Skip to main content
x
ነጋዴዎች ሰዓት አልፏል በሚል ሰበብ ፈቃድ ከማሳደስ እንደታገዱ ገለጹ

ነጋዴዎች ሰዓት አልፏል በሚል ሰበብ ፈቃድ ከማሳደስ እንደታገዱ ገለጹ

  • የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ ነጋዴዎቹ ባሰሙት አቤቱታ መሠረት እንዲታደስላቸው አዘዋል

በመቶዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነጋዴዎች፣ የታኅሳስ ወር ማብቂያ ማለትም ታኅሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ዓመታዊ የንግድ ፈቃድ ዕድሳት አገልግሎት ለማግኘት ማልደው በንግድ ሚኒስቴር ሕንፃ ቢገኙም፣ በንግድ ፈቃድ ዕድሳትና ምዝገባ ኃላፊዎች ‹‹የሥራ ሰዓት አልፏል፤›› በማለት በፖሊስ ጭምር እንዳባረሯቸው ገለጹ፡፡

የንግድ ፈቃድ ለማሳደስ በሕጉ መሠረት የስድስት ወራት ጊዜ ቢሰጥም፣ በርካታ ነጋዴዎች በመጨረሻዎቹ ቀናት በብዛት እየመጡ አገልግሎቱ ላይ መጨናነቅ ሲፈጠር ይታያል ያሉት የንግድ ሚኒስቴር ኃላፊዎች፣ በዚህ ሳቢያ ታኅሳስ 30 ቀን አመሻሹ ላይ በሚኒስቴሩ ፈቃዳቸውን ለማሳደስ ሲጠባበቁ የነበሩ ከ300 በላይ ነጋዴዎች አገልግሎቱን ሳያገኙ ማሰናበታቸውን ቅሬታ አስነስቶባቸዋል፡፡ በርካታ ነጋዴዎች ከታክስ ዕዳ፣ ከቤት ኪራይ ውልና ከሌሎችም ችግሮች ጋር በተያያዘ በተፈቀደው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማሳደስ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነጋዴዎች ገልጸዋል፡፡

ይህንን ተከትሎም ማክሰኞ፣ ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በርካታ ቅሬታ ያሰሙ ነጋዴዎች፣ ካዛንቺስ የቀድሞው ሱፐርማርኬት አካባቢ በሚገኘው የሚኒስቴሩ ጽሕፈት ቤት በመገኘት ችግራቸውን አሰምተዋል፡፡ ያለቅጣት እንዲስተናገዱና የደረሰባቸውን እንግልት በማብራራት ጭምር ለሚኒስትር ዴኤታው አቶ አሰድ ዛይድ ሲያስረዱ ሪፖርተር ታዝቧል፡፡ ለሰዓታት ሲያጣሩ፣ ነጋዴዎቹ የወከሏቸውን ግለሰቦችና የበታች ኃላፊዎችን በየተራ ሲያነጋግሩ የቆዩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከ240 ያላነሱ ነጋዴዎች የምግዝባና የፈቃድ ዕድሳት መዝጊያው ቀን ከመጠናቀቁ በፊት በሚኒስቴሩ ለመስተናገድ ስለመቅረባቸው ማረጋገጫ የነበራቸውና የስም ዝርዝራቸው የተመዘገቡ ነጋዴዎች ያለቅጣት እንዲስተናገዱ ትዕዛዝ ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡

‹‹በዕለቱ (ታኅሳስ 30 ቀን) ብቻ የነበረና የተመዘገበ ሰው ብቻ ነው የምንፈልገው፡፡ ለስድስት ወራት በሚዲያ ጭምር እየገለጽን ስንጠብቃችሁ ቆይተናል፡፡ ሆኖም አሁን በተፈጠረው ሁኔታ መስፈርቱን የሚያሟላ ብቻ ያለቅጣት ይታደስለታል፤›› ያሉት አቶ አሰድ፣ ነጋዴዎቹ የንግድ ፈቃዳቸውን በመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ አስቀምጠው እንዲሄዱና ለአገልግሎት የሚፈለግባቸውን 102 ብር አዘጋጅተው በማግስቱ ማለትም ጥር 2 ቀን 2010 እንዲመለሱ በማሳሰብ ነጋዴዎቹን አሰናብተዋል፡፡

ምንም እንኳ ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ቢሉም፣ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ቅርንጫፍ አንድ ጽሕፈት ቤትን የሚመሩት አቶ ጅራታ ነመራና ሌሎችም ባልደረቦቻቸው ነጋዴዎቹ የንግድ ፈቃዳቸውን ይዘው ወደየቤታቸው እንዲሄዱ ነግረዋቸዋል፡፡ ምክንያታቸውም ለአሠራር አይመችም፣ እንዲህ ባለው አሠራር ለመስተናገድ የሚያስችል አሠራር ባለመኖሩ ቃለ ጉባዔ መያዝ እንዳለበት በማብራራት ነጋዴዎቹ ጥር 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ንግድ ፈቃዳቸውን ይዘው እንዲመለሱ በመግለጽ ሸኝተዋቸዋል፡፡

የንግድ ፈቃድ በወቅቱ አለማሳደስ 2,500 ብር እንደሚያስቀጣ የሚኒስትሩ አዋጅ ይደነግጋል፡፡ ከአንድ በላይ የንግድ ፈቃድ ያላቸው ነጋዴዎች በያዙት የንግድ ፈቃድ ብዛት መቀጫው ይጣልባቸዋል፡፡ በመሆኑም በትንሹ አራት የንግድ ፈቃድ ያለው ነጋዴ እስከ 10 ሺሕ ብር መቀጫ ይጣልበታል ማለት ነው፡፡ ይህንን ቅጣት ሽሽት በርካቶች ባለቀ ሰዓትም ቢሆን በሚኒስቴሩ የፈቃድ ዕድሳት አገልግሎት ለማግኘት የሚረባረቡት፡፡

ባለፈው ዓመት በነበረው የዕድሳት ሒደት ከ50 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች በወቅቱ ባለማሳደሳቸው ምክንያት በተጣለባቸው መቀጮ፣ መንግሥት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እስካሁን ካለው አካሄድም በሺዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን በወቅቱ ማሳደስ ባለመቻላቸው የዕድሳት ጊዜው ሲራዘም መቆየቱ የተለመደ ነበር፡፡