Skip to main content
x
ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ቅርሶችን በተሻለ ለማስጠበቅ የሚረዳ ሕግ እያረቀቀ እንደሚገኝ አስታወቀ

ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ቅርሶችን በተሻለ ለማስጠበቅ የሚረዳ ሕግ እያረቀቀ እንደሚገኝ አስታወቀ

  • በመጪው ዓመት እንደሚተገበር ለሚጠበቀው የሆቴሎች ምደባ ክልሎችን ማወያየት ጀምሯል

በአገሪቱ የሚገኙ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ የተፈጥሮና ሌሎችም ቅርሶችን በተሻለ ክብካቤና በባለቤትነት ስሜት ለማስጠበቅ ያግዛል ያለውን የሕግ ረቂቅ ማዘጋጀት እንደጀመረ ያስታወቀው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በቅርስ መዳረሻዎች አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ከሚገኘው ገቢ እስከ 30 በመቶ እንዲደርሳቸው ማቀዱን ይፋ አድርጓል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ መዓዛ ገብረ መድኅን በተለይ ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ ምልልስ ወቅት እንዳብራሩት፣ የአገሪቱን ውድ ቅርሶች በባለቤትነት ስሜት ለማስጠበቅ ከሚረዱ መንገዶች አንዱ ሕዝቡ ከአባቢው ካለው የቱሪዝም ሀብት ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡

ሚኒስቴሩ ይህን በማሰብ እየወሰዳቸው ከሚገኙ ዕርምጃዎች መካከል ዘርፉ የሚመራባቸውን ሕጎች በማሻሻልና የተለያዩ የሥራ ዘርፎችን በማቀናጀት ለማስኬድ የሚረዱ የሕግ ማዕቀፎችን እያረቀቀ ይገኛል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ የዱር እንስሳት ጥበቃ ማቋቋሚያ አዋጅንና የቱሪዝም ፈንድ አዋጆችን እያረቀቀ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ በጠቅላላው የቱሪዝም አጠቃላይ ማዕቀፍ የሚኖረው አዋጅ በቅርቡ ተጠናቆ ለሕግ አውጪው አካል እንደሚላክ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሕጎቹ መውጣት በሚኒስቴሩና የቱሪስት መዳረሻዎች በብዛት በሚገኙባቸው በአማራ፣  በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋርና በደቡብ ክልሎች መካከል የሚታየውን የመናበብ ችግር ሊቀርፍ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ በመሆኑም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እየተረቀቁ የሚገኙት አዋጆች የሚታዩትን ያለመናበብ ችግሮች ከመፍታት ባሻገር፣ በቱሪስት መዳረሻዎች አካባቢዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ከሚገኘው የዘርፉ ገቢ እስከ 30 በመቶ እንዲደርሳቸው ለማድረግ መታቀዱን ወይዘሮ መዓዛ አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስቴሩ አገሪቱን የማስተዋወቅና የግብይት ሥራዎችን ጨምሮ፣ የቱሪስት መስህቦችን የመለየት፣ የመዳረሻ ቦታዎችን የማልማት፣ የሰው ኃይል አቅምን የመገንባት፣ የዱር እንስሳት ልማትና ፓርኮችን የመጠበቅ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ያብራሩት ወይዘሮ መዓዛ፣ እነዚህንና ሌሎችም ተጓዳኝ ሥራዎችን ለማከናወን የሚረዱ የቱሪዝም ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ እንዲሁም የአሥር ዓመት ማስተር ፕላን ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራ የቱሪዝም ትራንስፎርሜንሽን ምክር ቤትም ለዘርፉ የተሰየመ የበላይ አካል ነው፡፡ የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ ሚኒስቴሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም የዘርፉ ተዋናዮች በየመንፈቁ እየተሰበሰቡ ስለቱሪዝም ዘርፉ የሚመክሩበት አደረጃጀት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሩት ሦስተኛው የምክር ቤቱ ስብሰባ ወቅት በአገሪቱ በሚከሰቱ ሰው ሠራሽ ችግሮችና ግጭቶች፣ እንዲሁም ሕገወጥ ሰፋሪዎች ጫና ምክንያት ሊጠፉ የተቃረቡና አደጋ ውስጥ የወደቁ ፓርኮችን በማስመልከት ሲናገሩ፣ ‹‹መጪው ትውልድ ተጠያቂ የሚያደርገን ጥፋት እየተፈጸመ ነው፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ይህም ሆኖ አገሪቱ በርካታ ያልተነኩና ገና ያልታወቁ የቱሪዝም ሀብቶች እንዳሏት ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በቅርብ ጊዜ ከተለዩት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከወንጪ ሐይቅ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በስምንት ቁጥር ተፈጥሯዊ ቅርፅ ልዩ አቀማመጥ ያለው ዳንዲ የተሰኘው ሐይቅ ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በመቱ ከተማ የሚገኘው ሶር ፏፏቴም፣ ከጭስ ዓባይ ቀጥሎ ሊጠቀስ የሚችል ትልቅ የተፈጥሮ ቦታ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በጋምቤላ ክልል የሚገኘው የማጃንግ የደን ሀብትም በባዮሴፍቲ ጥበቃ ሥር የተመዘገበ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት እንደሆነም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

እንዲህ ያሉ የቱሪስት መስህቦችን ከመለየት ባሻገር፣ የአገሪቱን ሀብቶች በአግባቡ የሚያስተዋውቁና በአገልግሎት ዘርፍ የሚሠማሩ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሰው ኃይል ማሠልጠን የሚኒስቴሩና የሚመለከታቸው አካላት ትልቅ የቤት ሥራ መሆኑን ሲያብራሩም፣ በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል 23 በመቶ ብቻ በመሆኑ ሰፊ ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን በአገሪቱ የተጀመረው የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ በሚቀጥለው ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ እንዲካሄድ ለማድረግ ከሆቴል ባለቤቶች ጋር ውይይት ተጀምሯል፡፡ በአዲስ አበባ ከሦስት ሳምንት በፊት የተካሄደው ውይይት ወደ ክልሎች አምርቶ፣ በባህር ዳር ከተማም ተመሳሳይ ውይይት ተደርጓል፡፡ ወደ ሌሎቹም ክልሎች እንደሚዳረስ የተገለጸው የደረጃ ምደባውን የተመለከተው ውይይት፣ ከአሁን በፊት በተደረገው ምደባ የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ለኮከብ ደረጃ ምደባው ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ሎጆችና ሪዞርቶች ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች እንዲገነዘቡ፣ ሚኒስቴሩ የሚያሰማራቸው መዛኞችም ማሟላት የሚገባቸው የሙያና የሥነ ምግባር ደረጃም በውይይቶቹ ወቅት ትኩረት ያገኙ ነጥቦች ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት 50 ባለሙያዎች ሆቴሎችን ለመመደብ የሚያስችል ሥልጠና በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ሙያተኞች ወስደውና ተፈትነው የኮከብ ደረጃ ለመስጠት ብቁ መሆናቸው መረጋገጡን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረገው ምዘና 365 ሆቴሎች ተካተው፣ ከእነዚህ ውስጥ ደረጃቸው ይፋ የተደረጉት 167 ያህሉ ሲሆኑ፣ የተቀሩት ለምዘና ማሟላት የሚገባቸውን አስገዳጅ መስፈርቶች ባለማሟላቸውና በተለያዩ ምክንያቶች ደረጃ ማግኘት እንዳልቻሉ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተመዘኑት ውስጥ 80 ሆቴሎች ለኮከብ ደረጃ ብቁ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ስድስት ባለአምስት ኮከብ፣ 15 ባለአራት፣ ሒልተንን ጨምሮ 28 ሆቴሎች ባለሦስት፣ 22 ባለሁለት ኮከብ፣ እንዲሁም ዘጠኝ ባለአንድ ኮከብ ሆቴሎች በአዲስ አበባ እንደሚገኙ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ያስመዘገበው የኦሮሚያ ክልል አንድ ሆቴል ብቻ ይህንን ደረጃ እንዳገኘ ይፋ ማደረጉ ይታወቃል፡፡