Skip to main content
x
ፍርድ ቤት የእነ አቶ በቀለ ገርባ መከላከያ ምስክሮች እንዳይቀርቡ የሰጠው ትዕዛዝ ተቃውሞ ገጠመው

ፍርድ ቤት የእነ አቶ በቀለ ገርባ መከላከያ ምስክሮች እንዳይቀርቡ የሰጠው ትዕዛዝ ተቃውሞ ገጠመው

በአቶ አያና ጉርሜሳ የክስ መዝገብ የተካተቱት እነ አቶ በቀለ ገርባ በመከላከያ ምስክርነት የቆጠሯቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ አቶ ለማ መገርሳ፣ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ቀርበው እንዲመሰክሩ ያቀረቡትን ጥያቄ፣ ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረጉ በተከሳሾቹ ተቃውሞ ቀረበ፡፡

ተከሳሾቹ በመከላከያ ምስክርነት ከቆጠሯቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውስጥ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ምላሽ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካለባቸው አገራዊ ሥራ አንፃር ጊዜ ኖሯቸው ሊቀርቡ ስለማይችሉ፣ ንግግራቸውን ከተናገሩበት ቦታ ከመቅረፀ ድምፅ መውሰድ እንደሚቻል መግለጹን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡  

የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናትም አስቸኳይ አገራዊ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ጽሕፈት ቤት ገልጾ፣ ተለዋጭ የመመስከሪያ ጊዜ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱን በደብዳቤ መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ፍርድ ቤቱ ጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በሁለቱ ምላሾች ላይ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሳይቀርቡ የቀሩት፣ ባቀረቡት በቂ ምክንያት መሆኑን ማረጋገጡን ፍርድ ቤቱ በትዕዛዙ ገልጿል፡፡ በመቀጠልም በመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩት ባለሥልጣናት እንዲቀርቡ፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠት ይችላል? ወይስ አይችልም?›› የሚለውን ከተገቢው የሕግ ድንጋጌዎች አንፃር መመርመሩንም አስረድቷል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 124፣ 125 እና 94(1 እና 2ለ)፣ እንዲሁም የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 118 መሠረት መመርመሩን በትዕዛዙ ገልጿል፡፡

በምርመራውም ፍርድ ቤቱ የደረሰበት ውሳኔ ከፍተኛ ሥራ ያለባቸውን የመንግሥት ባለሥልጣናት በረባ ባልረባው ነገር እንዲቀርቡ ማድረግ፣ ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ ማድረግ መሆኑን ገልጿል፡፡ አቶ ጉርሜሳ አያኖ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋና አቶ አዲሱ ቡላላ ተከላከሉ የተባሉት በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) መሠረት መሆኑን፣ አቶ በቀለ ገርባ ደግሞ በወንጀል ሕግ 257(ሀ) መሠረት መሆኑን አስታውሶ፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቀርበው ይመስክሩ ማለት ጉዳዩን ከማዘግየትም በተጨማሪ፣ ተገቢነት እንደሌለውም በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ባለሥልጣናቱ እንዲቀርቡ ማዘዝ እንደማይገባው ትዕዛዝ መስጠቱንና በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ የቀረበውን ጥያቄ እንዳልተቀበለው ብይን መስጠቱን አስታውቋል፡፡

የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አስተያየት፣ ባለሥልጣናቱን በምስክርነት የቆጠሩት የሥራ ጫና እንዳለባቸው ሳያውቁ ቀርተው ወይም በቸልተኝነት ሳይሆን፣ ለችሎቱ አስረድተውና ፍርድ ቤቱም አምኖበት ሁለት ጊዜያት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡ በመከላከያ ምስክርነት ከተቆጠሩት ውስጥ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በስተቀር ሌሎቹ ቀርበው ለመመስከር ፈቃደኛ ሆነው፣ በተባለበት ቀን በአገራዊ ሥራ ምክንያት ሌላ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀው እያለ፣ ፍርድ ቤቱ አልተቀበልኩትም ለምን እንዳለ እንዳልገባቸው አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የአቶ አመሐን አስተያየት ከሰማ በኋላ በሰጠው ምላሽ፣ የተጠሩት ሰዎች ፈቃደኛ ናቸው ወይስ አይደሉም ሳይሆን፣ የተጠሩበት ምክንያት ጠቃሚ ነው ወይስ አይደለም የሚለው የሚታይ መሆኑን ሲገልጽ፣ ከተከሳሾቹ ተቃውሞ መቅረብ ጀመረ፡፡

ተከሳሾቹ አንድ ላይ በመሆን ባሰሙት ተቃውሞ ፍርድ ቤቱ ሐሳባቸውን ካልተቀበላቸው ፈርዶባቸው ውሳኔ እንዲነበብላቸው ተይቀዋል፡፡ ይኼ ታሪካዊ ውሳኔ መሆኑን፣ የመከላከያ ምስክሮቹን የጠሯቸው በ2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ተፈጥሮ የነበረው አመፅ የኦነግ ድርጊት ነው ወይስ የሕዝብ ጥያቄ ነው የሚለውን እንዲያስረዱላቸው እንደነበር ተከሳሾቹ እየጮኹ ገልጸዋል፡፡ ባለሥልጣናቱ የተጠሩት ራሱ ፍርድ ቤቱ አምኖበትና ትዕዛዝ ሰጥቶበት መሆኑን በማስታወስ፣ ይኼ የሕዝብ ጥላቻን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አገሪቱ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየሄደች ያለችውም በእንደዚህ ያለ አሠራር ምክንያት መሆኑንም አክለዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የመንግሥት አመራሮችን (በየወረዳውና ክልሉ ያሉ) አስመስክሮ ለምን እነሱ እንደተከለከሉ እንዳልገባቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለከሳሽም ሆነ ለተከሳሽ እኩል ነው ብለው እንደማያምኑ አቶ በቀለ ገልጸው፣ ‹‹በረባ ባልረባው እያላችሁ ህሊናችንን አትጉዱት፤›› ብለዋል፡፡ የፍርድ ቤቱን ድራማ መስማት እንደሌለባቸው፣ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ እየሞቱ መሆኑን በመግለጽ፣ በድጋሚ ወደ ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡም ተናግረዋል፡፡

ላለፉት 26 ዓመታት ሕዝቡ ችግር ውስጥ መሆኑንና እነሱም ሞተው በእነሱ ላይ መቆም እንዳለበት ከገለጹ በኋላ፣ በኦሮሚኛ ቋንቋ ጮክ ብለው መዝፈን ጀመሩ፡፡ ረዘም ላለ ደቂቃ ሲዘፍኑ ከቆዩ በኋላ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በችሎት የፈጠሩትን ሁከት አስመልክቶ ችሎት በመድፈር ወንጀል የጣለባቸውን የስድስት ወራት ቅጣት ለማንበብ ሲጀምር፣ ‹‹አናዳምጥም፣ ግደሉን ሞት በእኛ ይብቃ፡፡ ወደ ልጆቻችን መተላለፍ የለበትም . . . ›› በማለት ሁሉም በአንድ ድምፅ እየተናገሩ ማዳመጥ ባይቻልም፣ ችሎቱ በእነሱ ላይ የጣለውን ቅጣት እንብቦ ሲጨርስ፣ በመዝገቡ ላይ ፍርድ ለመስጠት ለጥር 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡