን መካካል ፕሮፌሰር መርድ ወልደ አረጋይ አንዱ ነበሩ፡፡ እኝህ የታሪክ ሊቅ ከሚናገሯቸው ተደጋጋሚ ሐሳቦች አንዱ ደግሞ እንዲህ የሚል ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የታሪክ ደሃ አይደለችም፡፡ ሲፈትናት የኖርው ነገር የኢኮኖሚና  የፖለቲካ ድህነቷ ነው፡፡ ስለዚህ በደሃና ደካማ ፖለቲካ ውስጥ መነጣጣል፣ ጥላቻና ቂመኝነት ስለማይቀር ሁሉን እያጠፋ ይቀጥላል፡፡ በተለይ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ደግሞ እነዚህን መሰናክሎች አልፎ ጠንካራ አንድነት መፈጠር ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፋዊነትንም እያነፁ መሄድ ካልተቻለ አገርን የሚጠቅም ትውልድ ለመገንባት ፈጽሞ አይቻልም፤›› ብለው ነበር፡፡ ነፍሳቸውን ይማረውና!!

ከሳምንታት በፊት ትምህርት ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2010 ዓ.ም. የበጀት ዓመትን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርብ ያነሳው አንዱ  ተግዳሮት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይ በኦሮሚያ የሰላም መደፍረስ በትምህርቱ መስተጋብር ላይ እንቅፋት ሆነብኝ የሚል ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየመጡበት ክልል አጥር ውስጥ ለመማር መፈለጋቸው፣ በብሔር ማንነታቸው መወዛገብ መጀመራቸው፣ ለተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥና በሥጋት ወደ ተመደቡበት ሥፍራ ለመሄድ መቸገር ፈተና እየሆነ መምጣቱን በአፅንኦት መግለጹ ይታወሳል፡፡

ይህ አገላላጽ ከቀናት በኋላ ደግሞ መልኩን ቀይሮ ወደ ብሔር የእርስ በርስ ግጭትና የለየለት ሁከት አድጎ ሰንብቷል፡፡ አሁንም በተለያዩ የትምህርት ተቋማት በርካታ ተማሪዎች በሥጋት ወደ ትምህርት እንዳልተመለሱም ይሰማል፡፡ ይህ እውነታ ነው እንግዲህ የአንጋፋውን ምሁር ትንቢታዊ ትንተና እንዳስታወስ ያደረገኝ፡፡

በሚኒስቴሩ በኩል በጭንቅ ሰዓትም ቢሆን ሐሳቡ በድፍረትና በግልጽነት መነሳቱ መልካም ነው፡፡ ይሁንና ሰላምም ሆነ የሕዝቦች አንድነት ያለማወላወል በወጣቱ  ልብ ውስጥ መገንባት ካልጀመረ ከውድቀት ለመዳን የሚቻል አይሆንም፡፡ እንደ አገር ክፉንም፣ ደጉንም አብሮ በአንድ አገራዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ንፍቀ ክበብ ውስጥ ሆኖ ለመዝለቅም እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን ደግሞ ደጋግሞ ማንሳት አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ይህን እውነት አብዛኛው የአገሪቱ ዜጋ እንደሚጋራውም አልጠራጠርም፡፡

የትም ሆነ መቼ ሰላም በመኖሩ ልጆቻችን ወደ ትምህርት ቤት ሄደው ይማራሉ፡፡ እኛም ከሥጋት ተላቀን በሰላም ወጥተን ሠርተን እንገባለን የሚሉ ሰዎች  ለሰላም ከሚከፈል ዋጋ በላይ ምንም እንደሌለ ሲናገሩ ይደመጣሉ። እነርሱ የሰላምን ጠቀሜታና ለእሱም የሚከፈለውን ዋጋ ውድነት በትክክል የተገነዘቡ ናቸው። ሰላም ባለበት ተረጋግቶ መኖር አለ። ሰላም በሰፈነበት ሠርቶ ማደግ፣ ወደ ትምህርት ቤት በነፃነት ሄዶ መማርና ማወቅ ይቻላል ያወቀና የተመራመረ ክፉና ደጉን ይለያል፡፡ ከግጭትናጦርነት ይልቅ ችግሮች በውይይት መፈታት እንዳለባቸው ያምናል።

ከሁሉ በላይ ማወቅና መብሰል ደግሞ ለዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ይጠቅማል፡፡ ዓለም በቋንቋ፣ በዘር፣ በቀለም፣ በሀብት መጠንና በእውቀት ሳይለያይ ከአጽናፍ አጽናፍ ተዟዙሮ በመማርና በመሥራት እየኖረ እንዳለ ለመረዳት ያስችላል፡፡ ከዘረኝነትና ከጥላቻ መነቃቀፍ ኋላቀርነትም ይታደጋል፡፡ በእርግጥ ይህን እውቀትና የሠለጠነ ልማድ በትውልዱ ውስጥ ለመገንባት ማኅበረሰቡም ሆነ ቤተሰብ ያለባቸው ኃላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡ አገር መሪ የሆነው መንግሥት ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ ሊጫወት ይገባዋል፡፡

ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተቋማት አንስቶ የትውልዱን አገራዊ ፍቅር በመገንባት የሕዝቦችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በማስረፅ ከጥላቻና ጽንፈኝነት ይልቅም ፍቅርን፣ ትብብርን በማስገንዘብ ላይ ማተኮር ነበረባቸው፡፡

 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱም ከመንደርና ከክልል አስተሳሳብ (ከፅዳት እስከ ፕሬዚዳንት የሠፈር ተወላጅ ቀጥረው፣ የዩኒቨርሲቲ ማንኛውንም ኃላፊነት በብሔር ማንነት እየሰጡ፣ የሌላ አካባቢውን ተማሪ በገዛ አገሩ እንደ ባዕድ እያዩ…) ወጥተው  የሚመጥናቸውን ዓለም አቀፋዊነትን ማስተማር ባለመቻላቸው፣ በአካዳሚክ ነፃነት ሐሳብን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመግለጽ፣ የመደራጀትና ዴሞክራሲንና አገራዊ አንድነት በተግባር የማሳየት ትግል ባለማስጀመራቸው የዘሩትን ማጨድ ጀምረዋል፡፡

 ዛሬ ላይ ብልሽቱ ድንገት እንደ ጎርፍ የመጣ ይምሰል እንጂ ለዓመታት ችግሩ ተለይቶ ለማስተካካል የተሠራ ሥራ ያለመኖሩ ውጤት መሆኑን መጠራጠር የዋህነት ነው፡፡ ስለሆነም በውጭም ያሉ በውስጥ የሚገኙ ምሁራን፣ መገናኛ ብዙኃን፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና የሙያ ማኅበራት በችግሩ መባባስ ከመወቀስ የሚድኑ አይደሉም፡፡

በእርግጥ አሁን እንደሚታየው ሰላም ከሌለ ተረጋግቶ መሥራትና መማር የሚባል ነገር አይኖርም። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ወደ ትምህርት ቤት የሚመጡ ሕፃናትና ወጣቶችም ሆኑ እነርሱን የሚልኩ ወላጆች፣ ሁልጊዜም በሥጋት ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡         

በዚህ ሁኔታ ከአሁን አሁን ምን ይመጣ ይሆን እያሉ ወላጆች ቀልባቸውን ሰብስበው የዕለት ሥራቸውን እንኳ ተረጋግተው መከወን አይችሉም። የሰላም ዕጦት የሚያስከትላቸው ችግሮች ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ህልውና የሚፈታተኑ ናቸው። ስለሆነም የሰላም መታወክ የሚያስከትለውን የዴሞክራሲ መጓደል፣ የመልካም አስተዳዳር ዕጦት፣ ኢፍትሐዊነት፣ ጠባብነት . . .  በጋራ መፋለም ግድ የሚል ነው፡፡ ካላፈው ተምሮ ዘላቂ ማስተካካይ ማበጀትም ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም፡፡

ይህን እውነታ ደግሞ ከእኛ ከኢትዮጵያውያን የበለጠ የሚረዳው ያለ አይመስለኝም፡፡ ገና ከያኔው የ1950/60ዎቹ የለውጥ ፈላጊ ትውልድ ጀምሮ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሲል ከአምባገነን ሥርዓቶች ጋር ባልተዳራጀ መንገድ ጭምር ፊት ለፊት እየተጋፈጠ በየሜዳው ደሙ የፈሰሰው፣ አካሉ የጎደለው፣ በሥነ ልቦና ጉዳት ቅስሙ ተሰብሮ የቀረው ለአባባሉ አንድ አስረጂ ነው፡፡ ከዚያም ወዲህ በትልቁም በትንሹም የፖለቲካና የኢኮኖሚ መሻሻልና ለውጥ ጥያቄ ፊት ለፊት እየተጋፈጠ ተመሳሳይ መስዋዕትነት እየከፈለ የሚገኘው የዚችው መከረኛ አገር ዜጋ ነው፡፡    

ቢያንስ በዚህ ጊዜ በመነጋጋርና በሠለጠነ መንገድ ችግሮችን መፍታት ሲቻል በመካረርና በኃይል ለመፍታት በሚደረግ ሙከራ ዜጎች መሞታቸው፣ ተማሪ ለተማሪ መተማማን አለመቻላቸው፣ እንዲሁም የአገር ሰላምና አንድነት መታወኩ ግን  የሚያሳዝን ክስተት ነው፡፡ በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በብሔር ጥላቻና በተዛባው የብሔርተኝነት ፖለቲካ ላይ ተመሥርቶ እየተካሄደ ያለው ፍልሚያ የነገዋን አገራችን ሰንካላ ዕጣ ፋንታ በግልጽ የሚያመላክት በመሆኑ ፈጥኖ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡

 በአገሪቱ በትምህርት ቤቶችም ሆነ በየመስኩ የሚገኙ ወጣቶች ለለውጥም ይሁን ለነውጥ በሚያካሄዱት ስሜታዊ ዕርምጃ ቤተሰቦች ሥጋት ውስጥ ይገባሉ መረጋጋት ያቅታቸዋል። የአገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሀብት ዋስትና ያጣል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ነው የማኅበረሰቡን ዴሞክራሲያዊ አንድነትና የዴሞክራሲ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ከድህነት ተስፈንጥሮ የመውጣት ተነሳሽነት የሚያቀጭጨው። ብሎም ዜጋው በአገሩም ሆነ በመንግሥት ላይ ለመተማመን እንዲቸገር የሚያደርገው፡፡

ለነገሩ በአኅጉር ደረጃም ቢሆን በሰላም ዕጦትና አንድነት መሸርሸር በቀዳሚነት ለመደናቀፍና ለችግር ለመጋለጥ የተዳረገው የትምህርቱ መስክ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህም ዋነኛ ተጎጅዎች ሕፃናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ባለፉት ጊዜያት በኅብረቱ የምክክር መድረኮች ደረጃም የአፍሪካን ዘላቂ ልማትና የአኅጉሪቱን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ለትምህርትና ለሰላም ትኩረት ይሰጥ ሲባል የከረመው:: ኢትዮጵያዊያንም “ሰላም  ነን“ ስንል ቆይተን ፖለቲካው በመደነቃቀፉ  በታወከው ሰላም በቀዳሚነት የትምህርት መስኩ ላይ እንቅፋት ሲገጥም ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

እንዲያውም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያጋጥመውን ይህን የጋራ ችግር ለማስቀረት ከሁለት ዓመት በፊት «ትምህርትን ለሰላም፣ ግጭትን ለመቋቋምና ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከር እንጠቀምበት»  በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ከተማ  የፓን አፍሪካ ሲምፖዚየም መካሄዱን አንዘነጋውም፡፡  

በዚያን ጊዜ በተለያዩ ጥናታዊ ሰነዶች እንደተገለጸው በዓለማችን በአምባገነን መንግሥታትና በወጣቶች ንቅናቄ መካካል እየተከሰቱ ባሉ የእርስ በርስ ጦርነቶችና  ግጭቶች ምክንያት፣ 430 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች ለትምህርት ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ፣ ሌሎች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ  ወጣቶችም ከትምህርት በመፈናቀል እንደሚሰደዱ፣ ወደ ግጭት ገብተው አልያም ከመደበኛ ሕይወታቸው ተስተጓጉለው ያሉትም እንደሚበዙ ተወስቶ ነበር፡፡ ይህን ለማስቀረት በትውልዱ ላይ ሊሠራ የሚገባው ዴሞክራሲያዊነት፣ አንድነትና ሰላም ሊሆን እንደሚገባም መግባባት ላይ ተደርሶበታል፡፡

በኮንፈረንሱ ወቅት ታዲያ የተሻለችና የተረጋጋች አፍሪካዊት አገር የተባለችው ኢትዮጵያ አሁን እንደምን ያለ በዘረኝነትና በጠባብነት ላይ የተመሠረተ የመገፋፋትና የሰላም እጦት ጎበኛት ብሎ መፈተሽ ለትምህርት መስኩ ብቻ ሳይሆን ለአገራዊ ሉዓላዊነትም ወሳኝ ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የአንዱ ክልል ተወላጅ በሌላ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች (ልብ አድርጉ ያውም ለይስሙላም ቢሆን ተቋማቱ የፌዴራል መንግሥት ናቸው ነው የሚባሉት) ሄዶ ለመማር የማይችልበትና ዋስትና የሚያጣበት ሁኔታ መንገሡ፣ የብሔር ተኮሩ ፌዴራሊዝም ቀዳሚ ውድቀት ነው፡፡ ያለጥርጥር!!  

ትምህርት የልማትናዕድገት መሣሪያ እንደሆነ እርግጥ ነው። ልማትና ዕድገት ለማምጣት ደግሞ ሰላማዊ ሁኔታ መኖር አለበት። በትምህርትና ሥልጠና ተኮትኩቶ ያደገ የሙያ ብቃትና ችሎታ ያለው ዜጋ ለመፍጠር የሚታሰበው ሰላምና መረጋጋት በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ ብቻ ነው። ይህን ሰላም ዕውን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በፀሎት ወይም ያለፈውን ድል በመተረክ ብቻ አይደለም፡፡

ይልቁንም እያደገ የመጣውን የሕዝብ ፍላጎት በማርካት፣ ዴሞክራሲያዊነትን በማጠናከር፣ እንዲሁም ከብሔርተኝነትና ከመንደርተኝነት ይልቅ አገራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ማጎልበት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥትና ገዥው ፓርቲን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ታሪካዊ ኃላፊታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕዝቡም በተለይ ወጣቱ በቀናነት ካለፈው ችግሩ መውጣት አለበት፣ ይገባልም፡፡

ሰላምና ልማት፣ ትምህርትና ለውጥ የተሳሰሩ ጉዳዮች ናቸው። ልማትን በማምጣትም ሆነ ትምህርትና ሥልጠናን በማስፋፋት የግጭት መንስዔዎችን ማድረቅ የሚቻለው ግን፣ በተለይ በእኛ አገር ሁኔታ ዴሞክራሲያዊነትን በማጠናከርና አንድነትን በማጎልበት ነው። አልተጤነ እንደሆነ እንጂ «ትምህርትን ለሰላም፣ ግጭትን ለመቋቋምና ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከር እንጠቀምበት» በሚል መሪ ሐሳብ  በአገራችን የተካሄደው የፓን አፍሪካ ሲምፖዚየም ትኩረትም ይኼው ነበር፡፡ በዚህ ረገድ እኛ እንደ አገር ምን ተጠቀምን? የትኛውን ክፍተታችንንስ ሞላንበት? ብሎ መጠየቅ  የፖሊሲ አውጭው ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካል ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡  

በትምህርት አማካይነት የማኅበረሰብን አንድነት ማጠናከር፣ ግጭቶችን ከጦርነት ይልቅ በውይይት መፍታት ወደሚቻልበት አስተሳሰብ የሚያመራና ለሁለንተናዊ ዕድገት መንደርደሪያ ዕውቀት የሚጨበጥ ትውልድ ለመገንባት አገሮች እንዲተጉ አኅጉራዊው ጉባዔ ማሳሳቡ አይዘነጋም፡፡ እዚህም ላይ እንደ አገር የመጣንበትን መንገድ በመፈተሽ  ምን ሠርተናል? ምንስ እየሠራን ነው? ብሎ መጠየቅ በተለይ በችግር ትብትብ ተቀፍድዶ የታያዘው ትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡

ያለፈው እንኳን አልፏል ቢባል ከአሁን ጀምሮ ትውልዱ አገራዊ አንድነቱን የሚገነባባትን፣ ከብሔርና የክልል አጥር ወጥቶ ከአገርም አልፎ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እያለመ እንዲሠራ መጎትጎትና ማንቃት ተገቢ ይሆናል፡፡ ከሁሉ በላይ ያለውን ሥርዓት ቢቃወምና ባይረካበት እንኳን ከነውጥና ከጥፋት በመራቅ በሠለጠነ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመታገል የሚያስብ ትውልድን መገንባት ግድ ይላል፡፡  

በተለይ ወጣቱ በማኅበራዊ ድረ ገጽና መሰል ዓውዶች እርስ በርስ ከመቋሰልና በጥላቻ ፖለቲካ ከመነዳት ወጥቶ፣ በክልል ወሰን ከመናቆርና “እኛና እነሱ” ከሚል አገራዊ አዙሪት ተላቆ እንዲገኝ አሠራሮች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሕግጋትና ፖሊሲዎችም ሊፈተሹ ግድ ይላቸዋል፡፡ 

ለዚህ ደግሞ መንግሥት ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም በተሻለ አቅም ለማዳረስ የሚጥረውን ያህል፣ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን (ጠባብነት ያልነገሠበት)፣ አገራዊ አንድነትን፣ በሠለጠነ መንገድ መነጋጋርን፣ በተለይ ደግሞ በከፍተኛ የትምህርት  ተቋማት የአካዳሚክ ነፃነትንና ተወዳዳሪነትን ማስፈን ይጠበቅበታል፡፡ የምሁራንን ፎረምና ገንቢ ሚና የሚጫወቱበትን መድረኮች መፈጠርም ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አሁንም ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ከሥጋትና ከትርምስ ቀጣናነት ማውጣት አዳጋች እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡

በአጠቃላይ በወጣቱ በተለይም ከየአካባቢው በየትምህርት ተቋማቱ የሚታደመውን ትኩስ ኃይል ለጦርነትና ለግጭት መንስዔ የሚሆኑ ምክንያቶችን፣ በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በመግባባትመፍታት ምክንያታዊነትና ባህል እንዲኖሩ በጋራ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ የሕግ ተቆርቆሪነትና የአገር ፍቅር ስሜት፣ ዴሞክራሲያዊነትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ሊገነባ  የሚችለው  በትምህርት አማካይነት በሚመጣ የአስተሳሰብ ለውጥ መሆኑም ሊዘነጋ አይገባውም። በሁሉም ወገን ቢሆን መፍትሔው እሳትን እያደፈኑ ዋናውን ቃጠሎ በዝምታ መጠበቅ ሳይሆን፣ ችግሩን ከአንጀት ወስዶ በድፍረት በመጋፈጥ መፍትሔ መፈለግ ወሳኝና ወቅታዊ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡

በቅርቡ ትምህርት ሚኒስቴር ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ እንዳቀረበው ሪፖርት ግን በተለመደው መንገድ ወደ ተቋማቱ የፀጥታ ኃይል በማስገባት፣ በአንድ ሰሞን የሰላም ኮንፈረስ ወይም በተለመደው ወደ ትምህርት ግባ፣ አትግባ ቅጣትና ማስፈራራት የነበረውን ሁኔታ ለመመለስ ማሰብ ከውድቀት አለመማር ነው፡፡ እንደ አገር የተደማማሩት የፖለቲካ ብልሽቶችና ከታሪክ የወረስናቸው ውዝግቦች ያደረሱትን ተፅዕኖዎች ያለመገንዘብ ምልክትም ነው፡፡ ስለሆነም ትውልዱን ከተቆለፈበት የልዩነትና የውዝግብ ዋሻ አውጥተን ትምህርት ለአንድነት፣ ለሰላምና መረጋጋት፣ ሰላምና መረጋጋት ለልማትና ዕድገት ብሎም ለጠንካራ አብሮነት፣ አንዱሌላው ውስጥ ያሉ ቅመሞች መሆናቸውን ልናሳይ ይገባል።

    ከአዘጋጁ- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡