Skip to main content
x
ልማት ባንክ አዳዲስ የእርሻ ፕሮጀክቶች የብድር  ጥያቄዎችን መቀበል አቆመ
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ናና

ልማት ባንክ አዳዲስ የእርሻ ፕሮጀክቶች የብድር ጥያቄዎችን መቀበል አቆመ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከአዳዲስ በዝናብ የሚለሙ እርሻ ፕሮጀክቶች የሚመጡ የብድር ጥያቄዎች መቀበል ማቆሙን አስታወቀ፡፡

ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ናና ለሁሉም የባንኩ ዲስትሪክት ጽሕፈት ቤቶች ተፈርሞ በወጣ ደብዳቤ፣ ተለዋጭ መመርያ እስከሚስጥ ድረስ አዳዲስ በዝናብ የሚለሙ የእርሻ ፕሮጀክቶች የብድር ጥያቄ ለጊዜው ማስተናገድ ማቆሙ ተገልጿል፡፡

‹‹ከዚህ በፊት የሰጠናቸው የእርሻ ብድሮችን ውጤታማነታቸውን እስክናረጋግጥ ድረስ አዳዲስ የብድር ጥቄዎችን ለማቆም ወስነናል፤›› ሲሉ የባንኩ የስትራቴጂና ለውጥ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ኃይለ ኢየሱስ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ይህ ማለት ግን ባንኩ ተመልሶ ብድሮች አይሰጥም ማለት አይደለም ብለዋል፡፡

ከሳምንት በፊት ባንኩ ጥሩ አፈጻጸም ባስመዘገቡ፣ ለሰፋፊ የእርሻ ፕሮጀክቶች ለሚቀጥለው የምርት ዘመን ብድር ለማቅረብ ዝግጅት እንዲደረግ ማዘዙ ይታወሳል፡፡

ከዚህ ቀደም በተለይም የአሁኑ የባንኩ ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን ከመጡ በኃላ፣ የሰፋፊ እርሻ ባለሀብቶች በቂ ብድርና ሌሎች ዕገዛዎች እየተደረጉላቸው እንዳልሆነ ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወሳል፡፡