Skip to main content
x

በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መግለጫ ላይ አንዳንድ ነጥቦች

በመርሐፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

አራቱን ብሔራዊ ድርጅቶች በማጣመር የተዋቀረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ድፍን 17 ቀናትን እንደፈጀ በተነገረለት ታሪካዊ ስብሰባው ማግሥት፣ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን የዳሰሰ አንድ ሰሞናዊ መግለጫ አውጥቷል፡፡ መግለጫው ትኩስና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች አማካይነት በቅብብሎሽ ላይ ያለ በመሆኑ ለብዙ አንባቢያን አዲስ እንደማይሆንባቸው ከወዲሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይልቁንም ከመታወቅ አልፎ አገራችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለገባችባቸው አደገኛና ውስብስብ ችግሮች ዓይነተኛ መፍትሔዎችን አንግቦ መጥቷል ከሚሉት የዋሃን አንስቶ፣ ከወትሮው የተለየ አንዳች ቁምነገር አልያዘምና በከንቱ አትድከሙ እያሉ እስከሚያሟርቱት የፍጹም ቀቢጸ ተስፋ ሰለባዎች ድረስ ከቀደምት የግንባሩ መግለጫዎች በተሻለ ሁኔታ የብዙዎችን ትኩረት እንደሳበ ተረድቻለሁ፡፡

በአስተያየቶች ላይ የእኔ አስተያየት

ግንባሩ ከሰማይ በታች ያሉ ጉዳዮችን ሁሉ ያለገደብ እንዳነሳና ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በግልጽነት ሲከራከርባቸው እንደሰነበተ ሊቀመንበሩ ራሳቸው በቴሌቪዥን ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ያም ሆኖ የትኛውም ድርጅታዊ መግለጫ የአንድን ታላቅ አገርና ሕዝብ መላ ችግሮች ጨርሶ እንደሚፈታ መመኘት ይቅርና ከመነሻው ማሰቡ ራሱ አመክንዮ የጎደለው አስተያየት ከመሆን ከቶ ሊዘል አይችልም፡፡

በመሠረቱ አገራችንን ክፉኛ እየተፈታተነ ላለው ፖለቲካዊ ቀውስ በሥልጣን ላይ ያለም ቢሆን ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት የአቋም መግለጫ አቅም ያለፈ መሆኑን በተገቢው መንገድ ማጤን ይገባል፡፡ መላው ሕዝባችን መግለጫውን ሊረዳውና ሊገመግመው የሚገባው የሁሉንም ባለድርሻዎች ገደብ የለሽ ተሳትፎ በሚጠይቀው ዘርፈ ብዙ ጥረት፣ ማዕቀፍና ዓውድ ውስጥ ሆኖና በችግሩ አፈታት ረገድም የራሱን ቀና ተባባሪነት ጭምር ግምት ውስጥ አስገብቶ መሆን ይኖርበታል፡፡

በእርግጥ ኢሕአዴግ ለጊዜውም ቢሆን በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያለ አንድ ወሳኝ ኃይል መሆኑን አስምሮ መነሳት አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን የአገራችን ችግሮች ሁሉ አልፋና ኦሜጋ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ መግለጫውም ያንን ታሳቢ አድርጎ የተቀረፀና የወጣ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ቢያንስ ጥሪውን በቀጥታ ያስተላለፈው ለራሱ ለድርጅቱ አባላትና ለሕዝቡ እንደሆነ ከአንዳንድ የመግለጫው መንደርደሪያ ወይም መዝጊያ ዓረፍተ ነገሮች ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መግለጫው ለጥቅስ የሚበቃ አንዳች ቁምነገር የሌለበት ባዶ ‹ቱሪናፋ› ብቻ ነው የሚሉ ጽንፈኞች ተቃራኒውን ማየት ይበጃቸዋል እላለሁ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እግዜርን የሚያካክሉ 36 ወንድና ሴት መሪዎች (በእርግጥ አብዛኞቹ ወንዶች ናቸው)፣ ለ17 ቀናት ያህል በአት ዘግተውና ሱባዔ ተቀምጠው ያውም ድምፅ የመስጠት መብት በሌላቸው ነባርና አንጋፋ የግንባሩ አበው ታጋዮቻቸው ምክር ጭምር እየታገዙ እልህ አስጨራሽ ውይይትና የጦፈ ክርክር ሲያካሂዱ ከሰነበቱ በኋላ፣ በመካከላችን ይታዩ ነበር ያሏቸውን የእርስ በርስ ጥርጣሬዎች አስወግደን መተማመንና የሐሳብ አንድነት ላይ ደርሰናል በማለት ያረቀቁትና ለሕዝባቸው ይፋ ያደረጉት ይህ የአቋም መግለጫና ውሳኔ፣ አንዳች ዓይነት በጎ ነገር የሌለውና በእንቶ ፈንቶ ጉዳዮች የታጨቀ ማዘናጊያ ብቻ ነው ብሎ መደምደሙ ጤናማነት አይመስለኝም፡፡ ይነስም ይብዛም መግለጫው በዝርዝር ሲታይ ከቀዳሚ የግንባሩ መግለጫዎች ሁሉ በተሻለ አንዳንድ ቁምነገሮችን እናገኝበታለን፡፡ እርግጥ ነው እነዚህ ውስን ቁምነገሮች ከነፃ መሬት ጉባዔዎች ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ የተራዘመ ስብሰባ ምክንያት ከባከነው ጊዜ አንፃር የባለ ዋጋነታቸው ደረጃ ሊያነጋግር እንደሚችል እኔም አምናለሁ፡፡

የመግለጫው አወቃቀር

በዚህ የአቋም መግለጫው ኢሕአዴግ እንደ አንድ መሪ የለውጥ ኃይል መንግሥታዊ ሥልጣን ከጨበጠበት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ከምልዓተ ሕዝቡ ጋር ባካሄደው ርብርብ አገሪቱን በኢኮኖሚ ረገድ ከነበረችበት የማሽቆልቆል ጉዞዋ በመግታት ወደ ሚያስጎመጅ የዕድገት ደረጃ ለማሸጋገር እንደቻለ አጠንክሮ በማወጅ ተንደርድሯል፡፡ ይህ መቼም ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ› ነውና ያልተለመደ ነገር መስሎ ጎራ በመለየት እንደ አዲስ ባያጨቃጭቀን እመርጣለሁ፡፡

በእርግጥ የቋንቋ አጠቃቀም ነገሮችን ሊያኮስስ ወይም ሊያወፍር ይችላል፡፡ የትኛውም ወገን ቢሆን ማስተባበል የማይችለው ግን በተለይ በመሠረተ ልማት ዝርጋታና በማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፎች ረገድ እንደተባለው ላለፉት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ ቀላል የማይባሉ እመርታዎች መመዝገባቸውን ነው፡፡ በሁሉም ማዕዘናት አውራና መጋቢ መንገዶች ተዘርግተዋል፣ ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል፣ የጤና አገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ተስፋፍተዋል . . .፡፡ በእኔ አስተያየት ለዚህ እውነታ የዓለም ባንክና የዓለም አቀፍ ገንዘብ ድርጅትን የመሳሰሉት የውጭ ተቋማት ምስክርነት እምብዛም አያስፈልገንም፡፡

ይሁን እንጂ ግንባሩ እንደ ሌላው ጊዜ ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን የዘልማድ መወድስ ተቀኝቶ ብቻ ከመድረኩ አልወረደም፡፡ በአቋም መግለጫው አነጋገር ከፍተኛ አመራሩ በፈጸማቸው ስህተቶችና ዕድገቱ በፈጠራቸው አዳዲስ ፍላጎቶች ሳቢያ ጊዜያዊና በቀላሉ ሊታለፉ የሚችሉ ናቸው ብሎ ሊያሳንሳቸው ቢዳዳውም፣ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከባድ ፈተናዎች እንደተደቀኑባት ያለማወላወል በአደባባይ አምኗል፡፡

መግለጫው ከዚህ በኋላ አከታትሎ ያሠፈራቸው ቅድመ ውሳኔ ሐተታዎች በ23 ረዣዥም ፓራግራፎች ተከፋፍለው መቀነባበራቸውን ተመልክቻለሁ፡፡ በሁሉም ላይ የሚሰማኝን አስፋፍቼ ብጽፍ ምንኛ በወደድኩ ነበር፡፡ ሆኖም ይህንን ላድርግ ብል የእናንተን ብቻ ሳይሆን የእኔንም ወርቃማ ጊዜ ክፉኛ ይሻማብኛል ብዬ ፈራሁና ለአሁኑ በጥቂት የተመረጡ ነጥቦች ላይ ብቻ ማተኮርን ፈለግሁ፡፡

ከዚህ የተነሳ በአባል ድርጅቶች መካከል መርህ አልባ ግንኙነትና ያልተገባ ነው በተባለው ቡድናዊ ትስስር፣ በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታና በፖለቲካ ብዝኃነት፣ በብሔራዊ ማንነትና በአገራዊ አንድነት ሚዛን አጠባበቅ፣ እንዲሁም በሚዲያ ተቋማት ክትትልና ቁጥጥር ላይ መግለጫው በተለይ አተኩሮ ያካሄዳቸውን ግምገማዎችና ደረስኩባቸው ያላቸውን ማጠቃለያዎች ለመመርመር እሞክራለሁ፡፡

ለዛሬው ባይደርስልኝም ግንባሩ ድኅረ ግምገማ ያሳለፋቸውን ባለስምንት ነጥብ ውሳኔዎች በመጨረሻ እተችባቸዋለሁ፡፡

መርህ አልባ ግንኙነት

ግንባሩ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአንዳንድ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል በመርህ ላይ ያልተመሠረቱ ናቸው ያላቸውን ግንኙነቶችና ቡድናዊ ትስስሮች እንዳሸተተ የአቋም መግለጫው በስምንተኛው ‹ፓራግራፍ› ላይ በዝርዝር አውስቷል፡፡ በበኩሌ ይህ ግምገማ ሰፊ ማብራሪያን የሚጠይቅና ለትርጉም ተጋላጭ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ይህንን ያልተገራ አባባል አንዳንዶች በቅርቡ ሲካሄዱ በነበሩት የፓርቲ ለፓርቲ  ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነው ሲሉ በጀሮዬ ሰምቻለሁ፡፡ ለምሳሌ በ2008 እና በ2009 ዓ.ም ተከስቶ የነበረውን ሕዝባዊ ሁከትና አለመረጋጋት ተከትሎ መጀመሪያ መቀሌ ለዳግመኛ ጊዜ ደግሞ ጎንደር ላይ በትግራይና በአማራ ክልል መንግሥታት አመራሮችና በተመረጡ ጉባዔተኞች መካከል የእርስ በርስ ግንኙነቶችና ምክክሮች ተካሂደው ነበር፡፡ በመቀጠል ደግሞ ከዚያ ሰፋ ባለ ዝግጅትና አደረጃጀት የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ባህር ዳር ከተማ ላይ ደማቅና የተዋጣለት ነው የተባለለትን የጋራ ጉባዔ በተሳካ ሁኔታ ማካሄዳቸው እውነት ሲሆን፣ በተመሳሳይ መንገድ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ተወካዮችና የኦሮሚያ አቻዎቻቸው አዳማ ከተማ ላይ ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ መምከራቸውና መዝከራቸው ይታወሳል፡፡

በእኔ በኩል የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንዲህ ያሉትን የሕዝብ ለሕዝብ የምክክር መድረኮች መርህ አልባ ግንኙነቶች ነበሩ ሲል የፈረጀ ስለመሆኑ፣ ከመግለጫው ውስጥ ፈልቅቄ ለማውጣትና ለመረዳት ፈጽሞ አልተቻለኝም፡፡ አያደርገውም እንጂ እንዲያ ብሎ ሊፈርጅ ከሞከረም ፍፁም ስህተት ይሆንበታል፡፡ ኢሕአዴግ እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን ሰፋፊ የምክክር መድረኮች ሊያበረታታ እንጂ፣ ሊነቅፍ የሚችልበት አንዳች ምክንያት ይኖረዋል ብዬ ለመገመት አልደፍርም፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሳይቀሩ ከፍ ብሎ የተጠቀሱት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች እኛ አስቀድመን ሳናውቃቸው የተከናወኑ አልነበሩም ብለው ሲናገሩ ማድመጤን አስታውሳለሁ፡፡ መሰል ግንኙነቶች ለወደፊቱ እንደሚቀጥሉም ፍንጭ ሰጥተው እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡

ከዚህ ይልቅ ግንባሩ መርህ አልባ ግንኙነት የሚለው ምናልባት የአንዱ ተጣማሪ ድርጅት ክፋይ ኃይል ከሌላኛው ድርጅት አንጃ ጋር በሚስጥር የሚያደርጋቸው፣ በጠባብ ፍላጎቶችና ጥቅሞች ላይ ይበልጥ አተኩረው ግንባሩ የሚመራበትን ጥብቅ የማዕከላዊነት አሠራር ሳይከተሉ በሹልክታ የሚካሄዱትን ግንኙነቶች ሊሆን እንደሚችል እጠረጥራለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ በጠራ አደባባይ የሚካሄደውን፣ ፀሐይ የሞቀውንና አገር ያወቀውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አበጃችሁ፣ ደግ አደረጋችሁ፣ ይልመድባችሁ፣ ከማለት በስተቀር በተባለው ደረጃ ሊኮንን የሚችልበት ምክንያት ፈጽሞ አይታየኝም፡፡ ሁላችንም በዚህ መንገድ እንድናስብ አበረታታለሁ፡፡

የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታና የፖለቲካ ብዝኃነት

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በሚፈቅደው ልክ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታውን ለማጠናከር እስካሁን ከልቡ ተግቶ እንዳልሠራ ያለማወላወል ማመኑ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በዚህ ረገድ ተቀናቃኝ ወይም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለችግሩ የየራሳቸውን ድርሻ መውሰድ እንዳለባቸው ቢታመንም፣ ላለፉት 26 ዓመታት አገራዊ፣ ክልላዊና የአካባቢ ምርጫዎች በተካሄዱ ቁጥር በአውራ ፓርቲነት የሚታይ አንድ ጥምር ግንባር ብቻ ከ99 እስከ 100 በመቶ የምክር ቤቶችን መቀመጫዎች እየተቆጣጠረ መቆየቱ አስተዛዛቢ ነው፡፡ ስለሆነም ሕገ መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሰፈነበት በየትኛውም ማኅበረሰብ ዘንድ ቅቡልነት የሌለውን ይህንን ዓይነቱን የተዛባ አሠራር ቀስ በቀስ ለማሻሻልና ለማረም ደፍሮ ቃል መግባቱ ራሱ ከፍተኛ ሞገስ ሊቸረው ይገባል እላለሁ፡፡

ሁሉም ነገር ራስን ከማወቅና እውነታውን በቅንነት ከመረዳት ይጀምራል፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ድባቡ ለተቃዋሚ ወገኖች ክፍት እንደሚደረግና በሕዝብ ምርጫ ለሚደረገው የመንግሥት ሥልጣን አያያዝ እስከ ዛሬ ድረስ ከሚታየው የተሻለ የመጫወቻ ሜዳ በእውነት ሊፈጠር እንደሚችል የተሰጠው የተስፋ ቃል ወደ ገቢር እንዲለወጥ ተጨማሪ ሰላማዊ ትግል ከማካሄድ ታቅቦ፣ ባዶ ፕሮፓጋንዳ ብቻ እንደሆነ ዘወትር ማዜሙ የለውጥ ፍላጎታችንንም ቢሆን አንድ ስንዝር እንኳ ወደፊት ፈቀቅ አያደርገውም፡፡

ብሔራዊ ማንነትና አገራዊ አንድነት

ሕአዴግ የፖለቲካ ፍልስፍና የሚጀምረው ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ የሆነች አገር ናትና በቅድሚያ የእነዚህን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት ከማወቅና በየሠፈሩባቸው አካባቢዎች የውስጥ አስተዳደር ከመትከል ባለፈ አስፈላጊ ሆኖ ቢያገኙት ከኅብረቱ ተነጥለው በመውጣት የየራሳቸውን ሉዓላዊ መንግሥታት የመመሥረት መብት ያላቸው መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ ከማረጋገጥ ነው፡፡ ይልቁንም በኢሕአዴግ እምነት እነዚህ ወገኖች ማንነታቸው በቅድሚያ ካልታወቀና ነፃ ህልውናቸው ወይም ሉዓላዊነታቸው ካልተረጋገጠ በስተቀር ኢትዮጵያ የምትባል አገር የለችም፣ አትኖርምም፡፡

ይህ የግንባሩ ፍልስፍና የማይዋጥላቸው ወገኖች በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዋነኝነት የዜጎቿ እንጂ የብሔር ብሔረሰቦቿ አገር ናት ብለው አያምኑም፡፡ በመሠረቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚለው ሐረግ የራሳቸው የዜጎች ስብስብ የሆነ ቡድናዊ መገለጫ እንጂ ያን ያህል አምርረን ልንጠላው የሚገባ አንዳች ጉድፍ አይደለም፡፡ ዋናው ችግር ያለው ከብሔራዊ ማንነትና ከኢትዮጵያዊ ዜግነት የትኛው ይበልጣል በሚል ማለቂያ የሌለው ፍትጊያ የሚካሄደው ሳብ ገትር ወይም የገመድ ጉተታ ላይ ይመስለኛል፡፡

በመሠረቱ ኢትዮጵያ የሁለቱም አገር ናት፡፡ ብሔር ብሔረሰቦቿ ሲመነዘሩ ግለሰብ ዜጎቿ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን በሁለቱም ደረጃ እኩል ሕጋዊ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ እንደ ብሔር ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋም ጭምር እኩል የመታየትና ያለአድልዎ የመጠበቅ የማይሸራረፍ መብት አላቸው፡፡

ግንባሩ ታዲያ በዚህኛው የአቋም መግለጫው ላይ ብሔራዊ ማንነትን ከአገራዊ አንድነት ጋር በንቃት አጣጥሞ ሲሠራ እንዳልቆየ በአደባባይ መናዘዙን እኔ በበኩሌ ለማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡ ዛሬም ቢሆን እንዳልመሸ አያይዤ ለመምከር እወዳለሁ፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች አገር መሆኗ አይካድም፡፡ ሆኖም እነዚህ ወገኖች ከሚለያዩባቸው ይልቅ የሚመሳሰሉባቸውና አልፎ አልፎም የአንደኛውን ብሔር ተወላጅ ከሌላኛው ለመለየት እስኪያቅት ድረስ ጭራሹን ተዋህደው የሚገኙባቸው ኩነቶች አመዝነው ይታያሉ፡፡ ስለሆነም በተፈጥሮ የተገኙ ልዩነቶችን በአግባቡ የማስተናገዱ ዕርምጃ ያለው ተገቢነት ሳይዘነጋ፣ ከሁሉም በላይ ለዜግነት ቅድሚያውን ሰጥቶ መሥራቱ አጥብቆ ይመከራል፡፡ ከዚህ አንፃር እስካሁን የተጓዝንበትን ርቀት በውል ፈትሸን የወደፊቱን ለማቃናት ቃል መግባቱ ሊበረታታ እንጂ  ያን ያህል ሊጣጣል ወይም ሊስተሀቀር አይገባውም፡፡

የሚዲያ ተቋማት ክትትልና ቁጥጥር

ኢትዮጵያ ውስጥ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት በሕገ መንግሥት ደረጃ ተረጋግጧል፡፡ ይህንን መብት በተሟላ ሁኔታ ገቢራዊ ለማድረግ ደግሞ ዓይነተኛው መሣሪያ ሚዲያ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዚህኛው የአቋም መግለጫው ታዲያ የግልም ሆነ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን የሥምሪት መስክ ለመወሰን የፈለገ መስሎ እንደተሰማኝ ለመደበቅ አልፈልግም፡፡ እንደ ግንባሩ አነጋገር ከሆነ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አተኩረው መሥራት ያለባቸው በልማትና በዴሞክራታይዜሽን ወይም ሕዝቦችን በማቀራረብ ላይ መሆን ይኖርበታል፡፡

አመለካከቱ በእርግጥ በጎ ቢሆንም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ይህንን ብሎ ብቻ መግለጫውን አልቋጨም፡፡ የግልና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተቋማት የአንድ ወገን ትርክት አፍራሽ መልዕክት ወይም ስብከት ማስተላለፊያዎች ሆነው ማገልገል እንደሌለባቸውና ከዚህ መስመር ወጥተው ቢገኙ ደግሞ ተገቢው ርምጃ እንደሚወሰድባቸው አጽንኦት ሰጥቶ እስከ ማስጠንቀቅ ዘልቋል፡፡

እዚህ ላይ የግሎችን ለጊዜው እናቆያቸውና ተግባራቸውን በመንግሥት ወጪ የሚያካሂዱ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተለያዩ አስተያየቶችን የማስተናገድ ግዴታ እንዳለባቸው፣ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ (5) ሥር በግልጽ ደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ ይህንን ግዴታ በመግለጫው መቀነስ ወይም ማሻሻል የማይቻል ጉዳይ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ከዚህ አልፈው በግንባሩ እንደተፈራው ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያቃቅሩ፣ የጦርነት ቅስቀሳዎችን የሚያካሂዱ ወይም አገራዊ ሰላምንና ደኅንነትን የማናጋት ውጤት ያላቸውን መልዕክቶች በዘፈቀደ ሲያሠራጩ የሚገኙ ተቋማት ቢኖሩ፣ ለድርጊቶቻቸው የራሳቸውን ኃላፊነት ይወስዳሉ፣ በሕግም ይጠየቃሉ፡፡ ስለሆነም ለጉዳዩ ዝርዝር የአሠራር ሥነ ሥርዓት ዘርግቶ አፈጻጸሙን መከታተል የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚወሰደው ማናቸውም ዕርምጃ ግን የምልዓተ ሕዝቡን መረጃ የማግኘት መብት ከአጠቃላዩ የደኅንነት ፍላጎት ጋር ባገናዘበ ሁኔታ በብርቱ የኃላፊነት ስሜት መፈጸም ይኖርበታል፡፡

ስምንቱ የውሳኔ ነጥቦች

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከግምገማው በኋላ ውሳኔ የሰጠባቸው ዓበይት ነጥቦች ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ናቸው፡፡

  1. ሁከት ፈጣሪዎችን በመቆጣጠር ሕግና ሥርዓትን ማስከበርና የኅብረተሰቡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሳይስተጓጎል መቀጠሉን ማረጋገጥ፣
  2. ብሔራዊ ድርጅቶች በከፍተኛ አመራር ደረጃ የየራሳቸውን ጥልቅ ግምገማ እንዲያካሂዱና የእርምትና የማስተካከያ ዕርምጃዎችን እንዲወስዱ ማድረግ፣
  3. በክልሎች መካከል የሚታዩ የልማት አቅርቦት ልዩነቶችን ማጥበብና አገራዊ አንድነትን ማጠናከር፣
  4. የሪፎርም ፕሮግራሞችን መከለስና አተገባበራቸውን ከወቅቱ የሕዝብ ጥያቄዎች ጋር ማጣጣም፣
  5. የሕዝብን አመኔታ መልሶ ለማግኘትና ለአንገብጋቢ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተከታታይ ዕርምጃዎችን መውሰድ፣ ብሎም ሕዝብ የሚደመጥበትንና ወሳኝነቱ የሚረጋገጥበትን ዕድል ማስፋት፣
  6. ከሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና ከሕዝቡ ጋር በመተባበር በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የሚታዩትን ጉድለቶች ለመቅረፍ መንቀሳቀስ፣
  7. በሕገ መንግሥቱ የተከበሩ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የመጣስ አዝማሚያዎችንና ተግባራትን አጥብቆ መመከትና መከላከል፣
  8. ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በሚያራርቅ አፍራሽ ተግባር ላይ የተሰማሩ የግልና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተቋማት አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ ማድረግ፡፡

ማሳሰቢያ

አልፎ አልፎ የነካካኋቸው ቢሆንም እነዚህን የውሳኔ ነጥቦች በሚመለከት ከማዘጋጀው አጭር ትንታኔ ጋር ሳምንት እመለሳለሁ፡፡ ብቻ የዚያ ሰው ይበለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡