Skip to main content
x
ጎመጁ ኦይል ተንቀሳቃሽ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች አስገባ

ጎመጁ ኦይል ተንቀሳቃሽ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች አስገባ

  • በ300 ሚሊዮን ብር 16 ማደያዎች ገነባ

የነዳጅ ማከፋፈል ኢንዱስትሪን በቅርቡ የተቀላቀለው ጎመጁ ኦይል የተሰኘው አገር በቀል ኩባንያ፣ አገሪቱ ውስጥ ያለውን የነዳጅ ማደያ እጥረት ለመቅረፍ እንደሚረዱ የታመነባቸውን ስድስት ተንቀሳቃሽ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች ገዝቶ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አገር ውስጥ አስገባ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በመዲናዋ አዲስ አበባ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ማደያ እጥረት እንዳለ ይታወቃል፡፡ የጎመጁ ኦይል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ የሺዋስ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኩባንያቸው በአዲስ አበባ የነዳጅ ማደያዎች ለመገንባት ፍላጎት ቢኖረውም መሬት ለማግኘት ተቸግሯል፡፡ ‹‹እኛ ብቻ ሳንሆን ሌሎች ኩባንያዎችና ግለሰቦች ነዳጅ ማደያ ለመገንባት መሬት አያገኙም፡፡ በዚህም ምክንያት አዲስ አበባ ውስጥ የነዳጅ ማደያ እጥረት ይስተዋላል፤›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ጎመጁ ኦይል ችግሩን በመመልከት ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከአውሮፓ ስድስት ተንቀሳቃሽ የነዳጅ ማደያዎች ገዝቶ አገር ውስጥ ማስገባቱን ተናግረዋል፡፡

እያንዳንዱ ተንቀሳቃሽ ማደያ 44,000 ሊትር ነዳጅ ማጠራቀሚያ ጋን፣ ፓምፕ፣ የሞተር ዘይትና ቅባቶች መሸጫ ሱቅና ቢሮ አለው፡፡ ተንቀሳቃሽ ማደያዎቹ በአዲስ አበባና በአዳማ ከተማ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ባለባቸው ቦታዎች እንደሚቀመጡ አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡

የጎመጁ ኦይል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይግዛው መኮንን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ተንቀሳቃሽ ማደያዎቹ ክፍት በሆኑ ቦታዎች ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ቦታው ለልማት ሲፈለግ ይነሳሉ ብለዋል፡፡ ተንቀሳቃሽ ማደያዎችን ተረክበው የሚያስተዳድሩት በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ ወጣቶች እንደሚሆኑና ጎመጁ ኦይል ለማደያዎቹ ነዳጅ፣ ዘይትና ቅባቶች እንደሚያቀርብ አቶ ይግዛው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአገራችን ያለውን የወጣቶች ሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ኩባንያችን የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይፈልጋል፤›› ያሉት አቶ ይግዛው፣ ተንቀሳቃሽ የነዳጅ ማደያዎቹ የሚተከሉባቸውን ቦታዎችና የተደራጁ ወጣቶች ማደያዎቹን ተረክበው በሚሠሩበት ሁኔታ ላይ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ተንቀሳቃሽ የነዳጅ ማደያዎቹ ከፍተኛ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች በተገኙበት በቅርቡ እንደሚመረቁ ተገልጿል፡፡

ጎመጁ ኦይል ማደያዎቹ የሚሰጡት አገልግሎት እየታየ ወደፊት ተጨማሪ ተንቀሳቃሽ የነዳጅ ማደያዎች ተገዝተው በአዲስ አበባና የነዳጅ ማደያ እጥረት ባለባቸው የክልል ከተሞች እንደሚያስገባ የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ ወደፊት ማደያዎቹ አገር ውስጥ ሊመረቱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ 710,000 የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ 70 በመቶ አዲስ አበባ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በመዲናዋ ለሚገኙት 400,000 ያህል ተሽከርካሪዎች አገልግሎት የሚሰጡት 100 የነዳጅ ማደያዎች ብቻ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ያሉት የነዳጅ ማደያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ያምናል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት 100 ማደያዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ዕድሜ የተጫናቸውና አነስተኛ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ጋን ያላቸው ናቸው፡፡ ‹‹አንድ የነዳጅ ማደያ በአማካይ 4,000 ተሽከርካሪዎች ያስተናግዳል፡፡ ይህ በጣም ብዙ በመሆኑ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጫና ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም አዳዲስና ዘመናዊ የነዳጅ ማደያዎች ያስፈልጉናል፤›› ብለዋል አቶ ታደሰ፡፡

በአገሪቱ በአጠቃላይ 800 የነዳጅ ማደያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ 100 ሚሊዮን ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ አነስተኛ መሆናቸውን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ 40 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ጎረቤት ኬንያ ከ2,000 በላይ የነዳጅ ማደያዎች እንዳሏት ተገልጿል፡፡

ጎመጁ ኦይል በአቶ ቴዎድሮስ የሺዋስና ባለቤታቸው ወ/ሮ ገነት ገብረ እግዚአብሔር በታኅሳስ 2008 ዓ.ም. በ53 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተመሥርቶ፣ 24 የነዳጅ ማደያዎች በ700 ሚሊዮን ብር ወጪ ገንብቶ ሥራውን ጀምሯል፡፡ በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኘው ጎመጁ ኦይል ካፒታሉን ወደ 100 ሚሊዮን ብር ያሳደገ ሲሆን፣ ተጨማሪ 16 የነዳጅ ማደያዎችን በ300 ሚሊዮን ብር ወጪ ገንብቷል፡፡

የመጀመርያዎቹን ሁለት ዘመናዊ ማደያዎች በአዲስ አበባ፣ በቱሉ ዲምቱና በቢሾፍቱ ከተማ በሚያዝያ 2009 ዓ.ም. ያስመረቀው ጎመጁ ኦይል በባህር ዳር፣ ሞጆ፣ ሐዋሳ፣ አሶሳ፣ ሰመራና ወላይታ ሶዶ አዳዲስና ዘመናዊ ማደያዎችን የገነባ ሲሆን፣ በደወሌና ኩያ (መቐሌ) ግንባታ ጀምሯል፡፡ በቀጣይም ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴና የትራፊክ ፍሰት ባለባቸውና የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሚገነቡባቸው ከተሞች ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡ የጎመጁ ኦይል የነዳጅ ማደያዎች 40 የደረሱ ሲሆን፣ 60 በመቶ በኩባንያው በራሱ ባለቤትነት ሲይዙ 40 በመቶ ደግሞ በግለሰቦች የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡

ጎመጁ ኦይል ተቀማጭነቱ በጣሊያን አገር የሆነ ፔትሮናስ ሉብሪካንትስ ከተሰኘ ታዋቂ ኩባንያ ጋር ስምምነት በመፈራረም፣ የፔትሮናስ የሞተር ዘይቶችና ቅባቶች ከጣሊያን አገር በማስመጣት ኢዮጵያ ውስጥ ማከፋፈል ጀምሯል፡፡ የውክልና ስምምነቱን መፈረም አስመልክቶ የፔትሮናስ ሉብሪካንትስ ኃላፊዎች በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት መግለጫ እንደሚሰጡ ታውቋል፡፡

ጎመጁ ኦይል የአንበሳ የከተማ አውቶብስ ድርጅት ያወጣውን ጨረታ በማሸነፍ ለኩባንያው ለሦስት ዓመት ነዳጅ፣ የሞተር ዘይትና ቅባቶች ለማቅረብ የሚያስችለውን ማደያ በአንበሳ አውቶብስ ቅጥር ግቢ በመገንባት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል ኩባንያው የአቪዬሽን ነዳጅ ገበያን ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ እንደሆነ አቶ ቴዎድሮስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የአውሮፕላን ነዳጅ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት፣ ሐዋሳና ሰመራ ኤርፖርቶች ለማቅርብ የሚያስችል የሥራ ዕቅድ አዘጋጅተው ለኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ማስገባታቸውን አቶ ቴዎድሮስ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ጎመጁ ኦይል የቡታጋዝ ምርት ለማከፋፈል በዝግጅት ላይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ኩባንያው ቢሾፍቱ በሚገኘው ማደያው የቡታጋዝ ማጠራቀሚያ ጣቢያ የገነባ ሲሆን፣ የቡታጋዝ ማከፋፈል የሚሠራ ጎመጁ ጋዝ የሚባል ክፍል በማዋቀር ላይ እንደሚገኝ አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ጋዙን ከሱዳንና ከኢራን የማስመጣት ዕቅድ እንዳለው የገለጹት አቶ ይግዛው፣ ለአገሪቱ አዲስ የሆነ የፕላስቲክ ሲሊንደር እንደሚያስገባ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሲሊንደሩ በውስጡ የተሞላውን ጋዝ መጠን የሚያሳይ በመሆኑ ኅብረተሰቡን ከመጭበርበር ይታደገዋል፤›› ብለዋል፡፡

ጎመጁ ኦይል እስካሁን በከፈታቸው 40 ማደያዎች ለ1,000 ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን፣ በቀጣይ አምስት ዓመታት የማደያዎቹን ቁጥር 150 ለማድረስ ማቀዱን አስታውቋል፡፡