Skip to main content
x

ለተሰጠን ውሳኔ የተግባር ዕርምጃ እንጠብቃለን!

ሁሉም እንደሚያውቀው፣ ለአንድ አገር ሕዝብ ከሚያምነው ፈጣሪ በታች ያሉት ያገሩ መሪና ሥራ አስፈጻሚዎቹ ናቸው። የአመራሩ ብቃት የሚፈተሸውም ባለው የማስፈጸም ችሎታ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ይመስለኛል። በተገቢው ጊዜ ውሳኔ ማስተላለፍ ከብቃቶቹ አንዱ ሲሆን፣ ከዚህ በበለጠ የተወሰነውን ውሳኔ ማስፈጸምና መፈጸሙን መከታተል ዋነኛው የብቃት ማሳያ ናቸው።

ጉዳዩ አገር አቀፍ ችግር የሆነው የአክሰስ ሪል ስቴት ቤት ገዢዎች ሰቆቃ ነው። ሪል ስቴቱ የአፓርትመንቶች ፕላን (Off Plan) በኒያላ ሞተርስ አካባቢ መሸጥ የጀመረው ስምንት ዓመታት በፊት ነው። አከታትሎም በተመሳሳይ መንገድ በተለያዩ ቦታዎች ቪላ ቤቶችና አፓርትመንቶች መቸብቸቡን ቀጠለ። ሪል ስቴቱ ፕላኖቹን ሲሸጥ ቃል የገባው ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ሠርቶ ለማስረከብ ነበር። ታሪኩ ረዥም ነው፡፡ ለማሳጠር ግን፣ ሪል ንስቴቱ እስካሁን ድረስ የሠራው ነገር ቢኖር፣ በኒያላ ሞተርስ አካባቢ በከፊል የተሠሩ ሕንፃዎችና ምናልባትም በአንዳንድ ቦታዎች መሠረት አውጥቶ ካልሆነ በቀር፣ እነሆ ከስምንት ዓመታት በኋላ አንድም ቤት ሳያስረክብ 2,500 በላይ ቤት ገዥዎች ቤት የማግኘት ምኞታቸው የውኃ ሽታ ሆኖ እንዲቀር አድርጓል።

መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር እንዲህ ያለ መጠነ ሰፊ ጥፋት ወይም ወንጀል ሊፈጸም ቻለ? የሚለውን ጥያቄ መተንተን የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም። በዚህ ብሶት ምክንያት የጠፋውን የሰው ሕይወትና የተበተነውን ትዳር ለመዘርዘርም አይደለም።  የዚህ ጽሑፍ ዋና አትኩሮት መንግሥት በወሰነው ውሳኔና አፈጻጸሙ ላይ ነው።

አምስት ዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ 2006 .ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጣልቃ በመግባት ጉዳዩን የሚያጠና ዓብይ ኮሚቴ እንዲቋቋም በማዘዛቸው ኮሚቴው ተቋቁሟል። በማስከተል የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቋመና ሥራውም በሰፊው ጀመረ። ከሁለት ዓመት ረጅም የማጣራት ሥራ በኋላ ቴክኒክ ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት አያይዞ ላከ። በሪፖርቱኮሚቴው የመፍትሔ ሐሳቦችን አመላክቶ መንትግሥት ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠየቀ። ከተጠቀሱት የመፍትሔ ሐሳቦች ዋነኛው፣ ቤት ገዥዎች በልዩ ሁኔታ እንዲደራጁና ሕጋዊ ማኅበር እንዲኖራቸው የሚል ነው።

በመፍትሔ ሐሰቡ መሠረት የንግድ ሚኒስቴር  ለአዲስ አባባ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ሕፈት ቤት፣ የከንቲባው ሕፈት ቤትም ወደ ንግድ ቢሮ ቤት በላኩት መሠረት፣ ቤት ገዥዎቹ በልዩ ሁኔታ በማኅበር እንዲደራጁ አምነውና ወስነው የመሩባቸው ደብዳቤዎች ይጠቀሳሉ። ይሁን እንጂ ቴክኒክ ኮሚቴው ሪፖርቱን ካቀረበ ከአንድ ዓመት በኋላ የተሰጠው የመፍትሔ ሐሳብ ሊፈጸም ስላልቻለ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመፍትሔ ሐሳቡ መሠረት እንዲፈጸም ማሳሰቢያ ለአዲስ አበባ ከንቲባ ሕፈት ቤት የላኩት ደብዳቤም ተጠቃሽ ነው፡፡

ውሳኔ መስጠት፣ ትዕዛዝ ማስተላልፍ አንድ ትልቅ አዎንታዊ ዕርምጃ ሆኖ ሳለ፣  የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ ደብዳቤ አንድ ዓመት አምስት ወር በላይ በኋላ እስካሁን ድረስፈፃሚው አካል ከብሮ ሊፈጸም ባለመቻሉ ወይም ባለመፈለጉ ግን ችግሩ የእንግውል ርግበረድ ጫፍ ይሆን? (Tip of the Iceberg) ያሰኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼንን ትእዛዝ የሰጡትቴክኒክ ኮሚቴውሁለት ዓመት ለፍቶ ያቀረበላችውን የመፍትሔ ሐሳብ መሠረት በማድረግ ነበር። ታዲያ ይህ ውሳኔ ለምን ተፈጻሚነት አይኖረውም? ሌሎች የአገር ጉዳዮች ጠቅላይ ሚኒስትርን በሚያክል ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ደረጃ ውሳኔ ሲሰጣቸው የእንደዚህ ዓይነት ችግር ሰለባ ይሆናሉ ማለት ነው? በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የምናያቸው አለመረጋጋቶች መንስዔዎቻቸው እንደነዚህ ዓይነቱ የፍትሕ ጥያቄዎች ሳይደመጡ ወይም ውሳኔዎቻቸው በአግባቡ ሳይፈጸሙ በመቅረታቸው እንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም።   

መንግሥትነቱን የያዘው የኢሕአዴግ ፓርቲ ጥልቅ ተሃድሶ ላይ እንደሆነ እየገለጸ ነው። ታድሻለሁ ብሎ ሲወጣ መታደሱን የሚያረጋግጥልን ግን በማስፈጸም ብቃቱ ነውና2,500 በላይ ቤት ገዢዎችንና ቤተሰቦቻቸውን ያቀፈ የሕዝብ አካል የተላለፈለትን ውሳኔ ያለ ምንም ቢሮክራሲና ለገምተኝነት በማስፈጸም ሕዝባዊነቱን እንደገና ያንሰራፋዋል ብለን በእጅጉ እንጠብቃለን።

(ከተጎዱት ቤት ገዢዎች አንዱ ነኝ)

***

Image removed.ያለቦታቸው ቦታ የሚሹትን አንድ እንበል!

ለሹመትና ለሽልማት መመዘኛውና መለኪያው አየር ላይ የሚነዛውና መሬት ላይ ወርዶ ግዘፍ ነስቶ በተጨባጭ የምመለመከተው አንድ አልሆንህ አለኝ፡፡ ይኼን ግርታዬን እንደዘበት እንዳላመጣሁት በአስረጅ ላረጋግጥ፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥርና ምርመራ፣ ከውጭ ዕቃ አቅራቢዎች ጋር በተያያዘ አንድ የግል ባንክ በሕግ የተቀመጠውን ተግባሩንና ግዴታውን አልተወጣም ተብሎ ክስ እንደቀረበበትና ብሔራዊ ባንክም አስደንጋጭ ዕርምጃ እንደወሰደበት ይታወሳል፡፡ የዚህ ዕርምጃ ቀዳሚ ሰለባዎች የባንኩ ሁለት ፕሬዚዳንቶችና የባንኩ ቦርድ ሊቀመንበር፣ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርገዋል፡፡ ፍትሕ ለሚሻ ሕዝብ ውሳኔው ይበል የሚያሰኝ ነበር፡፡ ከኃላፊነታቸው ታገዱ የተባሉት ፕሬዚዳንት የሠሩት በደል የማክሮ ኢኮኖሚ ምዝበራና ጥፋት ሆኖ ሳለ፤ እንዲያውም ጥፋቱ ተሠራ የተባለው እዚህ አገር ውስጥ ሆኖ እንጂ እንደ ቻይና ባሉት አገሮች ውስጥ ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ በጠራራ ጸሐይ የሚያሰቅል በደል ነው በማለት ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል ታገዱ የተባሉት ፕሬዚዳንት ትንፋሻቸውን የሚስቡበት ጊዜ ተሰጣቸው መሰል፣ ከፌዴራል ሥርዓት ውጭ በሆነ አግባብ የክልል ባለሥልጣንና የካቢኔ አባል ሆነው እንዲሰነብቱ ተደረገ፡፡

በዚህ ስንደነቅ ቆይተን ሳለ ሳይታሰብ የፌደራል መንግሥት ተቋም በሆነው ድርጅት ውስጥ ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ኮፍያ ቀይረው ተከሰቱ፡፡ ይኼንን በማሰላሰል ላይ ሳለሁ ሌላ አራምባና ቆቦ የረገጠ ሁኔታ ፊቴ ድቅን አለ፡፡ ጉዳዩ  የሰሞኑ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን መሪዎች ምርጫን አስመልክቶ ነው፡፡ በምርጫው ሁለት ዝሆኖች ጎልተው በአሸናፊነት ለመውጣት ሲታገሉ ይታያል፡፡

ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስና አቶ ተካ አስፋው፡፡ በቅርቡም ዶ/ር አሸብር ልምዳቸውን አንተርሰው ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ያላቸውን ራዕይና ህልም በሩቁም ቢሆን ሲጠቁሙ ከአንድ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ሆኖም ሰው ባገር ጠፋ እንዴ? ለማለት ያበቃኝ አንድ ግር የሚያሰኝ ነገር አለ፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያን እግር ኳስ አንድ ዕርምጃ ፈቀቅ ለማድረግ የሚችሉ፣ የተቀቡ ብፁዓን እነርሱ ብቻ ናቸው ወይ? ለማለትም ተገድጃለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ይብዛም ይነስም በፌዴሬሽኑ ውስጥ ተመርጠው የማገልገል ዕድል ከዚህ በፊት አግኝተዋል፡፡ ሆኖም ያመጡት ለውጥ አልነበረም፡፡ ይኼንን ቁጭቴን ማንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተቆርቋሪ እንደሚጋራኝ አምናለሁ፡፡

የአገሪቱን የእግር ኳስ ልምራ ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ እገረማለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ግለሰቦች በማይመጥናቸው ቦታ ተቀምጠው ውጤት አለማምጣቸውና እንዲያው ቀድሞ የነበረውን ደረጃ እንኳ ለመጠበቅ ቢያቅታቸው ምን ይደንቃል? የሚለውን ለማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለራሳቸው እንጂ ለተቀመጡበት ኃላፊነት እንደማይመጥኑ እንደሆነ ተረድተን በጊዜ ገለል ማድረግ ካልቻልን፣ የምንጠብቀውን ለውጥ ማግኘት አንችልም፡፡ በተለይም ብቸኛ የሆነውን የወጣቶቻችንም ሆነ የብዙዎችን ዕድሜ ያካተተ መዝናኛ እግር ኳሳችን ላይ ለውጥ እንዲመጣና እንዲያድግ ከተፈለገ፣ ከእንደዚህ ዓይነት አመራሮች እንዲፀዳ ማድረግ እንደሚገባን የበኩሌን ሐሳብ ለመስጠት እወዳለሁ፡፡

(ከታዛቢ)