Skip to main content
x
አደገኛ ጨረራዎች

አደገኛ ጨረራዎች

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአሜሪካና በሩቅ ምሥራቋ ጃፓን መካከል የነበረው ግጭት የጦርነትን አስከፊ ገፅታ ያሳየና በአገራት መካከል እስከዛሬ ከተካሄዱ ጦርነቶች አሰቃቂ ክስተት የተመዘገበበት ነበር፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ጦርነት መስመሩን የሳተው እ.ኤ.አ. ሐምሌ 30 ቀን 1945 ላይ ‹‹ሊትል ቦይ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው አቶሚክ ቦንብ በአሜሪካ ቦንብ ጣይ አውሮፕላን በሂሮሺማ ከተማ ላይ ሲጣል ነበር፡፡

ፍንዳታው 90 በመቶ የከተማዋን ገፅታ እንዳልነበር አድርጎ በቅፅበት ውስጥ ወደ ዶግ አመድነት የቀየረ፣ 80 ሺህ የሚሆኑ የከተማዋን ነዋሪዎችም እንደ ቅጠል ያረገፈው በአፍታ ጊዜ ውሰጥ ነበር፡፡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ፍንዳታው በፈጠረው ጨረር በሰዓታት ውስጥ አልቀዋል፡፡

‹‹ወደ ሂሮሺማ ፊታችንን አዞርን፡፡ ከተማዋ በዚያ በሚቀፍ ደመና ተውጣለች፡፡ ደመናው ከምንም ተነስቶ ወደ ላይ የሚወረወርበት ፍጥነት የሚያስፈራ ነበር፡፡ ሁላችንም በድንጋጤ ተወጡን ለአፍታ ያህል ፀጥ ብለን ስንመለከተው ቆየን፡፡ ከዚያም መንጫጫት ጀመርን፡፡ አስታውሳለሁ አብሮን የነበረው ረዳት አብራሪ ትከሻዬን እየመታ ተመልከት፣ ተመልከት ይለኝ ነበር፤›› ያለው ቦንብ ጣይ አውሮፕላኗን ሲያበር የነበረውና እ.ኤ.አ በ2007 ያረፈው ፖል ቲቤትስ ፍንዳታው በአፍታ ጊዜ ውስጥ ወደ ገሃነምነት የቀየራትን ሂሮሺማ ከላይ ሆኖ የታዘበውን ሲያስታውስ ነበር፡፡

ይህ አሰቃቂ ድርጊት በተፈጸመ ከሦስት ቀናት በኋላ በሌላኛዋ የጃፓን ከተማ ናጋሳኪ ላይ ሁለተኛ አቶሚክ ቦንብ ተጣለ፡፡ ቦንቡ በፈነዳበት ቅፅበት ውስጥ 40ሺህ ጃፓናውያንን ጨረሰ፡፡ የወቅቱ የጃፓኑ ንጉስ ሂሮሂቶም በሁኔታው ክፉኛ ተደናግጠው አገራቸው መማረኳን በራዲዮ መልዕክት አስተላለፉ፡፡ ለ280ሺህ ዜጎች መኖሪያ የነበረችው ሂሮሺማ በፍንዳታውና ፍንዳታው በፈጠረው አካባቢያዊ ቀውስ 237,000 ዜጎቿን አጥታለች፡፡ በነጋሳኪ የሞቱ ዜጎች አጠቃላይ ቁጥርም 80ሺህ ደርሷል፡፡

በታሪክ አሰቃቂ ከሚባሉ የጦር ውሎዎች በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው የሂሮሺማና ነጋሳኪ አደጋ ከተከሰተ 73 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በከተሞቹ የፈነዳው ኦቶሚክ ቦምብ በነዋሪዎቹ ያደረሰው አደጋ በዘር የሚተላለፍ የአሁኑን ትውልድ ሳይቀር በተለያየ መንገድ ለጤና ችግሮች እየዳረገ ያለ ነው፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት መሰል ጅምላ ጨራሽ ቦምቦች የሚቀመሙት ከፍተኛ ጉልበት ካላቸው ጨረሮች መሆኑ ነው፡፡

ጨረራ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ በሞገድ ወይም በቅንጣት መልክ የሚጓዝ ኃይል ነው፡፡ አዮን ፈጣሪና አዮን የማይፈጥር በሚልም በሁለት ምድብ ይከፈላል፡፡ አዮን ፈጣሪ የሆኑ ጨረራዎች በሰዎች ሰውነት አልያም በቁስ ውስጥ በሚያልፉበት ጊዜ ኤሌክትሮን በማውጣት የቻርጅ ልዩነት በማምጣት አዮን እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡

አዮን ፈጣሪ ጨረራዎች የሚባሉት አልፋ፣ ቤታ፣ ጋማ፣ ኤክስሬይ፣ ኒውትሮን  ሲሆኑ፣ እያንዳንዳቸው በአንድ ቁስ አካል ውስጥ ሰንጥቆ የመግባት አቅማቸውና ከገቡም በኋላ የሚፈጥሩት የአዮን ልዩነት ለየቅል ነው፡፡ የአልፋ ጨረራ ጠንካራ አቅም የሌለውና በወረቀት ሊገደብ የሚችል ነው፡፡ ቤታ የሚባለው ደግሞ ወረቀትን ሰንጥቆ የመሄድ ጉልበት ቢኖረውም በአልሙኒየም የሚገደብ ነው፡፡ ጋማ የሚባለው ጨረራ ግን ኃይሉ እየተዳከመ የሚሄድ ቢሆንም ማንኛውንም ቁስ ሰንጥቆ የመሄድ አቅም አለው፡፡ ነገር ግን እንደ ሊድ ባሉና ውፍረት ባላቸው ብረት ነክ ነገሮች ተውጦ ይቀራል፡፡ ኤክስሬይም በተመሳሳይ ማንኛውንም ቁስ ሰንጥቆ የመሄድ ጉልበት ቢኖረውም ወፍራም ተደርጎ በተሠራ ሊድ ውስጥ አብዛኛው ጉልበቱ ሊታመቅ ይችላል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ኒውትሮን ከሌሎቹ በተለየ ማንኛውንም ዓይነት ቁስ ሰንጥቆ የማለፍ አቅም ያለው ሲሆን፣ የሚያቆመው ነገር ቢኖር ከውኃ የተሠራ ወፍራም ኮንክሪት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

አዮን ፈጣሪ ያልሆኑ የጨረራ ዓይነቶች ደግሞ አዮን የመፍጠር አቅም የሌላቸውና ለጨረራው በተጋለጠው ቁስ አካል ላይ ሙቀት፣ መጠነኛ የኤሌክትሪክ ጅረት መፍጠር የሚችሉ ናቸው፡፡ የሚፈጥሩት የሙቀት መጠን ከፍተኛ ከሆነ ህዋሳትን የመግደል አቅም አላቸው፡፡ በዚህም በሰው ልጆች ላይ እስከ ሞት የሚያደርስ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡

 አዮን ፈጣሪ ለሆኑ ጨረራዎች አላግባብ መጋለጥ በሰዎችና በአካባቢ ጤና ላይ እንዲሁም በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡ አዮን ፈጣሪ ጨረራዎች በአይን የማይታዩ፣ በማንኛውም የስሜት ሕዋሳት የማይለዩ ሲሆኑ፣ በዙሪያችን መኖራቸውን ሳናውቀው ለጨረራዎቹ ልንጋለጥ እንችላለን፡፡

እነዚህ ጨረራዎች በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ መንገድ ይከሰታሉ፡፡ በአፈር፣ በውኃ፣ በተፈጥሮ ጋዝ፣ በምልዓተ ዓለም (Cosmic)፣ በትምባሆ፣ በሥልክ፣ በኮምፒዩተር፣ በኤክስሬይ (ሜዲካል ኢሜጂንግ) በመሳሰሉት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለተፈጥሮ ጨረራዎች የመጋለጥ ሁኔታ ከቦታ ቦታ የተለያዩ ቢሆንም አንድ ሰው በአማካይ ለ2.4 ኤምኤስቪ (ወደ ውስጥ የሚገባ ጨረራ ምጣኔ መለኪያ) በተፈጥሮ መንገድ በዓመት እንደሚጋለጥ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ይህም በደረት አካባቢ በሚታዘዝ አንድ ራጅ (Chest Radio Graphy) ወቅት ከሚለቀቅ ጨረር በስድስት እጥፍ የሚበልጥ ነው፡፡

ጨረራ በተለያዩ ዘርፎች ልዩ ልዩ ጥቅም የሚሰጥና ለአንድ አገር ብልፅግና ትልቅ ሚና የሚጫወትም ነው፡፡ የኤሌለክትሪክ ኃይል ማመንጫ በመሆን ያገለግላል፡፡ ያደጉት አገሮች የኑክሌር ኃይል ማብላያ ጣቢያ በመገንባትና ከፍተኛ የኑክሌር ኃይል በማምረት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በማግኘት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ ከ450 በላይ የኑክሌር ማብላያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በአማካይ 391,915 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጩ ይነገራል፡፡

በጤናው ዘርፍም የጨረራ አመንጪ ቁሶችንና መሣሪያዎችን በመጠቀም በሽታን ለመመርመርና ለማከም በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ የካንሰር በሽታን ጨምሮ የተለያዩ የውስጥ ደዌ ሕክምናዎች በጨረራም ይሰጣሉ፡፡ በአደጋ የሚያጋጥም የአጥንት ስብራት፣ ጠለቅ ያለ ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ውስብስብ የጤና ችግሮችና የመሳሰሉት ማንኛውንም ቁስ ሰንጥቀው ወደ ውስጥ መግባት በሚችሉ የኤክስሬይ ጨረራዎችን በመልቀቅ ይካሄዳሉ፡፡ የጨረራ ሕክምናዎች የሕክምናውን ሳይንስ አንድ ዕርምጃ ያስኬዱ የዘመኑ ቴክኖሎልዎች ናቸው፡፡ የጥርስ ራጅ፣ ሲት ስካን፣ ማሞግራፊ፣ ፍሎሮስኮፒ፣ ኢንተርቬንሽናል ራዲዮሎጂና የመሳሰሉት ደግሞ የጨረራ ሕክምናን መሰረት አድርገው የሚሰጡ  የጨረራ ህክምና ትሩፋቶች ናቸው፡፡

እነዚህ ጨረራን መሠረት ያደረጉ ሕክምናዎች ለሕሙማን ፈውስን ለመስጠት ወደር ያልተገኘላቸው ቢሆኑም፣ የዚያኑ ያህል አደገኛ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከፍተኛ የጨረራ ምንጭ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ የሆነውን ትምባሆ የሚያጨስ አንድ ሰው በዓመት 1300 Millirem (ወደ ውስጥ የሚገባ አንድ የጨረራ ምጣኔ መለኪያ) ጨረራ ወደ ውስጥ ያስገባል፡፡ በኤክስሬይ ወቅት ደግሞ በታካሚው ላይ እንደ ሕክምናው ዓይነት በአንዴ ከአሥር እስከ 1000 Millirem ጨረር ይለቀቃል፡፡

ይህም የኤክስሬይ ሕክምና አደገኛ እንዲሆን የሚያደርገው ሲሆን፣ በአንዴ የሚለቀቀው የጨረራ መጠን ዘረመልን የመለወጥና ለተለያዩ የጤና ችግሮች የመዳረግ አቅም እንዲኖረው አድርጎታል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትም የኤክስሬይ ሕክምናን የካንሰር በሽታ አማጭ ከሆኑ ነገሮች መካከል መድቦታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 ሜዲካል ኒውስ ቱዴይ የተባለው ተቋም የሲቲ ስካን ምርመራ 0.4 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያንን ለካንሰር በሽታ እንዲጋለጡ እያደረገ እንደሚገኝ በድረ ገፁ አስነብቧል፡፡

በጨረራ መከላከያ ባለስልጣን አዮን ፈጣሪ ያልሆኑ ጨረራ አመንጪ ተግባራት ተቆጣጣሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ታደለ ነጋሽ፣ ጨረራ በተለያዩ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በመንገድና ግድብ ግንባታና በመሳሰሉት ዘርፎች ጥቅም ላይ የሚውል ቢሆንም በኢትዮጵያ በስፋት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው በሕክምናው ዘርፍ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ኤክስሬይ በሰዎች ላይ የአጭርና የረዥም ጊዜ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ በአጭር ጊዜ ተፅዕኖው የቆዳ መለብለብ፣ መቁሰል፣ መጥቆር፣ የጣት መቆረጥና ሌሎችም እስከ ሞት የሚያደርሱ አካላዊ ጉዳቶች ሊያስከትል ይችላል፡፡ በረዥም ጊዜ ተፅዕኖው ደግሞ የካንሰር በሽታ ሊያስከትል፣ አልያም ዘረመልን በማዛባት ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የጤና እክል ሊያስከትል ይችላል፡፡

በተለያዩ የግል ሆስፒታሎች በራዲዮግራፈርነት የሚሠሩት አቶ ካሱ ገብሬ እንደሚሉት፣ አንድ ታማሚ ወደ ኤክስሬይ ሲላክ ለደረት፣ ለራስ ቅል አልያም ሌሎች የአካል ክፍሎችን በሌሎች የህክምና ዘዴዎች ችግሩን ማወቅ ካልተቻለ ነው፡፡ በእነዚህ የአካል ክፍሎች ላይ የሚለቀቀው የጨረራ መጠን እንደየአካል ክፍሉ፣ እንደታማሚው ዕድሜና የሰውነት ክብደት የተለያየ ይሆናል፡፡ ለአዋቂና ለሕፃናት የሚለቀቀው የጨረራ መጠን የተወሰነ ልዩነት እንዲኖረው የሚመረጥ ቢሆንም ሕፃኑ ክብደቱ ከአዋቂ እኩል በሚሆንበት ጊዜ የሚለቀቀው የጨረራ መጠንም በዚሁ መጠን ይሆናል፡፡

እንደ አቶ ካሱ ያሉ ራዲዮግራፈሮች በሊድ ወይም በወፍራም መስታወት ከተለበደው ክፍል በስተጀርባ ሆነው የታካሚውን አካል ኤክስሬይ ሲያነሱ ከሊድ የተሠራውን ‹‹ኤፕረም›› ለብሰው ነው፡፡ ታማሚውም በመራቢያ አካሉ ላይ የጨረራ መከላከያ እንዲለብስ ይደረጋል፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ጨረራው በመራቢያ አካላት ላይ ጉዳይ እንዳያደርስ ለመከላከል ነው፡፡

በመራቢያ አካላት ላይ የሚያጋጥም የጨረራ ተጋላጭነት ዘረመልን በመለወጥ በዘር የሚተላለፉ የጤና ችግሮች ሊያስከትል፣ አልያም መካን ሊያደርግ እንደሚችል በዚህ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ለዚህም የመራቢያ አካላት የሚሸፈንበት ‹‹ጐናድ ሽልድ›› ሕመምተኛው ከእምብርቱ በታች ሊታጠቅ ግድ እንደሚል በቅዱስ ያሬድ ሆስፒታል የኳሊቲ አሸራንስ ማኔጀሩ አቶ አዝማች በጅጉ ይናገራሉ፡፡ ባገለገሉባቸው በአንዳንድ የጤና ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎች በቸልተኝነት ሕመምተኛው ጐናድ ሽልዱን ሳይታጠቅ ወደ ኤክስሬይ ክፍል እንደሚያስገቡት መታዘባቸውንም ይገልፃሉ፡፡

‹‹ኤክስሬይ በታማሚው ላይ ሊያሳድር የሚችለውን የጤና ችግር ለመቀነስ አንድ ሰው በ24 ሰዓታት ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ ለጨረራ መጋለጥ የለበትም የሚል ሕግ አለ፤›› የሚሉት አቶ አዝማች፣ አልፎ አልፎ በባለሙያ ስህተት ታካሚዎች በቀን ሁለት ጊዜ ለጨረራ የሚጋለጡባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹ለሰባት ዓመታት ያህል በዚህ ሙያ ስሠራ ያጋጠመኝና ይገጥመኛል ብዬ የምሠጋው ነገር የለም፡፡ ምን ያህል ለጨረራ መጋለጣችንን የሚለካውና አንገታችን ላይ የምናንጠለጥለው ‹‹ቲኤልዲ›› የተባው መሣሪያም እስካሁን አላግባብ ለጨረራ መጋለጤን የሚያሳይ ልኬት አልመዘገበም፤›› የሚሉት አቶ ካሱ፣ ከሌላው ማኅበረሰብ በተለየ ለጨረራ የቀረቡ ቢሆንም፣ የሚደረገው ጥንቃቄ እስካልጎደለ ድረስ ሊያጋጥም የሚችል የከፋ ችግር አለመኖሩን ይናገራሉ፡፡ ዋናው ነገር ባለሙያው የሚቆምበት ክፍልና ጨረራው የሚለቀቅበት ክፍል ጨረራ የማያስተላፍ መሆኑ ላይ ነው፡፡

እንደ አቶ አዝማች የጤና ተቋማት የጨረራ ሕክምና የሚሰጡባቸውን ክፍሎች የሚሠሩበት የተለየ የግንባታ አሠራር አለ፡፡ ጥንቃቄው ሕንፃው ዲዛይን ሲደረግ ይጀምራል፡፡ ዲዛይኑ የጨረራ ክፍሎች ጨረራን አንፀባርቀው መመለስ በሚችሉ ልዩ መስታወቶች እንዲገነቡ በጥንቃቄ የሚሠራ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የመንግሥት የጤና ተቋማት ስጋት የሌለባቸው ሲሆኑ፣ ሕንፃ ተከራይተው የሚሠሩ የግል የጤና ተቋማት ግን የተከራዩትን ሕንፃ  ለጨረራ ሕክምና በሚመጥን መልኩ አፍርሰው በመስታወት አልያም በሊድ  ለመሥራት እንደሚገደዱ ይናገራሉ፡፡፡

‹‹ግድግዳው በተለየ ጥንቃቄ መሠራት ይኖርበታል፡፡ ግድግዳ ጥሶ አልፎ የሚሄድ ጨረር አለ፤›› ይህ ጨረር በተገቢው መንገድ ያልተገነባ ህንፃን አልፎ ከወጣ በሕንፃው ዙሪያ ያሉ ሌሎችን ሊያጠቃ እንደሚችል አቶ አዝማች ተናግረዋል፡፡ የጨረራ መከላከያ ባለሥልጣን ለሆስፒታሎች የሥራ ፈቃድ የሚሰጠውም ይህንን መስፈርት ማሟላታቸውን ካረጋገጠ በኋላ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም ራዲዮአክቲቭ የሆኑ በህክምናው ዘርፍ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ውህዶች አወጋገድ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን አቶ አዝማች ይናገራሉ፡፡ በከተማዋ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሆስፒታሎች እነዚህን ኬሚካሎች በሴፕቲክ ታንክ አጠራቅመው ማስመጠጥ ሲኖርባቸው ወደ ከተማው ፍሳሽ ማስወገጃ ስርኣት እንዲቀላቀሉ እንደሚያደርጉ የታዘቡትን ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ፍሳሾች ወደ ማህበረሰቡ ሲለቀቁ ገሚሱ ልብስ ያጥብባቸዋል፣ ገሚሱ ይዋኝባቸዋል፣ የተቀረው ደግሞ እንደ ጎመን ያሉ የጓሮ አትክልቶች ያለማባቸዋል፡፡

‹‹የመኪና ባትሪ ውስጥ ያሉ ራዲዮ አክቲቭ ውህዶች ሳይቀሩ ወንዝ ውስጥ ነው የሚገቡት፡፡ ይህም ህብረተሰቡንና አካባቢውን ለከፍተኛ የጤና ችግር እየዳረገ ይገኛል፤›› የሚሉት አቶ አዝማች በዓመት በፊት በተሰራ አንድ ጥናት በከተማው አንዳንድ አካባቢዎች የሚለማ የጎመን ምርት ከፍተኛ የራዲዮአክቲቭ ውህድ እንደተገኘበት በምሳሌነት በመጥቀስ ነው፡፡

የጨረራ መሳሪያዎችን ጨምሮ ከቁጥጥር ነፃ ያልሆኑ የጨረራ አመንጪዎችና ተዛማጅ ተግባራት በግለሰቦች፣ በኅብረተሰቡ፣ በንብረትና አካባቢ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን የጨረራ ጠንቆች ለመከላከል የተቋቋመው ባለሥልጣኑ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡

አንድ ሰው በዓመት ከአንድ ሚሊ ሲቨርት (የጨረራ መለኪያ) የበለጠ ለጨረራ መጋለጥ እንደሌለበትም ደንግጓል፡፡ አቶ ታደለ እንደሚሉት፣ አንድ ሚሊ ሲቨርት ጨረራ በዓመት በጤና ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ የለውም፡፡ ይህም ለብዙኃኑ ማኅበረሰብ የተቀመጠ ከፍተኛው የተጋላጭነት መጠን ሲሆን፣ ለጨረራ ባለሙያዎች ደግሞ 12 ሚሊ ሲቨርት ትልቁ ገደብ ሆኖ ተቀምጧል፡፡

እንደሳቸው ገለጻ፣ የጨረራ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት የሚጠቀሙ ያደጉት አገሮች ለጨረራ ባለሙያዎች የተቀመጠው የተጋላጭነት መጠን እስከ 20 ሚሊ ሲቨርት ይደርሳል፡፡ አንዳንድ አገሮች እንዲያውም ገደቡን ከ20 ሚሊ ሲቨርት በላይ እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ የተቀመጠው ከፍተኛው የተጋላጭነት መጠን ከአንድ እስከ 12 ሚሊ ሲቨርት መካከል መሆኑ አገሪቱ በጨረራ ቴክኖሎጂ ብዙም ተጠቃሚ ባለመሆኗና የማኅበረሰቡ ተጋላጭነት መጠንም ከፍተኛ ቁጥጥር ለማድረግ አስቸጋሪ ባለመሆኑ ነው፡፡

እንዲህም ሆኖ በግንዛቤ ችግር የሚፈጠሩ አደጋዎች መኖራቸውን አቶ ታደለ ይናገራሉ፡፡ በባለሙያ ብቻ መሠራት ያለባቸውን የጨረራ የኤክስሬይ የሕክምና ክፍሎች ውስጥ ገብተው እንደ ማብሪያና ማጥፊያ ማሽን የሚያጠፉ ሰዎች እንደሚያጋጥሙ ገልጸዋል፡፡ በአፍና በአፍንጫ የሚገቡ ራዲዮ አክቲቭ የሆኑ ነገሮች ባሉበት የማዕድን ማውጫ ላይ አለምንም መከላከያ ሲሠሩ የተገኙ ሰዎችም አሉ፡፡ በቆላ ዝንብ ማራቢያ ፕሮጀክት ላይ ሲሠራ የነበረ አንድ ባለሙያ ሲሠራበት የነበረው ማሽን በመበላሸቱ እጁን ልኮ ችግሩን ለማወቅ ባደረገው ጥረት ጣቶቹን በጨረራ ማጣቱን ያስታውሳሉ፡፡ ወደ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሄዱ መሰል ጉዳዮች እስካሁን ሰባት የደረሱ ቢሆንም፣ አብዛኛው ኬዝ የመሥሪያ ቤቶች ሪፖርት ሳይደረግ እንደሚቀር ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡