Skip to main content
x
የተጨማሪ እሴት ታክስ አከፋፈል አዲስ ሥርዓት ተግባራዊ ሊሆን ነው

የተጨማሪ እሴት ታክስ አከፋፈል አዲስ ሥርዓት ተግባራዊ ሊሆን ነው

ከሁለት ሳምንት በፊት በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በወጣ ሰርኩላር፣  የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋዮች ምዝገባ አዲስ ሥርዓት ከየካቲት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገባ ታወቀ፡፡

በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር በሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) አማካይነት ተፈርሞ በወጣው በዚህ ሰርኩላር መሠረት፣ ከዚህ ቀደም ለተጨማሪ እሴት ታክስ ለመመዝገብ ግዴታ የተጣለባቸው የንግድ ተቋማት ዓመታዊ የግብይት መጠን ላይ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡

በዚህም መሠረት ከየካቲት 1 ቀን 2010 ጀምሮ ዓመታዊ የግብይት መጠናቸው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ብቻ የሆኑ ታክስ ከፋዮች ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲሰበስቡ የሚደረግ ሲሆን፣ አሁን ባለው አሠራር ከ500 ሺሕ ብር በላይ ዓመታዊ ገቢ ያላቸውም ጭምር የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲሰበስቡ ይገደዳሉ፡፡

ሰርኩላሩ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ግሽበት በመከሰቱና የብር የመግዛት አቅም እየቀነሰ በመምጣቱ ምክንያት፣ በታክስ ሥርዓቱ እንዲታቀፉ የማይፈልጉ በርካታ ቁጥር ያላቸው በአነስተኛ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ በታክስ ሥርዓቱ ውስጥ የሚካተቱበት ሁኔታ መፈጠሩን ይጠቅሳል፡፡ ሰርኩላሩ በተጨማሪ እሴት ታክስና በተርን ኦቨር ታክስ ሕጎች መካከል አለመጣጣም የፈጠረው ችግር ለማሻሻያው ምክንያት መሆኑን ይገልጻል፡፡

ይኼ ሰርኩላር በዋናነት ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተላከ ሲሆን፣ ይኼን ተከትሎም ባለሥልጣኑ ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ዝግጅት እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በዚህም መሠረት አዲሱ አሠራር ከየካቲት መጀመርያ ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል ሲሉ የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በአዲሱ አሠራር መሠረት ባለሥልጣኑ ከ500 ሺሕ ብር ዓመታዊ ገቢ ጣሪያ በታች የሆኑ ግብር ከፋዮች፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት እንዲሰረዙ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡

ከወራት በፊት ከቀን ገቢ ግምት በተያያዘ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ቅሬታ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡