Skip to main content
x
ዓለማችንን በትምባሆ ኢንዱስትሪ ከተደቀነባት አደጋ እንዴት እንታደጋት?

ዓለማችንን በትምባሆ ኢንዱስትሪ ከተደቀነባት አደጋ እንዴት እንታደጋት?

በቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) እና በታባሬ ራሞን

ትምባሆና ከትምባሆ ጋር ተያያዥ የሆኑ ምርቶች ለጤና አደገኛ በሆነ ሁኔታ ጠንቅ አንደሆኑና በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ፣ እንዲሁም ከዚህ የበለጠ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች እየጎዳ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ትልልቅ ዓለም አቀፍ የትምባሆ አምራች ኩባንያዎች፣ ምርታቸው ጤና ላይ ሰለሚያደርሰው ጉዳት ለዘመናት አሳሳች የሆነና የውሸት መረጃዎችን ሲያወጡና ሲፈበርኩ እንደቆዩ የሚታወቅ ሀቅ ነው፡፡

ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ትልልቅትምባሆ አምራቾች፣ ትምባሆ የሚያስከትለውን ከፍተኛ ጉዳት በተመለከተ ትክክለኛውን መረጃ ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ በፍርድ ቤት ተገደዋል፡፡

ከአሥር ዓመት በፊት በአሜሪካ የፌዴራል ፍርድ ቤት የተፈረደባቸውና ይህን ተከትሎ ብዛት ባላቸው የይግባኝ አቤቱታቸው ላይ ተቀባይነት ያጡ አራት ትልልቅ የትምባሆ አምራቾች በክርክሩ ተሸንፈዋል፡፡ በፍርድ ውሳኔውም ለዘመናት እነዚሁ የትምባሆ አምራቾች ከምርቶቻቸው ጋር በተያያዘ የውሸት መረጃዎችን ያሠራጩ እንደነበር፣ አሳሳች የገበያና የሽያጭ ሥልቶችን ይጠቀሙ እንደነበርና ይህንኑ ድርጊት ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርጉ ተገደዋል፡፡

ይህን ተከትሎም እነዚህ የትምባሆ አምራቾች ለሠሯቸው በሕግ የሚያስጠይቁ ተግባራት ዕርምት እንዲያደርጉ፣ በተለያዩ ጋዜጦችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሕዝብን እንዳሳሳቱና እውነቱን እንዲናገሩ ጭምር ተገደዋል፡፡ በዚህም የፍርድ ውሳኔ ፊሊፕ ሞሪስ (Philip Morris USA)፣ አር ጄ ሬይኖልድ ቶባኮ (RJ Reynolds Tobacco)፣ ሎሪላርድ (Lorillard) እና አልትሪያ (Altria) የተባሉ ኩባንያዎች ትምባሆ ለጤና ያለውን ጉዳት እያወቁ፣ ነገር ግን በተቃራኒው ምርታቸውን አሳሳች በሆነ የሽያጭ ሥልት ይሸጡ ስለነበር፣ ይህንኑ እውነታ ‹‹የእርምት ማስታወቂያ›› እያሉ በጋዜጣና በቴሌቪዥን እንዲያወጡ ተደርጓል፡፡ 

ከእነዚህና ተመሳሳይ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ላይ ካነጣጠሩ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በተጨማሪ፣ በቅርቡ አንድ ፈረንሣይ አገር የሚገኝ ቢኤፒ ፓሪባስ የተባለ ባንክ ለትምባሆ አምራች ተቋማት ብድር መስጠት ማቆሙንና እነዚህ ተቋማት ላይ በምንም መንገድ ገንዘቡን ኢንቨስት እንደማያደርግ በቅርብ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ይኼም የኅብረተሰብ ጤና ጥበቃ ከንግድና ከንዋይ ፍላጎቶችና ጥቅማ ጥቅሞች በላይ ትኩረት እየተሰጠው እንደሆነ ያሳያል፡፡

አሁን እያየነው ያለው የትምባሆ ኢንዱስትሪ የእምነት ቃል ከፍላጎትና ሰብዓዊነት የመነጨ ነው ብለን መረጋጋት የለብንም፡፡ በተቃራኒው የትምባሆ ኢንዱስትሪው ሲጠቀምበት የነበረውን አሳሳች የግብይት መንገድ የአሜሪካው የፍትሕርዓትበትምባሆ ቁጥጥር ተሟጋቾቹ በፈጠሩት ጫናና ከጥርጣሬ የፀዳ ሊባል በሚችል ብዛት ያለው የሳይንሳዊ ግኝት ማስረጃ አማካይነት የመጣ ውጤት ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢንዱስትሪው ባለፉት ጊዜያት ሊታመን የማይችል አንደሆነ የተረዳንበትና ለወደፊቱ ትክክለኛውን ነገር ይሠራል ተብሎ መታመን የሌለበት ነው ብለን እናምናለን፡፡

በአሁኑ ወቅትም የትምባሆ ኩባንያዎች ከሲጋራ የተሻለና ‹‹መጠነኛ ጉዳት›› ያለው ምርት ነው እያሉ አዳዲስ ምርቶችን እያስተዋወቁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በማጨስ ሳይሆን በማሞቅ የሚጠቀሙባቸው "heat-not-burn" የሚባሉ አዳዲስ መሣሪያዎች በማስተዋወቅና በተያያዥ ከእነዚህ ምርቶች ንግድ በተጨማሪ ከትምባሆ ጭስ ነፃ ዓለም (smoke-free world) ለመፍጠር እንታገላለን የሚሉና በትምባሆ ኢንዱስትሪው የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ፣ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትን በማገዝ የራሳቸውን ተፅዕኖ ለመፍጠር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

የዓለም የትምባሆ ኩባንያዎች እንደ ኡራጋይና አውስትራሊያ ያሉ አገሮችን ጨምሮ በሌሎችም አገሮች የትምባሆ ምርቶችን ለመቆጣጠር፣ ሕግን ተከትለው በወጡ የትምባሆ የቁጥጥር ደንቦች ላይ ጠንካራ የሆኑ ተግዳሮቶችንና እንቅፋቶችን ለመፍጠር መሞከራቸው ተስተውሏል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ደግሞ የትምባሆ ኩባንያዎች የሕዝብን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሕግን ለመቃወም፣ አዳዲስ የማምለጫ ዘዴዎችን መፍጠሩን እንደሚቀጥሉ ግልጽ ነው፡፡

በእርግጠኝነት በአሜሪካ ሚዲያዎች አማካይነት ‹‹የእርማት ማስታወቂያዎች›› እንዲተላለፉ ፍርድ ቤቱ መወሰኑ ለእውነት ትልቅ ድል ነው፡፡ ይህ የአሜሪካ ፍርድ ቤት ውሳኔ እ.ኤ.አ በ1999 በማጭበርበር ገንዘብ የሚያገኙ ሙሰኛ ድርጅቶች አዋጅን (Racketeer Influenced and Corrupt Organizions Act) መሠረት አድርጎ፣ ክስ በተመሠረተባቸው የትምባሆ ምርት አምራቾችና እ.ኤ.አ በ2006 ከተላለፈው ትዕዛዝ በኋላ ለአሥር ዓመታት በይግባኝና ሕጋዊ ውዝግብ የቆየውን ጉዳይ እ.ኤ.አ በጥቅምት 2017 ፍፃሜ እንዲያገኝ አድርጓል፡፡

የእርማት ማስታወቂያዎቹ ትምባሆ ማጨስና አጫሽ ያልሆነ ሰው ለሲጋራ ጭስ ከተጋለጠ ገዳይ እንደሆነ የሚዘረዝር ነው፡፡ በትምባሆ ድርጅቶቹ በኩል ከተላለፉት የእርማት ማስታወቂያዎቹ መካከል፣ ‹‹ሲጋራ ሆን ተብሎና ታቅዶበት በውስጡ ያለውን ኒኮቲን የተባለ ንጥረ ነገር ወደ ሰውነታችን ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲዋሀድ የተሠራ ምርት ነው››፣ ‹‹አነስተኛ ታር ያላቸውና ቀላል ሲጋራዎች እየተባሉ የሚሸጡት ከመደበኛው የትምባሆ ምርት እኩል ጎጂ ናቸው››፣ ‹‹ማጨስና በሲጋራ ውስጥ የሚገኘው ኒኮቲን የሚባለው ንጥረ ነገር በእጅጉ ሱስ አስያዥ ነው፤›› የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ሌላው ቢቀር የሲጋራ አምራቾች እንኳን በየቀኑ 1,200 አሜሪካውያን ሕይወታቸው በሲጋራ ምክንያት አንደሚያጡ ያውቃሉ፡፡ በዓለም ዙሪያ ደግሞ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ትምባሆ ማጨስ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ይገድላል::

አሁን በዚህ አስጨናቂና ወሳኝ ጊዜ ላይ ሆነን በትምባሆ ምክንያት የሚመጡና እየደረሱ ያሉ ዘርፈ ብዙ አሉታዊ ተፅዕኖዎችንና ችግሮችን ለአንዴና ለመጨረሻ በቃ የምንልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ እንደ እኛ ያሉ መንግሥታዊ የሆኑና እንደ እኛ ዓይነት የጤና ድርጅቶች ከትምባሆ ኢንዱስትሪ ጋር ከባድ የሚባል ጦርነት ላይ መሆናቸውን፣ እነዚህን ትልልቅ ትምባሆ ኩባንያዎች ሳናሸንፍ እንቅልፍ እንደማይወስደን ግንዘቤ መወሰድ አለበት፡፡

የአገሮች መሪዎች፣ የጤና ሚኒስትሮችና የፋይናንስ መሪዎች የትምባሆ ምርቶችን ለመቆጣጠር ምን ያህል ርቀት መጓዝ እንዳለባቸው ካሳሰባቸው፣ የራሳቸው የትምባሆ አምራቾች የእምነት ቃልና ኢንቨስተሮች በትምባሆ ላይ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ በድጋሚ እያሰብንበት ነው ማለታቸው እንደ አስፈላጊነቱ በቂ የሆነ መልስ ይሆናል፡፡ መንግሥታት ዜጎቻቸውን ከትምባሆ ለመጠበቅ እጅግ በጣም ጠንካራ የሆኑ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ የሞራልና የሕግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የትምባሆ ቁጥጥር ወደፊት የሚመራበትን የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣውን የዓለም የጤና ድርጅት የትምባሆ መቆጣጠሪያ ኮንቬንሽን (WHO FCTC) ውስጥ የተካተቱት የትምባሆ ቁጥጥር ተግባራት እንዲፈጸሙ ማድረግ አንዱ መንገድ ነው፡፡ ይህ የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን እንደ ትምባሆ ቀረጥ መጨመርን፣ በትምባሆ ምርት ማሸጊያ ፓኬጅ ላይ የጤና ማስጠንቀቂያዎች ማስቀመጥና የሕዝብ ግንዛቤ መፍጠር ባለፈው አሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለማዳን ረድተዋል፡፡ በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በትምባሆ የሚመጡ የጤና ወጪዎችን አድኗል፡፡

ሆኖም ይህንን የጤና ስኬት በበለጠ ማከናወን ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው አገሮችን የበለጠ የትምባሆ መቆጣጠሪያ ፖሊሲዎች ዕርምጃዎችን እንዲወስዱ ጥሪ የምናስተላልፈው፡፡ አገሮች የትምባሆ መቆጣጠሪያ ኮንቬንሽንን በተሻለ ሁኔታ መተግበር አለባቸው፡፡ ይህንንም በማድረግ ከትምባሆ ኢንዱስትሪዎች የሚመጣባቸውን ጫና በብቃት መከላከል ይችላሉ፡፡

እንዲሁም መንግሥታት ሕገወጥ የትምባሆ ንግድንና ሥርጭቶችን ለመከላከልና ለማስቀረት የወጣውን ፕሮቶኮል ማፅደቅ ይኖርባቸዋል፡፡ እስካሁን ድረስ 33 የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ፕሮቶኮል የፈረሙ ሲሆን፣ ፀድቆ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ሰባት ተጨማሪ መንግሥታት ፕሮቶኮሉን ማፅደቅ አለባቸው፡፡

በመጨረሻም እ.ኤ.አ በ2018 በሚደረገው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስብሰባ ላይ በመገኘትና ጠንካራ የትምባሆ ቁጥጥር የሕግ ማዕቀፎችን በማውጣት ሕዝባቸውን ከልብ፣ ከሳንባ፣ ከካንሰርና ከስኳር ከመሳሰሉ በሽታዎች ለመጠበቅ ያላቸውን ቁርጠኝነትና ዝግጁነት ማሳየት አለባቸው::

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊዎቹ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር (ቴድሮስ አድሃኖም) እና የኡራጋይ ፕሬዚዳንት (ታባሬ ራሞን) ሲሆኑ፣ ጹሑፋቸው በቅርቡ ፕሮጀክት ሲንድኬት ላይ ወጥቶ ነበር፡፡ ጽሑፉ የእነሱን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡