Skip to main content
x

መፈተሽስ ራስን ነው!

ሰላም! ሰላም! ‹‹እነሆ ከ17 ዓመታት ብሶት የወለደው ትጥቅ ትግልና ብሶት ከገፋፋው የ17 ቀናት 'የዝግ ስብሰባ' ያተረፍነው ነገር ቢኖር የማይታረም ጥፋትን በጥልቅ ተሃድሶ ስም፣ የሕግ የበላይነትን በይቅርታ አሳቦ መሸወድ ነው፤›› ያለኝ ማን ነበር? የታሰሩት ይፈታሉ ሲባል ሰምቶ አዳሜ ቀላል ይቀባጥር መሰላችሁ? “የታሰሩት እየተፈቱ እንዴት አዳዲስ ያስራሉ?” እያለ ነዋ። ድንቄም ሕግና የሕግ የበላይነት . . . ‹‹በቃ ግን ይህች አገር የሥልጣን እንጂ የሕግ የበላይነት የማይገዛት አገር ሆና ልታረጅ ነው?›› ሲል ልጃቸውን ሰምተውት ኖሮ ባሻዬ፣ ‹‹ከዚህ በላይ እንዴት ታርጅልህ? ማለት ካለብህማ እንዲህ በዋዛ ፈዛዛ እንዳፋዘዝናት ክርስቶስ መጥቶ ሊገላግለን ነው ወይ ነው ማለት ያለብህ፤›› አሉት። አሁን ይኼን ሁሉ የሚያባብለን ምን እንደሆነ አውቃችኋል አይደል? የሰሞኑን የኢሕአዴግ መግለጫ ነዋ።

አንድ ቀልደኛ ወዳጅ አለኝ። ባለፈው ቅጥቅጥ አይሱዙ እያሻሻጥን ነበር። እና ልናስፈትሸው ጋራዥ ወሰድነው፡፡ ጋራዥ ግቢ ውስጥ ቆመን አንድ ልጅ እግር አካሉ ግን ግዙፍ (የማዳበሪያው ትውልድ አካል መሆኑ ነው) በአጠገባችን ሲያልፍ ሲያገድም እየረገጠን ያልፋል። መለስ ይልና ‹‹ይቅርታ አላየኋችሁም፤›› ብሎን ይቅለሰለሳል። ደግሞ ሲያልፍ ሁለታችንንም ጨፍልቆን ዞር ብሎ፣ ‹‹ውይ ዛሬ ምን ነክቶኝ ነው? ዓይኔ ጠፍቷል እንዴ?›› እያለ ልባችንን ሲያደርቀው ወዳጄ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹ሰው እኮ ወዶ አይደለም የቆመበትን ትቶ የሚሰደደው? ይኼ ልጅ እንደ ኢሕአዴግ በዓመት ሦስት ጊዜ አጥፍቻለሁ፣ እታደሳለሁ የማለት አባዜ ላይ ስለሆነ እብደቱ እስኪለቀው፣ ዓይኑ እስኪበራ ና ፈቀቅ እንበል፤›› አይለኝ መሰላችሁ? በዓመት ሦስቴ እንደ ኢሕአዴግ ደስ አይልም? ግን ሦስቴ እየበላችሁ ነው ለመሆኑ? ‹‹ፅድቁ ቀርቶብኝ ጥጋብ በገደለኝ፤›› አለ አሉ ጠኔ ያደባየው!

 እናላችሁ ሰሞኑን ቀደዳ በቀደዳ ላይ ነበርን። ያም ይቀዳል፡፡ ይኼም ይቀዳል፣ ሁሉም የሚያወራው ባለፈው ስለተሰጠው መግለጫ ነው። ‹‹እኛ . . .›› አለኝ አንዱ በቀደም የንብ ቀፎ ልማት ላይ የተሠማራ ወጣት መሬት ላጋዛው ደብረ ዘይት ተጉዘን ሳለ፣ “ . . . ስለፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል፣ ሕግና የሕግ የበላይነት፣ ስለፍትሕና ተጠያቂነት፣ ስለአንደኛና ሁለተኛ ዜግነት፣ ስለኑሮ ውድነትና ስለመኖሪያ ቤት እጥረት ነው እንጂ ጥያቄያችን ሙዚየም አጥሮናል፣ አንሶናል ብለናል? 27 ዓመታት ከተጠቀሙበት በኋላ 17 ዓመታት ደርግ የገረፈበትና ያንገላታበትን እስር ቤት ዘጋን ሲሉ አያፍሩም?” ሲለኝ የት ልግባ። የትም ብገባ፣ ‹‹እሱን ስትገረፍ ታወጣዋለህ›› በሚዘፈንባት የጡጫ አገር የትስ አመልጣለሁ? የሰማ ያልሰማ ብሎ ነገር የለማ። ታውቁት የለ እንዴ? አሁን ይ ዘፈን የሆነው ቀልድ ራሱ ማለት እኮ ነው።

‹‹ስምህ ማን ነው? ለነገሩ ተወው ስትገረፍ ታወጣዋለህ። ፆታህስ? እሱንም ስትገረፍ ታወጣዋለህ . . . ›› አይደል ቀልዱ? ሀቁም ያው ቀልዱም ያው ነው ብዬ ነው። እና በጥልቅ ታዳሹ መንግሥታችን ከ27 ዓመታት በኋላ ዜጎቹ ‹‹አንብብልኛ . . . እሱን ስትገረፍ ታወጣዋለህ፤›› በሚል ዘፈን የምሽት ሕይወታቸውን ማቅለጣቸውን ሳያይ፣ ሳይሰማ መሆኑ ነው ብሶትና የአሸሼ ገዳሜ ማጫፈሪያ ቅመም እንደሆነ ልብ ሳይል ማለት ነው፡፡ ከዛሬ 27 ዓመታት በፊት ለ17 ዓመታት ደርግ ለእስርና ለእንግልት ይጠቀምበት የነበረውን ሥፍራ ሙዚየም ማድረጉን ሲያበስር እነሆ በታላቅ . . . ብዬ በእንጥልጥል ብተወው፣ መቼም ይህቺን ዳሽ መሙላት አያቅታችሁም። ስንቱን ሞልተናል እንኳን ይኼን። ዘንድሮ ካርዱም ሲፋቅ ቁጥሩ አብሮ እየተፋቀ ከዜሮ እስከ ዘጠኝ በግምት ስንሞላ ነው የምንውለው። ካርድም እኛን ቢሆን እንዳትሉኝ ብቻ? ‹‹ቁጥሩን ስትገረፍ ታወጣዋለህ ልትሉት?” ኧረ እንዴት ተቀለደ . . . ።

ሳይፍቁን በፊት ከፍቀትና ከዳሽ ሙላ እንውጣና በተቃራኒ እንጫወት። ከአማርኛ ትምህርት በቀር ሌላውን መቶ የሚዘጋ የጎረቤቴ ልጅ አለ። እና ሠፈራችን ውስጥ አማርኛ ይሻላል፣ ያውቃል የምባለው እኔ ሆኜ የአማርኛ መምህሩ የሚሰጡትን የቤት ሥራ የምሠራው እኔ ነኝ። በነገራችን ላይ ለዚህ ኃላፊነትና ተግባር በተለይ በዚህ ዘመን መታጨቴን ልብ ስለው ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት እኩል ልቤ ይኩራራብኛል። በሰው በቋንቋ ደምቀን፣ በሰው ሥሌት ኮርተን፣ በገዛ ራሳችን ልሳን የተፋፈርን የምንገርም፣ የምንደንቅ ፍጡሮች ሆንና ይኼው አማርኛ ቋንቋ ከሃምሳ ቀርቶ ከመቶ 49 ማምጣት የማይችሉ ልጆች ወለድን። እናላችሁ እሱን የቤት ሥራውን እያሠራሁ ሬዲዮ ከፍቼ አዳምጣለሁ። የአማርኛ ጥያቄና መልስ ዝግጅት ነው። ጋዜጠኛው፣ ‹‹ዘለዘለ ለሚለው ቃል ተቃራኒውን ተናገር፤›› ብሎ በስልክ መስመር ላይ ከሚገኘው አድማጭ መልስ ይጠብቃል። አድማጩ አስበ፣ አሰበ፣ አወጣ፣ አወረደና፣ ‹‹የስፖርት ጥያቄ የለህም? ይኼ ይከብዳል። ስለእንግሊዝ ፕሪሚየም ሊግ ጠይቀኝ፤›› አለው።

ልብ በሉ። የተሳሳትኩት ወይም የገደፍኩት ቃል የለም። ያለውን ነው የምነግራችሁ። ጋዜጠኛው መልሶ፣ ‹‹ግድ የለም የዘለዘለን ተቃራኒ ሞክርና ወደ ስፖርታዊ ጥያቄዎች እናልፋለን፤›› ሲለው የሞት ሞቱን፣ ‹‹የዘለዘለ ተቃራኒው አልዘለዘለም ነዋ፤›› ብሎት አረፈው። ወዲያው ሳቄን አፍኜ ታዳጊው ተማሪ ይኼን መሰል ድፍረትና ፍፁም ያለማወቅ ስህተት ልብ እንዳይል ቶሎ ብዬ አጠፋሁት። አላውቀውም ይለፈኝም አንድ ነገር ነዋ። አፍራሽና ተቃራኒን በአንድ መጨፍለቅ ግን በቃ የዘመኑ ፋሽን ሆኖ ሲያሰቃየን ሊኖር ነው ማለት ነው? የገባው ገብቶታል!

ኧረ ሳልነግራችሁ። ከነገርኳችሁ አይሱዙ ከምኑም ከምኑም ብዬ ኪሴን ብሞላውም ሰሞኑን ስባንን ነው የሰነበትኩት። በህልሜ ይመስለኛል ዶሮዎች በሙሉ ሰላማዊ ሠልፍ ወጥተው፣ ‹‹በበዓል ስም ማረድ ይቁም!›› ሲሉ አያለሁ። እኔ እኮ ዘንድሮ ምን እንደሚሻለን አላውቅም። በህልም አመፅ፣ በዕውን አመፅ፣ ውዷ ማንጠግቦሽ ራሷን አልችል ብላው፣ ደረቴ ላይ ጣል አድርጋው ሳለ ይኼው የአመፅ ቅዠት ነው መሰል ብንን አልኩ። ቀን እንባንንና ሌት ሌት ይቀናናል። እንዲያው እኮ! ስባንን ቀሰቀስኳት። እየተገላበጠች፣ ‹‹ስንት ሰዓት ነው?” ብላ ጠየቀችኝ። አይገርምም? እስኪ አሁን ጨለማ ተቆጠረ አልተቆጠረ ምን ይፈይዳል? ‘ከሌሊቱ ስንት ሰዓት ነው?’ ይሉናል ደርሰው። እንጃ የእናንተን። ብቻ እኔ ሳልደርስባቸው የሚደርሱብኝ እያደር ጨምረዋል። ምናልባት እኔ ሳባርራቸው ወደ እናንተ ከመጡ መልሱ ‘አልነጋም ገና ነው!’ ነው። አደራ ከእኔ አልቀዳችሁትም እሺ። ደግሞ ያስኮርጃል ተብዬ ኋላ ጣጣ እንዳታመጡብኝ።

የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ማንም አይነካህም አይዞህ። መጀመርያ በኩረጃ እያለፉ ያስመረቁዋቸውን ይከልሱ፤›› ሲለኝ ነበር። ማን ተመራቂ ማን አስመራቂ እንደሆነ እሱ ሲያወራ ግራ ገባኝ። ግን እንዲያው አደራችሁን ሌት ከሆነ ሰዓት ማሥላት ምን ይጠቅማል? ሰቅዞ ይዞኝ እኮ ነው የምደጋግምባችሁ። የቀኑን ብሃን ሳይቀር ይኼ የዘመን ጨለማ ከል እያለበሰው የመንገድ መብራት 24 ሰዓት ይብራልን ሳንል አንቀርም ትላላችሁ ትንሽ ቆይተን? “አይ አንበርብር! ‘ዩ አር ቱ ፋር ፍሮም ዘ ሪያሊቲ” ይለኛል ምሁሩ ወዳጄ። “አብራራ!” ስለው፣ “አንተም ቤት ለቤት በቅጡ ያልተዳረሰና የሚቆራረጥ ኃይል እንዴት ሆኖ መንገድ ለመንገድ 24 ሰዓታት ሊበራ እንደምታስብ አብራራ፤” ብሎ ይስቅብኛል። ኧረ እኔስ አልስቅም። ቀኑ በጨለማ ኃይል የተያዘበት ምስኪን ይህን ሁሉ ዕልቂት፣ ይህን ሁሉ ፍጅት፣ ይኼን ሁሉ የፖለቲካ የበላይነትን ለማስጠበቅ የሚደረግ የአውሬዎች ሴራ እያየ እንዴት ይስቃል? ማን ነበር፣ ‹‹የሳቅ መቆራረጥ ያስቸገረን በዓለም መንግሥታት የአስተዳደር ብልሹነት ነው፤›› ብሎ ሲደመድም የሰማሁት?

በሉ እንሰነባበት። በህልሜ ስላየሁት የዶሮዎች አመፅ ለባሻዬም ቢሆን ትንፍሽ አላልኩም። ይባስ ብላ ማንጠግቦሽ፣ “ሦስት ዶሮ ካልታረደ በአንድ ዶሮ ብቻ አልውልም፤” አለችኝ። “ምን ማለትሽ ነው ሰውስ ምን ይለናል?” ስላት፣ ‹‹ምንስ ቢል? ከዓመት ዓመት በቆዳ ብቻ መዋል ሰልችቶኛል። አንድ እኔና አንተ ለብቻችን የምንበላው፣ አንድ ለእነ ባሻዬ የምናበላው፣ ሌላው ደግሞ ድንገት ዘው ለሚለው ጎረቤት የምናቀርበው ሦስት ዶሮ ማረድ አለብን፤” ብላ ሰቅዛ ስትይዘኝ የህልሜ ፍቺ ተገለጠልኝ። ይሁን ብዬ ለሦስት ዶሮ አንድ ሺሕ ከምናምን ብር አወጣሁ። በኋላ ሳስበው ግን ማንጠግቦሽ ልክ ናት። በተለይ በተለይ ካወጣሁት ገንዘብ አንፃር ሳስበው ነገር ዓለሙ ተዘባረቀብኝ።

በቀደም አንድ ቡቲክ ገብቼ ቲሸርት ስጠይቅ ሻጩ ዘጠኝ መቶ ብር እንዳለኝ  ነግሬያችኋለሁ? ታዲያ ሦስት መቶ ብር ጨምራችሁበት ሦስት ዶሮ አርዳችሁ በምትበሉበት ቅጥ ያጣ ገበያ ባለበት አገር መወለዳችሁ በራሱ እንደ ክርስቶስ መቀባት አይደለም ትላላችሁ? በኋላ ለባሻዬ እንዲያ ስላቸው፣ “ምን ሆነሃል ይህ በዓል እኮ የመብልና የመጠጥ አይደለም። የፀጋ፣ የሰላም፣ የደስታና የእርቅ በዓል ነው፤” ብለው ሳይጨርሱ ትን አላቸው። ተሯሩጠን ውኃ ሰጠናቸውና ነፍሳቸው መለስ አለች። በአሸሼ ገዳሜ የተያዘ ፆም በአሸሼ ገዳሜ በሚፈታባት አገር ገበያው ቅጥ ባያጣ፣ ሰው ቅጥ ባያጣ፣ መንገዱ ቅጥ ባያጣ፣ ፍትሕ ባይሰፍን፣ እርቅ ባይወርድ አልነበር እንዴ የሚገርመው? አይደለም ነው? እስከ መቼ ከራሳችን ጋር ተፈራርተን እንዘልቀው ይሆን? አንዳንዴ ወደ ውጭ ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጥ ብንተያይ ምን ይለናል? በንፋስ ዘመን ንፋስ አመጣሽ ነገሮች ላይ ተንጠልጥለን እስከ መቼ እንዘልቀዋለን? ውስጣችንን ማየት ምን ይለናል? ራስን መፈተሽ ምን ይጎዳል? መልካም ሰንበት!