Skip to main content
x
በማዕድን ዘርፍ ከ70 በላይ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ዓውደ ርዕይ ሊካሄድ ነው
የኢትዮ ማይኒንግ ኤክስፖና የማዕድን ሚኒስቴር ኃላፊዎች መግለጫ ሲሰጡ

በማዕድን ዘርፍ ከ70 በላይ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ዓውደ ርዕይ ሊካሄድ ነው

  • የተቀናጀ የማዕድን ግብይት አለመኖር ዘርፉን እንደጎዳው ተገልጿል

ኢትዮ ማይኒንግ ኤክስፖ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ከማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የማዕድን ኮንፈረንስና ዓውደ ርዕይ ለማካሄድ ዝግጅት መጀመሩን አስታወቀ፡፡

የኢትዮ ማይኒንግ ኤክስፖና የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋር ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የማዕድን ኮንፈረንስና ዓውደ ርዕዩ ከጥር 18 እና 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ የማዕድን ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት  ተገልጿል፡፡

የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ባጫ ፋጂ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ የተለያዩ ማዕድናት ሀብት ባለቤት መሆኗን በሚገባ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡ የማዕድን ሀብት መልማት ያለበት በግል ባለሀብቶች እንደሆነ መንግሥት በማመኑ፣ አገሪቱ ያላትን ዕምቅ የተፈጥሮ የማዕድን ሀብት ለዓለም የዘርፉ ተዋንያን ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ አቶ ባጫ ገልጸው፣ እየተሰናዳ የሚገኘው የማዕድን ኮንፈረንስና ዓውደ ርዕይ ያሉትን የማዕድን አለኝታዎች ከማስተዋወቅ ባሻገር፣ ባለሀብቶችን ለማገናኘት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

ከማዕድን ዓውደ ርዕዩ ጎን ለጎን በሚካሄደው ጉባዔም በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ የሥነ ምድር ባለሙያዎች ጥናታዊ ጽሑፎችን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮ ማይኒንግ ኤክስፖ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማይ ተፈራ በበኩላቸው፣ የኢትዮ ማይኒንግ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የማዕድን ሀብት ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች ማስተዋወቅ፣ የከበሩ ማዕድናትና ጌጣጌጥ አምራቾችና ገዢዎችን፣ የማዕድን ማሽነሪን አቅራቢዎችን በማዕድን ፍለጋና ልማት ዘርፍ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ጋር ማገናኘት ነው፡፡

‹‹እንደ ኦፓል፣ ሳፋየርና ኤመራልድ ላሉት የከበሩ ድንጋዮች የተቀናጀ የገበያ ሥርዓት ባለመኖሩ አምራቹ ለምርቱ የሚገባውን ዋጋ እንዳያገኝ አድርጎታል፤›› ያሉት አቶ ግርማይ፣ የኢትዮ ማይኒንግ ዓውደ ርዕይ ዋና ዓላማም በማዕድን አምራቾችና ገዥዎች መካከል የገበያ ትስስር እንዲፈጠር መንገዱን ማመቻቸት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ክልሎች ያላቸውን ዕምቅ የማዕድን ሀብት ለማስተዋወቅም መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮ ማይኒንግ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስና ዓውደ ርዕይ ላይ እንዲሳተፉ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች መጋበዛቸውን የገለጹት አቶ ግርማይ፣ የ75 ኩባንያዎች ተሳትፎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ በጉባዔውም የውጭና የአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎችና ኩባንያዎች፣ እንዲሁም ታዋቂ የሥነ ምድር ተመራማሪዎች ጥናታዊ ጽሑፎችን በማቅረብ ሰፊ የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ማይኒንግ ኤክስፖ ይህን ጉባዔና ዓውደ ርዕይ ሲያዘጋጅ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን፣ ወደፊትም በቋሚነት እንደሚሰናዳ ተገልጿል፡፡