Skip to main content
x
መንገዶች ባለሥልጣን 1.8 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ መንገዶችን ለማስገንባት ስምምነት ፈጸመ

መንገዶች ባለሥልጣን 1.8 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ መንገዶችን ለማስገንባት ስምምነት ፈጸመ

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ የሦስት መንገድ ግንባታዎችን ለማካሄድ ከሦስት የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ተዋዋለ፡፡

በበጀት ዓመቱ የውል ስምምነት የተፈጸመባቸው ሦስቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚካሄደው በሶዶ-ድንቄ 86 ኪሎ ሜትር መንገድ፣ በወልድያ ከተማ 5.3 ኪሎ ሜትር መንገድና በድሬዳዋ ከተማ የሚገኘው የመልካ ጀብዱ-ድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ 7.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው መንገዶች ላይ ነው፡፡

ከእነዚህ መንገዶች ውስጥ 86 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ሶዶ-ድንቄ የመንገድ ፕሮጀክትን ለመገንባት ጨረታውን ያሸነፈው ቻይና ሬል ዌይ ሰቨን ግሩፕ የተባለው ኩባንያ ነው፡፡ ከሶዶ እስከ ድንቄ ያለውን ነባሩን 74.5 ኪሎ ሜትር ተከትሎ እንሚገነባ የሚገልጸው የባለሥልጣኑ መረጃ፣ ከ5.5 እስከ 7.5 ሜትር ስፋት ኖሮት በጠጠር መንገድ ደረጃ ተገንብቶ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ መንገድ እንደነበር ጠቅሷል፡፡

አሁን በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ የሚገነባውን የዚህን መንገድ ዲዛይን፣ መንገዱ በሚያልፍባቸው ከተሞች አካባቢ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 19 ሜትር ስፋት ኖሮት እንዲገነባ የሚጠበቅ ነው፡፡ በገጠር አካባቢ በግራና በቀኝ በኩል 1.5 ሜትር ስፋት ያላቸው ትከሻዎችን ጨምሮ በአሥር ሜትር ስፋት እንደሚገነባ ተገልጿል፡፡

ቻይና ሬልዌይ ሰቨን ግሩፕ 86 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ይህንን መንገድ ለመገንባት በጨረታ ያሸነፈበት ዋጋ 1.05 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ እንደ ባለሥልጣኑ መረጃ የዚህን ግንባታ የቁጥጥርና የማማከር ሥራ የሚያከናውነውን ድርጅት ገና አልተሰየመም፡፡ ሆኖም አማካሪውን ለመምረጥ በጨረታ የመረጣ ሒደት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

ለዚህ መንገድ ግንባታ የሚውለው ገንዘብ ከአፍሪካ ልማት በተገኘ ብድርና በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈን ታውቋል፡፡ መንገዱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ተቋራጩ የአራት ዓመት ጊዜ እንደተሰጠው በኮንትራት ስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

መንገዱ የሶዶ፣ የሳውላና የጋሞ ጎፋ ዞኖችንና የጌሬራ፣ የቢሸ፣ የጋሱባ፣ የሰላም በርና የድንቄ መንደሮችን አቋርጦ የሚያልፍ ሲሆን፣ የዚህ መንገድ ቀጣይ ክፍል የሆነው የድንቄ-ሳውላ-ሸፈቴ 76 ኪሎ ሜትር መንገድ ፕሮጀክትም የጨረታ ግምገማ ሒደቱ እንደተጠናቀቀ ታውቋል፡፡ ለድንቄ ሳውላ መንገድ ግንባታ የአፍሪካ ልማት ባንክ የፋይናንስ ስምምነት እየተጠበቀ እንደሚገኝና ገንዘቡ እንደተገኘ የመንገዱ የግንባታ ስምምነት እንደሚፈረም የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ግርማይ ገልጸዋል፡፡

ማክሰኞ ታኅሳስ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. የተፈረመው ሌላኛው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ስምምነት፣ ከአዲስ አበባ 520 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በወረታ በኩል ግንባታው የሚጀመረው፣ በወልድያ ከተማ ውስጥ የሚገነባው የ5.3 ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡ እስከ መለ መውጫ ድረስ እንደሚዘልቅ የተገለጸው ይህ መንገድ በ30 ሜትር ስፋት ይገነባል ተብሏል፡፡ ይህንን መንገድ ለመገንባት ጨረታውን በ504 ሚሊዮን ብር በማሸነፍ ከባለሥልጣኑ ስምምነት የተፈራረሙት ዘልዑል ዮሐንስና ባኮራ ትሬዲንግ የተባሉ አገር በቀል ተቋራጮች ናቸው፡፡ የመንገዱን የቁጥጥርና የማማከር ሥራ የሚያከናውነው ፒዩር ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ የተባለ አገር በቀል አማካሪ ድርጅት ነው፡፡ ለመንገዱ ግንባታ የሚውለው ገንዘብ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ሲሆን፣ መንገዱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የተሰጠው የሁለት ዓመት ጊዜ እንደሆነም ታውቋል፡፡

ሌላው ስምምነት የተፈረመበት የመንገድ ፕሮጀክት፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኘው የመልካጀብዱ ድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ የ7.5 ኪሎ ሜትር መንገድ ሲሆን፣ የ50 ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ የሚገነባ ነው፡፡  

ይህንን የመንገድ ለመገንባት ጨረታውን በ298 ሚሊዮን ብር በማሸነፍ ከባለሥልጣኑ ጋር ስምምነት የተፈረመው ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የተባለው ተቋራጭ ነው፡፡ የመንገዱን የቁጥጥርና የማማከር ሥራ የሚያከናውነውን ድርጅት ለመምረጥ በጨረታ ሒደት ላይ እንደሚገኝ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

ለመንገዱ ግንባታ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ መንግሥት የሚሸፈን ሲሆን፣ መንገዱን ለማጠናቀቅም ለተቋራጩ የዘጠኝ ወራት የጊዜ ገደብ ተሰጥቶታል፡፡ መንገዱ ሲጠናቀቅ 21.9 ሜትር የመኪና መሄጃ፣ 15.1 የመንገድ አካፋይ እንዲሁም በግራና በቀኝ ሦስት ሜትር የእግረኛ መሄጃ፣ ሁለት ሜትር የብስክሌት መንገድና 1.5 አረንጓዴ ሥፍራ ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም አምስት ድልድዮች፣ የፋብሪካዎችና የመፋሰሻ ቱቦዎች ግንባታን እንደሚያካትት ታውቋል፡፡

የኮንትራት ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አርዓያ ግርማይ ሲሆኑ፣ በተቋራጮች በኩል ያም ዋንግቲንግ የቻይና ሬል ዌይ ሰቨንስ ግሩፕ፣ የዘልዑል ዮሐንስ ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘልዑል ዮሐንስ እንዲሁም የባኮራ ትሬዲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓብይ አጥናፉ ናቸው፡፡

የግንባታ ሥራዎቹን ከተረከቡት ተቋራጮች መካከል ሁለቱ ከዚህ ቀደም ከባለሥልጣኑ ጋር በመዋዋል የተለያዩ የመንገድ ግንባታዎች ላይ የተሳተፉ ሲሆን፣ የቻይናው ሬል ዌይ ሰቨንስ  በመንገድ ሥራ ለመሳተፍ ከባለሥልጣኑ ጋር ሲዋዋል ግን የመጀመርያው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ባለሥልጣኑ ለ2010 በጀት ዓመት 45 ቢሊዮን ብር በጀት ከመንግሥት የተመደበለት ሲሆን፣ በዓመቱ የ69 አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለመፈራረም ዕቅድ ይዟል፡፡ በሦስቱ የመንገድ ግንባታ ስምምነት ወቅት አቶ አርዓያ እንደገለጹት፣ እስካሁን የ19 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቁ 19 ፕሮጀክቶች ተፈርመዋል፡፡

የመንገዶቹ ግንባታ በሚጠናቀቅበት ወቅት ከዚህ በፊት በየአካባቢው የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ፣ ነዋሪዎች በቀላሉ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱበት አመቺ ሁኔታ ይፈጥራሉ ያለው ባለሥልጣኑ፣ በኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ባለሀብቶችም ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ ማውጣት እንዲችሉ፣ አዳዲስ ባለሀብቶችም መንገዶቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች በቀላሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያመች ዕድል እንደሚከፍቱ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአካባቢው የሥራ ዕድል እንዲፈጠር በማስቻል፣ በአካባቢው የሚገኙ ትንንሽ መንደሮች በከተማ ደረጃ እንዲስፋፉና እንዲያድጉ ከማድረግ እንዲሁም የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት በሰፊው እንዲስፋፋ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብሎ ይታመናል፡፡