Skip to main content
x
ምርት ገበያ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ወርኃዊ ግብይት አስመዘገበ

ምርት ገበያ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ወርኃዊ ግብይት አስመዘገበ

  • በግማሽ ዓመት 14 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን አገበያይቷል

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወርኃዊ የግብይት ክዋኔዎች፣ በቡና ሰሊጥ ምርቶች ግብይት በመጠንና በዋጋ ረገድ ከሌላው ጊዜ የበለጠ ጭምሪ እያሳዩ መምጣታቸውን ምርት ገበያው ይፋ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ዋነኛ የወጪ ንግድ ምርቶች በመሆን የሚጠቀሱት ቡናና ሰሊጥ ላይ የሚታየው የግብይት መጠን ከወትሮው ይልቅ እየጨመረ በመምጣቱ፣ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል እያመላከተ ነው፡፡

በተለይ በታኅሳስ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የታየው አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ግብይት የተከናወነበት ሆኗል፡፡ ምርት ገበያው በታኅሳስ ወር በነበሩ 21 የግብይት ቀናት ውስጥ የ4.4 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 105,208 ቶን ምርቶችን ማገበያየት ችሏል፡፡ ይህ የግብይት መጠን በግማሽ ዓመት ውስጥ በምርት ገበያው በየወሩ ከተከናወኑ ግብይቶች ውስጥ በገንዘብም ሆነ በምርት መጠን ከፍተኛው ግብይት የተፈጸመበት ለመሆን በቅቷል፡፡ በመሆኑም ምርት ገበያው በግማሽ ዓመት ውስጥ ብቻ የ14.1 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ማገበያየት እንደቻለ የሚያሳይ አኃዝ ነው፡፡

ካለፈው ወር ጀምሮ ለምርት ገበያው የሚቀርበው የሰሊጥ ምርት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ፣ በግማሽ ዓመቱ ውስጥ ከፍተኛው የግብይት መጠን ለማስመዝገብ አስችሏል፡፡ እንደ ምርት ገበያው መረጃ፣ በታኅሳስ ወር ለምርት ገበያው ከቀረበው አጠቃላይ ምርት ውስጥ ሰሊጥ የ63 ከመቶ ድርሻ በመያዝ ለሁለተኛ ጊዜ ከቡና የበለጠ የምርት መጠን በማቅረብ በምርት ገበያው የበላይ ሆኗል፡፡ በኅዳር ወርም ለምርት ገበያው የቀረበው የሰሊጥ ምርት ከቡና ብልጫ እንደነበረው ይታወሳል፡፡

በታኅሳስ ወር በምርት ገበያው ከተገበያየው ጠቅላላ ምርት ውስጥ ሰሊጥ 63 ከመቶ የግብይት መጠን እንዲሁም 50 ከመቶ የግብይት ዋጋ በመያዝ ቀዳሚውን ቦታ ለመያዝ በቅቷል፡፡ 66,764 ሺሕ ቶን ሰሊጥ በ2.2 ቢሊዮን ብር ዋጋ በምርት ገበያው ተገበያይቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ የሁመራ (ጎንደር) ሰሊጥ 79 በመቶ የግብይት መጠን በማስመዝገብ የአንበሳውን ድርሻ ለመያዝ በቅቷል፡፡

በታኅሳስ ወር የተገበየው የሰሊጥ ምርት ከኅዳር ወር 2010 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ17 በመቶ ብልጫ እንዳሳየ ታውቋል፡፡ በዋጋ ረገድም የ24 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ የግብይት ዋጋውም ባለፈው ወር ከተሸጠበት አኳያ ስድስት በመቶ ጭማሪ እንዳስመዘገበ ታይቷል፡፡ ግብይቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ57 በመቶ የዋጋና የ149 በመቶ የመጠን ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ የተሸጠበት ዋጋም እንዲሁ በ59 በመቶ ማድጉ በዚህ ዓመት ከሰሊጥ የሚገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ሊጨምር እንደሚችል አመላካች ሆኗል፡፡

የሰሊጥ ወርኃዊ ግብይትን የሚያሳዩ መረጃዎች፣ በሐምሌ 2009 ዓ.ም. 317 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው 12,600 ቶን ሰሊጥ ለምርት ገበያው መቅረቡን ያሳያሉ፡፡ በነሐሴ ወር ግን 11,479 ቶን ሰሊጥ ለገበያው ቀርቦ በ303 ሚሊዮን ብር ግብይት እንደተፈጸመበት ይታወሳል፡፡ በጥቅምት 2010 ዓ.ም. የተገበያየው የሰሊጥ መጠን  8,990 ቶን ሲሆን፣ ዋጋውም 265 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ምንም እንኳ እየቀነሰ የመጣው የሰሊጥ የግብይት አቅርቦት፣ በታኅሳስ ወር ግን በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ እንደታየበት ሲጠቀስ፣ በምርት መጠን 66,764 ቶን መድረሱና የተገበያየበት ዋጋም 2.2 ቢሊዮን ብር መሆኑ የሰሊጥ ግብይት ለወጪ ንግዱ መልካም አፈጻጸም ተስፋ እንዲጣልበት ምክንያት ሆኗል፡፡

ከሰሊጥ ባሻገር በታኅሳስ ወር 29,724 ቶን ቡና በ2.05 ቢሊዮን ብር ግብይት የተፈጸመበት ሲሆን፣ ይህ የግብይት መጠን ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በመጠን በ24 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ በዋጋ ደረጃም በ29 በመቶ ጭማሪ አስመዝግቧል፡፡ ቡና የተሸጠበት የግብይት ዋጋም በ3.7 በመቶ ጨምሯል፡፡ በዚህ ወር ለግብይት ከቀረቡ የቡና ዓይነቶች ውስጥ ለውጭ ገበያ የተገበያየው ቡና በግብይት መጠን 54 በመቶና በግብይት ዋጋ 52 በመቶ ድርሻ በመያዝ ቀዳሚነቱን ሲይዝ፣ የልዩ ጣዕም ወይም ስፔሻሊቲ ቡናና ለአገር ውስጥ ግብይት የቀረበው ቡና በሁለተኛነትና በሦስተኛነት ይከተላሉ፡፡

የዚህ ወር የቡና ዋጋ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ላይ ከተሸጠበት ዋጋ ጋር ሲነፃፀር በአራት በመቶ እንደጨመረ የምርት ገበያው የታኅሳስ ወር የግብይት አፈጻጸም ሪፖርት ያሳያል፡፡ የምርት ገበያው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በጥቅምትና በኅዳር ወር የተመዘገበው የግብይት መጠንም ሆነ የተገበያየበት ዋጋ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮው ከእጥፍ በላይ በመጨመሩ፣ የ2010 በጀት ዓመት የቡና የወጪ ንግድ ጭማሪ እንደሚኖረው ለመገመት አመላካች መነሻ ሆኗል፡፡

በታኅሳስ ወር ግብይት ወቅት 8,500 ቶን ጠፍጣፋና ድቡልቡል ነጭ ቦሎቄና ቀይ ቦሎቄ በ135 ሚሊዮን ብር ተገብይቷል፡፡ ካለፈው ወር ጋር አኳያም 161 በመቶ በግብይት ዋጋ፣ 160 በመቶ ደግሞ በመጠን እንደመጨመረ ታውቋል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የቦሎቄ ግብይት የ51 በመቶ በመጠንና 79 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ሲያሳይ፣ የመሸጫ ዋጋውም በ17 በመቶ አድጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 139 ቶን የማሾ ምርት ግብይት በ2.4 ሚሊዮን ብር መከናወኑን ምርት ገበያው ይፋ አድርጓል፡፡

የታኅሳስ ወር ግብይትን ለየት የሚያደርገው፣ ምርት ገበያው በዚህ ዓመት የመጀመርያው ሩብ ዓመት (በሦስት ወራት) 4.1 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በታኅሳስ ወር ብቻ የ4.4 ቢሊዮን ዋጋ ያለው ምርት ማገበያየቱ፣ በስድስት ወራት ውስጥ ከተመዘገው ይልቅ ከፍተኛው የግብይት መጠን የተፈጸመበት ወር ሆኖ እንዲመዘገብ አብቅቶታል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት፣ ከታኅሳስ ወር ባሻገር በግማሽ ዓመቱ ከፍተኛ ግብይት የተፈጸመበት የኅዳር ወር ሲሆን፣ በወቅቱ የተገበየው ምርት 3.4 ቢሊዮን ብር ዋጋ ነበረው፡፡

በምርት ገበያው የሚገበያዩት ዋና ዋና ምርቶች በምርትም ሆነ በመጠን እየጨመሩ መምጣታቸው አንዱ ምክንያት ወቅቱ የምርት ጊዜ ከመሆኑ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ሌላኛው ምክንያት ግን ምርት ገበያው የጀመራቸው አዳዲስ የግብይት አሠራሮች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ምርት ገበያው የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን አስፋፍቶ መጀመሩ አይዘነጋም፡፡ ከዚህም ባሻገር የቡና ግብይት ማስፈጸሚያ አሠራሮች ላይ ለውጥ መደረጉም ተጨማሪ አስተዋጽኦ ስለማድረጋቸው ይጠቀሳል፡፡