Skip to main content
x

ሚዛናዊ ተራማጅነት

በጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

የተሻለ፣ ከዛሬው ይልቅ መልካም፣ ያሁኑን ያህል ያልከፋ፣ ክፋቱና መጥፎነቱ የቀነሰ፣ በጎ ጎኑና መልካምነቱ የላቀ  ማኅበረሰብ እንፈልጋለን፡፡ ነገሮችና ሁኔታዎች በጐና አዎንታዊ በሆነ መልክ እንዲለወጡ እንፈልጋለን፡፡ የተሻለ ቀን፣ የተሻለ ማኅበረሰብና አገር፣ መልካም የሆነ ለውጥ እንዲመጣ መፈለግ ለወጣቶችና የዛሬው ቀንና ሁኔታ ላልተመቸው ሁሉ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የተጐሳቆለ፣ ሆድ የባሰውና የከፋው ለውጥ ቢፈልግ አይገርምም፡፡ ዛሬ ስትጠነሰስ ያልነበረ፣ ትናንትናና ከትናንትም በፊት ከዘመን ጋር አብሮ ተቦክቶ፣ ተላምዶ ዛሬን ያልደረሰው፣ እጅግም ያልለመደው ወጣት መሻሻልንና ለውጥን ቢፈልግ አይገርምም። ይህ እውነት ዛሬም በአገራችን ይታያል። ለውጥንና መሻሻልን የሚፈልግ ወጣት ተነስቷል፡፡ ታዲያ የዛሬው ወጣት በሚፈልጋት አገርና የትናንት ወጣቶች፣ የዛሬው አዛውንቶች በደነገጉዋት አገር መሀል ያለው ልዩነት እያጋጫቸው፣ ከባድ ውጥረትና ቀውስ ውስጥ ያለን ማኅበረሰብ ሆነናል፡፡

ታዲያ አገርና ማኅበረሰብን ለማሻሻል፣ በበጐ ለመለወጥ የሚነሳ ሁሉ አፍታቶና አብራርቶ፣ ግልጽ አድርጐ ባያስቀምጠውምመልካምወይምየተሻለየሚለው የማኅበረሰብና  የአገር ምሥል አለው፡፡ ይህ ምሥል ወይም ዕይታ በተቀናጀና ወጥ በሆነ መንገድ ተደራጅቶ ሲገለጽርዕዮተ ዓለምልንለው እንችላለን። በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ቀደም  ብሎና ገኖ ይገኝ የነበረው፣ አሁንም ጠፍቶ ያልጠፋው ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ የአዘማኝነት እሳቤ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ያላት፣ ከምዕራባውያን ሥልጣኔ በተለይም ከቁሳዊና አስተዳደራዊ መላ፣ ዘይቤና  ዘዴዎቻቸው ጋር የተዋሀደ ማኅበረሰብ ያላትን አገር የሚናፍቅ አመለካከት ነበር፡፡ ስለዚህም ዘመናዊ ትምህርት ተስፋፍቶ፣ የተማከለና ዘመናዊ አስተዳደር ሥር ሰዶ፣ ዘመናዊ ጦር ተደራጅቶ፣እርሻና የምርት እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም ግብይትም ዘምኖ ማየትን የሚፈልግ ዘመናዊ አገረ መንግሥትና ምጣኔ ሀብታዊ ሥርዓትን ለማቋቋም ያለመ አስተሳሰብ ነበር፡፡ ታዲያ ይህ አስተሳሰብ በወቅቱ የነበረውን መዋቅራዊ ኢፍትሐዊነት፣ በደልና ጭቆና እምብዛም ያላስተዋለ አመለካከት ነበር። አገርን የማዘመንና መንግሥትን የማጠናከሩ ሒደት ለብዙዎች ሸክም ሲያከብድ፣ ጉስቁልናና ችግርን ሲያባብስ፣ ለጥቂቶች ደግሞ ኑሮን ሲያደላድል፣ አዳዲስ ዕድልና አጋጣሚዎችን ሲያመቻች የማኅበራዊ ሚዛኑ መናጋት ጥግ ደረሰና አብዮት አስከተለ፡፡

አብዮተኞቹ  መሻሻል፣ በጐ ለውጥ ማለት የሀብት እኩልነትን መፍጠር፣ የመደብ ልዩነትን ማስወገድ ነው ብለው በቀደመው ሥርዓት ለነበረው የማኅበራዊ ሚዛን መናጋት ዋነኛ ምክንያት የነበረውን የመሬት ሥሪት ሥር ነቀል በሆነ ሁኔታ ለወጡ፡፡ እነዚህኞቹ አብዮተኞች በዚህ መልኩ ለለውጥ ሲንቀሳቀሱ፣ ይኼ አይበቃም ያሉት ሌሎች አብዮተኞች ደግሞ ተዋግተውና ተጋድለው ሌላ አብዮት አመጡ፡፡ ማኅበረሰባዊ ሚዛኑ የተናጋው በሀብት ክፍፍልና በመሬት ሥሪት ብቻ ሳይሆን በቋንቋ፣ በባህል ብሎም በብሔሮች ፖለቲካዊ አሠላለፍ ነው በማለት ሁሉም ብሔሮች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩባትና ባህልና ቋንቋቸው የተከበረባት አገር ለመፍጠር ሁለተኛ አብዮት እነሆ አሉ፡፡ የመጀመሪያው አብዮትኀብረተሰባዊት ኢትዮጵያንዕውን ለማድረግ ነው ተባለ፡፡ ሁለተኛው አብዮት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን የብሔረሰቦች መብት የተከበረባት ኅብረ ብሔራዊና ፌዴራላዊ ኢትዮጵያን ለማምጣት ነው ተባልን፡፡

ሁለት አብዮቶችን አሳልፈን፣ ብዙ ደም ፈሶ፣ ብዙ ነፍስ ለለውጥ ተገብሮ ይኸው ዛሬም ነገር አልጥም ብሎ፣ ዙርያ ገባው የማያኖር ሆኖበት ለለውጥ የተነሳ፣ ለለውጥ እየሞተ ያለ ትውልድ መጥቷል፡፡ ምናልባትም በሦስተኛ አብዮት ማዕበል ውስጥ ሳንሆን አንቀርም፡፡ እናም በዚህ ሰዓት ቆም ብሎ ከታሪካችን መማር፣ ነገሮችን መመርመርና ማጤን ይገባል፡፡ ከዚህ የቀደሙት ሁለቱም አብዮቶችእኩልነት ዋና ግባቸው ያደረጉ አብዮቶች ነበሩ፡፡ የምጣኔ ሀብትን እኩልነት፣ የብሔሮችን እኩልነት ያመጣሉ የተባሉ አብዮቶች ነበሩ፡፡ ታዲያ ከእነዚህ አብዮቶች በኋላ የብሔር እኩልነት እጅግ አወዛጋቢ ሆኖ፣ የሀብት ክፍፍል ብሶት አስከትሎ አገር እየታመሰ ነው፡፡ እኩል እየተስተዳደርንና እየተስተናገድን  አይደለም የሚለው ድምፅ እጅግ ጐልቶ ወጥቷል፡፡

ስለዚህ ሁለቱም አብዮቶች የየራሳቸው ዘላቂ ስኬቶችና ትሩፋቶች ቢኖሩዋቸውም ጉድለትና ውስኑነትም  አለባቸው፡፡ ይህ ጉድለታቸው ለዛሬው ቀውሳችን ምክንያት ነው፡፡ እነዚህን ስህተቶች መረዳት ስህተቶቹን እንዳንደግም  ይረዳናል፡፡ ይህን በማሰብ ይህንን ጽሐፍ እነሆ ብያለሁ፡፡ ዓላማው የቀደመውን ትውልድ መውቀስም ሆነ ማንቋሸሽ አይደለም፡፡ በቅንነትና ከራስ ይልቅ  ሌሎችን በማስቀደም ከባድ መስዋዕትነት ለከፈሉት፣ ሕዝብና አገርን  በተለያየ መንገድ ላገለገሉ የቀደምት ትውልድ አባላት፣ ለአብዮተኞቹም ሆነ ከእነሱ ለቀደሙት እናቶችና አባቶቻችን ከፍተኛ አድናቆትና ምሥጋና እንደሚገባቸው እረዳለሁ፡፡ ሆኖም ይህ እንደተጠበቀ ለትምህርታችን ይሆን ዘንድ ስህተቶቻቸውን በመጠኑ እንዳስሳለሁ።

የአንድ  ችግርችግር

የትኛውም ማኅበረሰብችግሮችእንጂችግርኖሮት አያውቅም። አንድ አገርና ማኅበረሰብ እንዲሻሻል መለወጥ ያለባቸው የተለያዩ ነገር ግን የተሳሰሩ የማኅበረሰቡ ባህሪያትና ሁኔታዎች እንጂ፣ አንድ ነገር፣ አንድ ጉዳይ፣ አንድ ጣጣ ብቻ የለም፡፡ አንድ ችግር ላይ ብቻ በማተኮር፣ ሌሎች ተግዳሮቶችን  ቸል በማለት የሚመጣው ለውጥ ስንኩልና የተዛባ እንዲሆን፣ ሌሎቹ ችግሮች እንዲባባሱና ሥር እንዲሰዱ ሁኔታውን እናመቻቻለን፡፡ በእርግጥ በአንድ ጊዜ የማኅበረሰቡን ችግሮች ሁሉ መፍታት አይቻልም፡፡ ሁሉም ችግሮች በእኩል ሁኔታ አንገብጋቢም አይደሉም፡፡ ነገር ግን በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ አንገብጋቢ የሆኑ፣ የተሳሰሩና ጐን ለጐን መፍትሔ ሊበጅላቸው የሚገቡ ከአንድ በላይ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ትርጉም ባለውና በዘላቂ ሁኔታ ማኅበረሰባዊ መሻሻልና ለውጥን ለማምጣት ትኩረት የሚሹ ከአንድ በላይ የሆኑ ጉዳዮች አሉ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩት አብዮቶች ዋነኛ የአገር ችግርና ህፀፅ በማለት አብዮተኞቹ ከለዩት  ነገር ውጪ፣ ለሌሎች ችግሮች በተጓዳኝነት የተሰጠው አትኩሮት ከአንገት በላይና አነስተኛ ነበር፡፡ የተለያዩ ችግሮቻችን ለመፍታት ዋነኛ ጉዳዮቻችንን ሁሉ ከግምት ያስገባ፣ የተጣጣመ መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ አንድ አቅጣጫ ላይ አተኩሮ ሌሎች ችግሮችን ቸል ብሎ መራመድ በለውጥ ሒደቶቻችን የታየ አዝማሚያ ነው፡፡ የመደብ እኩልነትን ዋነኛ ዓላማ አድርጐ የብሔር ጉዳይን መዘንጋት፣ የብሔር ጥያቄን ዋነኛ ጉዳይ አድርጐ የድህነትና የዕድገትን ነገር መርሳት፣ የምጣኔ ሀብት ዕድገትን ዋና ቁም ነገር አድርጐ የግለሰብ ነፃነትንና የብሔር ጥያቄንእጅጉ ችላ ማለት፣ ሚዛን ባልጠበቀና በተዛባ አካሄድ በጣም መሮጥ ከባድ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ በለውጥ ጐዳና ተራመድን፣ ነጐድን፣ ከፍ አልን ብለን ሳናበቃ ወደኋላ ማዝገም፣ መውደቅና መንኮታኮት የታሪካችን ዑደት መገለጫ እየሆነ ነው፡፡ ችላ ያልናቸው ጉዳዮች እየጐተቱን፣ እያሰሩን ሩቅ መሄድ ሲያቅተን በተደጋጋሚ ዓይተናል፡፡

ስለዚህ ዛሬም ከዚህ ከቀደመው ስህተት በመማር ችግራችንአንድነገር ብቻ አለመሆኑን ልናስተውል ይገባናል፡፡ ዛሬ አነሱም በዛም ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ቢጠየቁ ዋነኛ ችግሮቻችን የሕወሓት መግነን ወይም የበላይነት ነው በማለት ይመልሳሉ፡፡ የዚህ  ሁኔታ መለወጥ ደግሞ ለአገራችን መሻሻል ሁነኛው መፍትሔ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ይህ ችግር በዕውን መኖሩን፣ ላለንበት ቀውስም ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን እስማማበታለሁ፡፡ ሆኖም በዚህ ጉዳይ ላይ ያለን አትኩሮት ሚዛኑን የጠበቀና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ተያያዥ ነገሮችን ለማሰብ የማይከለክለን ሊሆን ይገባል፡፡ ከአንድ የተደራጀ ቡድን ፈር የለቀቀ የበላይነት ባለፈ ለሰብዓዊ ክብርና እኩልነት ብዙም ቦታ የሌለው የፖለቲካ ባህላችን፣ የኢኮኖሚ ሁኔታችን፣ የአፍሪካ ቀንድ ውጥንቅጥ ሊያሳብቡን የሚገቡ ነገሮች ናቸው፡፡ ሕወሓት በሆነ ተዓምር ከመድረኩ ገለል ቢልም እንኳን  የአገሪቱ ድህነት፣ እኔና ጉልበቴ ብቻ የሚለው አጉል የፖለቲካ ዘይቤያችንና የቀጣናችን ቀውስ  ችግሮቻችን ሆነው ይቀጥላሉ። ችግር ተደርጐ የተወሰደውን የሕወሓት የበላይነት በማስወገድ ሒደት ሌሎቹን ችግሮችን  የሚያባብስ አካሄድ ከኖረን ለውጥ ቢኖርም ለውጡ የተሻለ ማኅበረሰብና አገር አያመጣልንም፡፡

ውስንነታችንንአለማጤን

ከዚህ ቀደም በተለይም በአብዮተኞች ዘመን ለለውጥና የተሻለ አገርን ለመገንባት በተደረጉ ጥረቶች በትህትና የራስን ውስንነቶች ያለማጤን ችግር ነበር፡፡ የሰው ውስንነት ብዙ ነው፡፡ እንዲሁ ከብዙ ጥቂቱን ብናነሳ እያንዳንዳችን የእውቀትና የመረዳት ውስንነት አለብን። በቅጡ ያልተረዳነውና የማናውቀው እጅግ ብዙ ነው፡፡ አለማወቃችንና አለመረዳታችንን ካለማስተዋል የተነሳ አቋማችን ሁሌ ልክ እንደሆነ በማሰብ ከእኛ የተለየ ሐሳብ ያንፀባረቁትን ደግሞ አላዋቂና የተሳሳቱ አድርጐ መቁጠር ያስከትላል፡፡

የአገሪቱ ዋነኛ ችግርይህነው፣ መፍትሔውም ደግሞእንደዚህና እንዲያነው ስንል የያዝነው አቋም ስህተት ሊኖርበት እንደሚችል አለመጠርጠር፣ ሁሌም ሙሉ በሙሉ ልክ ነኝ ማለት ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ከእኛ የቀደመው ትውልድ የዚህ ስህተት ተጠቂ ነበር፡፡ ከዚህም ባለፈ፣ ማለትም ከእውቀትና ከመረዳትም ባሻገር ሌሎች ውስንነቶችም አሉ፡፡ አቋማችን በእውቀትና  በመረዳት ላይ ብቻ የተመረኮዘ ሳይሆን በጥቅም፣ በፍላጐትና በስሜትም የሚወሰን ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ የፍላጐትና የጥቅም ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ለሕዝቡ ሁሉ በቅንነትና ያለማዳላት የሚጠቅመውን አስባለሁ፣ የሁሉን ፍላጎትና ስሜት አንፀባርቃለሁ ማለትም አይቻልም፡፡ ሁሉን መወከልና መረዳት ከባድ ነው፡፡ የራስን ስሜትና ጥቅም መግራት ከባድ ነው፡፡ የሚቀለው የራስን ጥቅምና ፍላጎት የሕዝብ ጉዳይና ፍላጎት አድርጐ ማቅረብ ነው፡፡ ከብዙዎች ቀድመው ራሳቸውን  በዚህ መልኩ ያታልሉና ከዚያ በኋላ የሚያደርጉት ሁሉ ለሕዝብ ጥቅምና በቅንነት የሚደረግ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ውስንነታቸውን ባለማስተዋል ሁሌም ትክክልና ሁሉንም የሚወክሉ እንደሆኑ ያስባሉ። በዚህ ሁኔታ በመራመድ ከእነሱ የተቃረነ አመለካከትና አቋም ያለውን ሁሉ የሕዝብ ጠላት፣ አላዋቂ ወይም ክፉ  አድርገው ያያሉ፡፡ ስለዚህ ለራሳቸውም የመታረም ዕድል ይነፍጋሉ፣ ሌላውንም ያለምሕረት ለማጥቃት ይደፍራሉ፣ ይጨክናሉ፡፡

የመርህ ሚዛን አለመጠበቅ

ከዚህ በቀደመው ትውልድ ሁለት የሚቃረኑ አዝማሚያዎች ታይተዋል፡፡ በአንድ በኩል በንድፈ ሐሳብና በምናብ ያለን ዕቅድ ወይም መርህ ሙሉ በሙሉ እንደ ወረደ ካልተገበርኩኝ የሚል ጭልጥ ያለ የመርህ አክራሪነትና ምናባዊነት ነበር፡፡ የአልባኒያን ኮሙዩኒዝም፣ የጠራና ሳይንሳዊ ማርክሲዝም  እንተግብር ወይም ለሰማንያ ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል እናጐናፅፍ የተባለው ይህን በመሠለ የመርህ ጽንፈኝነት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ የመርህ ፅንፈኝነት ጀርባ የለየለት የግብረገብ ወይም የሥነ ምግባር ደንቦችን ሁሉ የመጣስ አዝማሚያ ነበር፣ አሁንም አለ፡፡ ፅንፍ የረገጠውን ፖለቲካዊ መርህ ሰበብ በማድረግ በጭካኔ መግደል፣ ማሰቃየት፣ መግረፍ፣ መዋሸት፣ በግለሰቦች ላይ በደልና ግፍን መሥራት የተለመደ ነበር፣ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ጠበቅ ተደርጐ መያዝ ያለበት እያላላ፣ መክረር የሌለበትን ደግሞ እጅግ ማጥበቅ የአብዮተኞቻችን ባህሪ ነበር፡፡ የተራማጅነት ጐዳናቸው በራሳቸውና በሌሎችም ደም የጨቀየ፣ የነፃ አውጪነታቸው ቀንበር የማያላውስ፣ ለዓላማ የቆረጡ፣ ሰብዓዊነትን ያልተላበሱ፣ ሕዝብየወገኑ፣ በግለሰቦች ላይ የጨከኑ ነበሩ፡፡ ይህ የአብዮተኞቻችን የሞራል ተቃርኖና  የሚዛን ማጣት ብዙ ዕንባ፣ ብዙ ደም  እንዲፈስ ምክንያት ሆኗል፡፡ እና ምን እናድርግ?

ስለዚህ ከዚህ በመማር ምን እናድርግ? በኛ ትውልድስ ለውጥን ስንፈልግ የትኛውን አካሄድ እንምረጥ?

እንደ ሕዝብና እንደ አገር ያሉብን ችግሮች ዘርፈ ብዙ፣ ውስብስብና ተያያዥ መሆናቸውን አንዘንጋ፡፡ የእነዚህን ችግሮች ተያያዥነትና ውስብስብነት በመረዳት ስለ መፍትሔውም ስናስብ ሰፋና  ጠለቅ አድርጐ በማሰብ ፍትሕ፣ ብልፅግናና ነፃነትን ዓላማ አድርገን፣ የእያንዳንዱን የማኅበረሰባችን አባል ሰብዓዊ ክብር ማስጠበቅን ዋና ዓላማችን አድርገን እንንቀሳቀስ፡፡ ችግሮቻችንን ዘላቂነት ባለውና ሁሉንም በሚያሳትፍ ሒደት እየለየን፣ እየመከርንና እየተግባባን መፍትሔ ለማበጀት ፈቃደኛ መሆን አለብን፡፡ ይህ ደግሞ የአንድ ጊዜ ክስተት ሳይሆን ተቋማዊ ቅርፅ ያለው  ቀጣይ ሒደት ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ያለው ችግር ቢቀረፍ ሌላ አዲስ ችግር ይመጣል፡፡ ዓለም ዘጠኝ እንጂ አሥር ሆኖ አያውቅም፡፡ የአንዳንዶች ችግር አትኩሮት አግኝቶ የሌሎች እንዳይዘነጋ ደግሞ ሒደቱ ለሁሉም ክፍትና አሳታፊ መሆን አለበት፡፡

ውስንነታችን አንርሳ፡፡ እውቀታችን ሙሉ አይደለም፡፡ የማንወክለውና የማንረዳው ሰው ጥቂት አይደለም፡፡ ሐሳብና ፍላጎታችን ሁሌም ቅን ላይሆን ይችላል፡፡ አለማወቅ፣ ራስ ወዳድነት፣ የግል ፍላጎትና ጥቅም ወይም ስሜት ሊያሳስቱን ይችላሉ፡፡ ያልተረዳነውና ያልገባን ብዙ ነገር ሊኖር ይችላል። ስለዚህ ሁሌም ለመታረም ዝግጁ  መሆን አለብን፡፡ ከእኛ የተለየ ሐሳብና አቋም ያለውን ሰውም እንደ ክፉ፣ እንደ  አላዋቂና እንደ ጠላት ማየት የለብንም፡፡ በውይይት ለመግባባትና ለመቀራረብ፣ እስከተስማማነው ድረስ አብሮ ለመሥራትና ለመተጋገዝ ዝግጁ መሆን አለብን፡፡ ባልተግባባንበትም ጉዳይ ላይ ተከባብሮ ለመኖርና ለመቻቻል ፈቃደኛ መሆን አለብን፡፡

የፖለቲካ መርሆቻችንን ፅንፍ ባልረገጠ፣ ተግባራዊ ሊሆን በሚችል ሁኔታ ይዘን የሥነ ምግባር መመርያዎቻችንን ደግሞ በተቻለን መጠን በጥብቅ ልናከብር  ይገባል። የፖለቲካ ግባችንን ለማሳካት ስንንቀሳቀስ  አግባብነት ባለው የሥነ ምግባር ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን፣ በሞራል ልጓም ተጠብቀን ሊሆን ይገባል፡፡ እነዚህን የሥነ ምግባር መመርያዎቻችንንም በሕግና በተቋም አስደግፈን፣ አስገዳጅ አድርገን ልናስከብራቸው ይገባል፡፡

ይህን አካሄድ ሚዛናዊ ተራማጅነት ልንለው እንችላለን፡፡ ምክንያቱም፡-

  • ማኅበረሰባዊና አገራዊ ለውጥ ወይም መሻሻልን የሚፈልግ ተራማጅ ዝንባሌና አስተሳሰብ ነው፡፡
  • በማኅበረሰቡ ውስጥ አንድን ችግር ለመፍታት ተብሎ የሚወሰደው ዕርምጃ የባሰ ችግርና ቀውስን እንዳያመጣ፣ አግባብነት ያላቸውና ምክንያታዊ ጥቅሞችና ፍላጐቶችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አስታርቆ፣ ሚዛኑ ባልተዛነፈ መልኩ ለውጥና መሻሻልን ለማምጣት የሚፈልግ አካሄድ ነው፡፡
  • በምናውቀውና በተረዳነው ልክ የመራመድን፣ ሥነ እውቀታዊ ትህትናን ዋጋ የሚሰጥ፣ የራስን ውስነንት የተረዳ፣ የመወከል ብቃትና አቅማችን ልኬት ያገናዘበ፣ የግል ስሜት፣ ጥቅምና ፍላጎት በአቋማችን ላይ የሚያሳድሩትንፅዕኖ ከግምት ያስገባ፣ በውስጣችን ያለውን በጎነትና ታላቅነት፣ እንዲሁም ክፋትና ትንሽነት በአግባቡ የተገነዘበ ሚዛናዊ አካሄድ ነው።
  • ለፍትሕ፣ ለሰብዓዊ ክብርና ነፃነት፣ ለእህትማማቾች/ወንድማማቾች ኅብረትና ትስስር የሚቆም፣ በእነዚህ መርሆዎች ስም የሚደረግ የዘቀጠ አካሄድን የማይቀበል፣ ፖለቲካዊ ፍትሕን በጨዋና በሠለጠነ መንገድ የሚሻ አስተሳሰብ ነው። ይህ ሚዛናዊ ተራማጅነት ነው።     

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡