Skip to main content
x
የተማሪዎችን ምገባ ብሔራዊ ለማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር ከ289 ሚሊዮን ብር በላይ መደበ

የተማሪዎችን ምገባ ብሔራዊ ለማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር ከ289 ሚሊዮን ብር በላይ መደበ

በግልና በሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ በተወሰኑ አካባቢዎች እየተከናወነ የሚገኘውን የተማሪዎች ምገባ ብሔራዊ ለማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር ከ289 ሚሊዮን 452 ሺሕ ብር በላይ መመደቡን አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር) አገር አቀፍ የትምህርት ምገባ ፕሮግራምን አስመልክተው ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ በጥር 2010 ዓ.ም. ይጀመራል በተባለው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት በ305 ትምህርት ቤቶች ይማሩ የነበሩ ከኦሮሚያ 65,228 እንዲሁም ከሶማሌ 44,350 በአጠቃላይ ከ100 ሺሕ በላይ ተማሪዎች መፈናቀላቸውን ያስታወሱት ዶ/ር ጥላዬ፣ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በተለይም ከእነዚህ ሥፍራዎች ለተፈናቀሉና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ለሚኖሩት ተማሪዎች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

ምገባው በድርቅ ከተጎዱ አካባቢዎች በተመረጡ 228 ወረዳዎች ላይ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥና ከአዲስ አበባ ውጭ የትምህርት ሽፋኑ ዝቅተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች የሚከናወን ሲሆን፣ ይህም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይፈናቀሉ፣ ወላጆች ላይ የሚደርሰውንም ጫና ለመቀነስ ያግዛል ተብሏል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ድርቅ በስፋት በተንሰራፋባቸው አካባቢዎች በተቋቋሙት የቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ 4.9 ሚሊዮን ተማሪዎች 798 ሚሊዮን ብር ወጪ የምገባ ፕሮግራም ማከናወኑን ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ወር ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ በዚህኛው ፕሮግራም በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚካተቱ ታውቋል፡፡

የሚኒስቴሩ የትምህርት ቤት ማሻሻያ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ያስቡ ብርቅነህ ከወር በፊት በነበረ መድረክ እንደገለጹት፣ በደቡብ፣ በሶማሌ፣ በአፋርና በሐረሪ ክልሎች በሚገኙና ድርቁ ክፉኛ በጎዳቸው ልዩ ልዩ አካባቢዎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በተወሰኑ ሥፍራዎች ላሉት የቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተከናውኗል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት በድርቅ ለተጎዱት ወገኖች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ከማቅረብ በተጨማሪ ትምህርትን ማዕከል ያደረገ የምግባ ፕሮግራም እንዳልተካሄደ፣ ይህን መሰል አዲስ ፕሮግራም በመካሄዱም በተጠቀሱት ሥፍራዎች የሚገኙት የቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የተከሰተው ድርቅ ሳያደናቅፋቸው ትምህርታቸውን ለመከታተል እንደቻሉም ገልጸው ነበር፡፡

የትምህርት ቤት የምገባ ፕሮግራም በሁሉም አካባቢ በመደበኛነት ለማከናወን እንዲቻል ሚኒስቴሩ ‹‹ብሔራዊ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ስትራቴጂ›› በማርቀቅ ላይ እንደሆነና፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያዘጋጀው የትምህርት ቤት የጤናና ኒውትሬሽን ፕሮግራም ደግሞ ትግራይ ውስጥ በሙከራ ደረጃ በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ይታወቃል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር በጥር 2010 ዓ.ም. ይጀመራል የተባለው የምገባ ፕሮግራም አዲስ አበባን ባያካትትም፣ በአዲስ አበባ ብቻ በመንግሥት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከሚገኙ  ተማሪዎች 90 በመቶ ያህሉ የምግብ ዕርዳታ ፈላጊ መሆናው ከዚህ ቀደም በተደረገ ዳሰሳ ታውቋል፡፡

ይህ የዳሰሳ ጥናት ከመደረጉ አስቀድሞ በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች፣ በተለያዩ ተቋማት የምግብና የዩኒፎርም፣ የትምህርት መርጃና ሌሎችም ድጋፎች ሲሰጡ የነበረ ቢሆንም፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉንም ችግረኛ ተማሪዎችም ለመድረስ አልተቻለም፡፡

ሆኖም የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ግለሰቦችና መምህራን የሚያደርጉትን እገዛ ለመደገፍ የአዲስ አበባትምህርት፣ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮዎችና በቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ የበላይ ጠባቂነት የሚንቀሳቀሰው የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማኅበር 2007 .. ጀምሮ በመንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ የሚማሩና በጣም ችግረኛ የሆኑ ከ20 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን በመመገብ ላይ ይገኛል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች፣ መምህራንና የትምህርት ቤት ክበባት ደግሞ 10 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ይመግባሉ፡፡

በአዲስ አበባ በመንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከሚማሩ ተማሪዎች፣ በወላጆች ወይም በአሳዳጊዎች አቅም ማነስ ምክንያት ምግብ ማግኘትና ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ ተማሪዎችን፣ 2007 .. ጀምሮ የሚመግበውና በቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ የሚመራው የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማኅበር፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት በሰኔ 2009 ዓ.ም. ባደረጉት ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ እንዳስታወቁት፣ ማኅበሩ በአዲስ አበባ በሚገኙ 207 የመንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩና ከዝቅተኛ ቤተሰብ የመጡ 20,135 ተማሪዎችን ቁርስና ምሳ እየመገበ ነው፡፡ ዓመታዊ ወጪውም 60 ሚሊዮን ብር እንደሆነ በወቅቱ አሳውቆ ነበር፡፡

የፕሮግራሙን ቀጣይነት ለማረጋገጥና ተጨማሪ ችግረኛ ተማሪዎችንም የምገባው ተጠቃሚ ለማድረግ ከተደረገው ገቢ ማሰባሰቢያ ጎን ለጎን መንግሥት በጀት እንዲይዝ እንቅስቃሴ መጀመሩም በወቅቱ ተነግሯል፡፡