Skip to main content
x
የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በአንድ ዓመት እንዲራዘም ተጠየቀ

የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በአንድ ዓመት እንዲራዘም ተጠየቀ

ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በየካቲት ወር ሊደረግ የነበረውን አራተኛውን የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ለሚቀጥለው ዓመት እንዲተላለፍለት ጥያቄ አቀረበ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት በአገሪቱ በተፈጠረው አለመረጋጋት፣ በተለይም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች  ባጋጠመው ግጭት ምክንያት በርካታ ዜጎች በመፈናቀላቸው ምክንያት ቆጠራውን በዚህ ዓመት ማድረግ እንደማይቻል፣ የኤጀንሲው ኃላፊዎች እምነት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዓርብ ታኅሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ረፋዱ ላይ የኤጀንሲው ኃላፊዎች በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን ከሚመራው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ኮሚሽን ጋር ስብሰባ ተቀምጠው እንደነበር ታውቋል፡፡ በወቅቱም ቆጠራውን ለሚቀጥለው ዓመት የማራዘሙ ሐሳብ አጀንዳ ሆኖ ቀርቦ እንደነበር፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመንግሥት ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በስብሰባው የኤጀንሲው ኃላፊዎች የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽኑ ቆጠራውን የማራዘም ሥልጣን እንደሌለው፣ ጉዳዩ ለፓርላማ ቀርቦ መፅደቅ እንዳለበት እንደ ተነገረው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጉዳዩ በሳምንት ውስጥ ተጠናቆ ለፓርላማው ለውሳኔ እንዲቀርብ በስብሰባው መወሰኑ ታውቋል፡፡

ለቆጠራው መራዘም በዋናነት በሁለቱ ክልሎች የተፈጠረው የዜጎች መፈናቀል መሆኑን፣ በዚህም ሁኔታ ቆጠራውን ማከናወን የቆጠራውን ውጤት ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ሊከት እንደሚችል፣ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አንድ የኤጀንሲው ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም አራተኛው የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ በኅዳር ወር 2010 ዓ.ም. እንዲደረግ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም፣ ለቆጠራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በዋናነት ታብሌት ኮምፒዩተሮች ፓወር ባንኮች ግዥ በታቀደው ጊዜ ቀድሞ ባለመከናወኑ ምክንያት፣ ቆጠራው ለየካቲት ወር 2010 ዓ.ም. መተላለፉ ይታወሳል፡፡

ለየካቲት ወር ቆጠራም ኤጀንሲው አብዛኞዎቹን የዝግጅት ሥራዎቹን አጠናቆ፣ ለቆጠራው በሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ መረከቡ ይታወሳል፡፡ የቆጠራው ዝግጅት እንደተገባደደ የሚታመነው ዘጠኝ ሺሕ ከተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተውጣጡ በቆጠራው የሚሳተፉ ግለሰቦች ከሠለጠኑ በኋላ ነበር፡፡ አሥር  ቀናት ይጠይቅ የነበረው ሥልጠና ባለፈው ሳምንት መጀመር የነበረበት ቢሆንም፣ በኤጀንሲው ትዕዛዝ እንዲቆም መደረጉ ታውቋል፡፡

ወደ 3.5 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለት ሊከናወን የታቀደው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ሁሉንም የአገሪቱን ክልሎች የሚያካልል ነው፡፡ በኤጀንሲው የቀረበው የጊዜ ማራዘሚያ ጥያቄ በፓርላማ ተቀባይነት ካገኘ ቆጠራው በኅዳር 2011 ዓ.ም. ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡