Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ ያስጠሩታል

ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ ያስጠሩታል

 • ሰውዬ ምን እየሠራህ ነው?
 • ምን አጠፋሁ ክቡር ማኒስትር?
 • ትናንትና የሰጠሁን ሥራ ምን አደረግከው?
 • እየሠራሁት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ባለፈው ሥራ ያልኩህስ ሪፖርት?
 • አልደረስዎትም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼ ነው ሪፖርቱ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እየቀለድክ መሆን አለበት?
 • ለምን እቀልዳለሁ ክቡር ሚኒስትር?
 • ካልቀለድክማ ይኼን ሪፖርት ብለህ ማቅረብ አልነበረብህም፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ከዚህ በፊት የምታቀርባቸውን ሪፖርቶች አውቃቸዋለሁ፡፡
 • ታዲያ ይኼኛው ምን ሆነ?
 • ምን ተገኝቶ ነው እንደዚህ ዓይነት የወረደ ሪፖርት የምታቀርበው?
 • ሪፖርቱን አልወደዱትም ማለት ነው?
 • ይኼን ሪፖርት ብለህ ስታቀርብ ራስህ አትፍርም?
 • ምን ያሳፍራል?
 • ይኼ አሁን ለፓርላማ የሚቀርብ ሪፖርት ነው?
 • ሌሎች ለፓርላማ የሚያቀርቡትን ሪፖርት አናውቅም እንዴ?
 • ምን እያልክ ነው?
 • የፓርላማ አባላት እጃቸው እስኪቀላ ያጨበጨቡለት ሪፖርት ውሸት ሆኖ ሲገኝ እናውቃለን አይደል እንዴ?
 • ስለእነሱ ሪፖርት ማን ጠየቀህ?
 • አይ ያው ነገሩን ስላነሱት ነው፡፡
 • ትኩረት ሰጥተህ እንድትሠራው አይደል እንዴ የነገርኩህ?
 • ለነገሩ ይኼኛው ትንሽ ወረድ ያለ እንደሆነ ይገባኛል፡፡
 • ስለዚህ ሆን ብለህ ነዋ የሠራኸው?
 • እ…
 • ለመሆኑ የትምህርት ደረጃህ ምንድው?
 • ሁለተኛ ዲግሪዬን ይዣለሁ፡፡
 • ለዚያውም በማዕረግ ነው የተመረቅኩት ብለኸኛል?
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • መመረቂያ ጽሑፍህ ራሱ ስንቶችን ያስተምራል ሲባል አልነበር እንዴ?
 • እውነት ነው፡፡
 • ከዚህ በፊት በሠራሃቸው ሪፖርቶች እኔ ራሴ ሹመት አግኝቻለሁ አይደል እንዴ?
 • አልተሳሳቱም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ይኼን ምን ብዬ ነው ሪፖርት ብዬ የምቀበለው?
 • አይ ክቡር ሚኒስትር እኔም እኮ ስለሚያምረኝ ነው?
 • ምንድነው የሚያምርህ?
 • ሥልጣን፣ የደረጃ ዕድገትና ሹመት፡፡
 • የምር እነዚህን ነገሮች ትፈልጋቸዋለህ?
 • በሚገባ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ሥራህን ለምን በአግባቡ አትሠራም?
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስገለፍጥሃል?
 • ሹመት ለማግኘት ሥራዬን በአግባቡ መሥራት አይጠበቅብኝም፡፡
 • እንዴት?
 • የመንግሥታችንን ባህል ስናውቀው ብቃት አያሾምም፡፡
 • ታዲያ ምንድነው የሚያሾመው?
 • ለፓርቲው ታማኝ መሆን፡፡
 • ሌላስ?
 • ሌሎች በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡
 • ምን እያልክ ነው ታዲያ?
 • እኔ አሁን ሹመት አምሮኛል፡፡
 • ምን ልታደርግ ነው ታዲያ?
 • አንድ ነገር ብቻ፡፡
 • እኮ ምን?
 • መስነፍ!

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝባዊ ስብሰባ እየመሩ ነው፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ለሁለት ሰዓታት ያለማቋረጥ ሲያወሩ አንድ ተሳታፊ በንዴት እጁን አወጣ]

 • አንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • አልጨረስኩም እኮ?
 • ከዚህ በላይ እርስዎን መስማት አንችልም፡፡
 • ምንድነው?
 • የእርስዎ ዲስኩር አሁን መቆም አለበት፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ነስር ነስር አለን እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ቆይ ቆይ ቆይ ቆይ በአገር ጉዳይ እየመከርን አይደል እንዴ?
 • እየመከርን ሳይሆን እየመከሩን ነው እርስዎ፡፡
 • ዋናው ዓላማ መመካከር አይደል እንዴ?
 • እንደዚያ ከሆነ መመካከር ነው ያለብን፡፡
 • እኮ እንመካከራ?
 • ስለዚህ እኔ እርስዎን ልምከርዎት፡፡
 • አንተን የመሰለ አንድ ፍሬ ልጅ ምንድነው የምትመክረኝ?
 • ይኼ ችግራችሁ ነው እኮ ብዙ ነገር እየፈጠረ ያለው፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ከቅድም ጀምሮ ሕዝቡ ላይ ጣትዎን እየቀሰሩ ነው፡፡
 • ታዲያ ችግሩ በሕዝቡ ነዋ የመጣው፡፡
 • አይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • አንድ ጣትዎን ሕዝብ ላይ ሲቀስሩ ሦስቱ ራስዎት ላይ ነው የሚጠቁሙት፡፡
 • እ…
 • ስለዚህ ሕዝቡን ፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት፣ ኪራይ ሰብሳቢ እያላችሁ አታደንቁሩት፡፡
 • እንዴት?
 • በእርግጥ ኪራይ ሰብሳቢው ማን ነው?
 • እ…
 • ገበሬው ነው ወይስ እርስዎ?
 • ብንከባበር ጥሩ ነው፡፡
 • ይኼ የመከባበሪያ መድረክ ሳይሆን የመመካከሪያ መድረክ ነው፡፡
 • ስለዚህ ከአጀንዳው ወጥተህ እንድትናገር አልፈቅድልህም፡፡
 • እኔ እርስዎ የሚፈልጉትን ነገር ብቻ አላወራልዎትም፡፡
 • እ…
 • የሚሰማኝንና እውነቱን ነው የምናገረው፡፡
 • እውነቱ ምንድነው?
 • እውነቱማ አገሪቱ ላለችበት ችግር ተጠያቂው አመራሩ መሆኑ ነው፡፡
 • ምን?
 • ክቡር ሚኒስትር ያጠፋ መሪ የሚሾምበት ብቸኛ አገር የት እንደሆነ ያውቃሉ?
 • አላውቅም፡፡
 • ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡
 • እኔ ጠፋሁ?
 • ለነገሩ አሁን የምንታወቅባቸው ነገሮች እየበዙ ነው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • በፊት ቀይ ቀበሮና ዋልያ የመሳሰሉ አራዊት የሚገኙባት ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ነበረች፡፡
 • አሁንስ?
 • አሁንማ መቶ ፐርሰንት ምርጫ ማሸነፍ የሚቻልባት አገር በመሆን እየታወቀች ነው፡፡
 • አንተ ፀረ ሰላም መሆንህን አውቄያለሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼ ጣት መቀሰር መቆም አለበት፡፡
 • ታዲያ መንግሥትን ስትተች ምን ልበልህ?
 • እናንተ እኮ ለሕዝቡ ከእኛ በላይ የሚያውቅልህ የለም እያላችሁ ነው?
 • ድሮስ ማን ያውቅለታል?
 • ለዚህ ነው አገሪቷ እንደዚህ እየታመሰች ያለችው?
 • ፀረ ሕዝብ ኃይሎች ናቸዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ወደ ሌላ ጣትዎን አይቀስሩ?
 • ታዲያ መንግሥት ሲተች ቁጭ ብዬ ላዳምጥ?
 • ዋናው ችግራችሁ እሱ ነው፡፡
 • ምንድን?
 • አለማዳመጥ!

[ክቡር ሚኒስትሩ የፓርቲ ስብሰባ ተጠርተው እየተወቀሱ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር በጣም አደገኛ አካሄድ እየሄዱ ነው፡፡
 • ምን ማለት ነው አደገኛ አካሄድ?
 • እኛ በዝግ የምናደርገውን ስብሰባ እየወጡ ለሚዲያ የሚሰጡ እርስዎ መሆኑን ደርሰንበታል፡፡
 • ማን? እኔ?
 • አዎን እርስዎ፡፡
 • እኔ ከሚዲያ ጋር?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በጣም ተሳስታችኋል፡፡
 • እንዴት?
 • እንዲያውም ከሁላችሁም ይልቅ ከሚዲያ ጋር ፀበኛና ጦረኛ እኔ ነኝ፡፡
 • መረጃውና ማስረጃው የሚለው ግን ሌላ ነው፡፡
 • ምን እያላችሁ ነው?
 • እዚህ የምንነጋገረውን ነገር እየወጡ የሚያወሩት እርስዎ ነዎት፡፡
 • እኔ ይኼን አልቀበልም፡፡
 • ለማንኛውም በእርስዎ ምክንያት አገሪቷ እየታመሰች ናት፡፡
 • በምንድነው እኔ አገሪቷን የማምሰው?
 • ገና ስብሰባ ስንጀምር ሕዝቡ በአጀንዳችን ላይ ሠልፍ ይወጣል፡፡
 • ታዲያ እኔ ምን ላድርግ?
 • ይባስ ብሎ የስብሰባው አጀንዳ ስብሰባው ሳይጠናቀቅ በተለያዩ ድረ ገጾችና ሶሻል ሚዲያ ላይ ይወጣል፡፡
 • እኔ ስለምትሉት ነገር የማውቀው ነገር የለም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እንደዚህ አይበሉ፡፡
 • የምን ድረ ገጽ ነው የምታወሩት?
 • ክቡር ሚኒስትር በእርስዎ ምክንያት ነው ስብሰባው ውስጥ ስልክ እንዳይገባ የተደረገው፡፡
 • እንደዚያ የወሰናችሁት በእኔ ምክንያት መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡
 • በወቅቱ ምክንያቱን መግለጽ አላስፈለገም ነበር፡፡
 • ምን አድርግ ነው ታዲያ የምትሉኝ?
 • አሁን ይኼ ጉዳይ የፓርቲው ህልውና ላይ አደጋ እየጋረጠ ነው፡፡
 • ወይ ጣጣ?
 • በእርስዎ ላይ ወደፊት ዕርምጃ መውሰዳችን አይቀርም፡፡
 • በእኔ ላይማ ማንም ዕርምጃ መወሰድ የለበትም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የሚያደርጉት ነገር ከፓርቲያችን ባህል ውጪ በመሆኑ ዕርምጃ ይወሰድብዎታል፡፡
 • እኔ በዚህ አልስማማም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ከፓርቲው ባህል እያፈነገጡ ነው፡፡
 • እኔ ፓርቲዬን የምወድና አንገቴን የምሰጥ ነኝ፡፡
 • ለማንኛውም አሁን ራስዎን እንዲያሞካሹ አይደለም የተጠሩት፡፡
 • ምን ላድርግ ታዲያ?
 • የቀጣይ ስብሰባችን ቦታ ይቀየራል፡፡
 • የት ሊሆን?
 • ለራሳችን ደኅንነት ሲባል ኤሌክትሮኒክስ የማይገባበት ቦታ ስብሰባችን ይካሄዳል፡፡
 • የት ሊደረግ?
 • እንትን እየወሰድን ነው የምናደርገው?
 • ምን?
 • ስቲም ባዝ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ የውጭ ኢንቨስተሮች ይመጣሉ]

 • በጣም በአጭር ቆይታ ስለተገናኘን እናመሰግናለን፡፡
 • ምን ችግር አለው?
 • ያው የአንድ አገር ሚኒስትር ማግኘት ከባድ ነው ብለን ነው፡፡
 • ለእናንተ በራችን ሁሌም ክፍት ነው፡፡
 • እዚህ አገር ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ነው የመጣነው፡፡
 • እኔም በጣም ላበረታታችሁ እፈልጋለሁ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ላለፉት አሥርት ዓመታት በላይ አገሪቷ በሁለት አኃዝ እያደገች ነው፡፡
 • እሱንማ ሰምተናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዕድገታችን ዓለም ሁሉ መስክሮልናል፡፡
 • እኛም ለዕድገቱ ተጨማሪ አስተዋጽኦ እናደርጋለን ብለን እናስባለን፡፡
 • በዚያ ላይ አገሪቱ ከሙስና የፀዳ ሥርዓት ያላት ናት፡፡
 • እ…
 • ስለዚህ አካውንተቢሊቲና ኢንተግሪቲ ያለበት ገበያ ውስጥ ነው የምትገቡት፡፡
 • እንግዲህ ይኼን ወደፊት የምናየው ነው የሚሆነው፡፡
 • አሁን ምን ትፈልጋላችሁ?
 • ለፕሮጀክታችን ሰፊ መሬት እንፈልጋለን፡፡
 • መሬት እንኳን እንዲህ በቀላሉ አይገኝም፡፡
 • ለምን እንደምንፈልገው በፕሮፖዛላችን ተገልጿል እኮ?
 • ለመሬት ፕሮፖዛል ብቻ አይበቃም፡፡
 • ሌላ ምን ያስፈልጋል?
 • ኮሚሽን፡፡
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • እኛ እኮ ኢንቨስት ልናደርግ ነው የመጣነው?
 • ለእኔ እናንተ ከኢንቨስተር በላይ ናችሁ፡፡
 • ሌላ ምን?
 • ለገና ስጦታ የሚሰጠው ነዋ፡፡
 • አልገባንም፡፡
 • የገና አባት!