Skip to main content
x
የቱሪዝም ዘርፉ አኃዞች

የቱሪዝም ዘርፉ አኃዞች

በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲኖራቸው ከሚፈለጉ ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ነው፡፡ ዘርፉ እንዲኖረው የሚፈለገው ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንዲሆን ስለተፈለገ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት ለየት ያለ አካሄድ መከተል ጀምሯል፡፡ ይኸውም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራና በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰበሰብ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት የሚባል ተቋም ተመሥርቷል፡፡ የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ፣ ዘርፉ በቀጥታም በተጓዳኝም የሚመለከታቸው አገሪቱ ባለሥልጣናት፣ የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ የየክልሉ የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊዎች በምክር ቤቱ አባል ሆነው በየስድስት ወራት እየተገናኙ ይመክሩበታል፡፡

የቱሪዝም ዘርፉን በበላይነት ከሚመራው ከዚህ ምክር ቤት በተጨማሪም፣ ዘርፉን ለማስተዋወቅ፣ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን የማስፋፋትና የግብይት ሥራዎችን እንዲወጣ በማሰብ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ወደ ሥራ ከገባ ሰነባብቷል፡፡ 

ኢትዮጵያ ያላትን ያልተነካ የቱሪዝም ሀብት ትጠቀምበት ዘንድ፣ ይህንን ሀብት በመጠቀምም በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገቢ ታስገባ ዘንድ የተለጠጡ ዕቅዶችን ማውጣቱ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኙ አምስት ዋና ዋና የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዷ ትሆናለች፤›› ከሚለው ጀምሮ በየዓመቱ ከ2.5 ሚሊዮን ያላነሱ ቱሪስቶችን በማስጎብኘት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መካተቻ ዘመን፣ ከቱሪዝም ዘርፍ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማመንጨት እንደሚቻል ይታሰባል፡፡

ምንም እንኳ መንግሥት በዚህ ደረጃ ተለጣጭ ዕቅድ በማውጣት ከዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ከፍተኛ ቢያደርገውም፣ በርካታ ችግሮች ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ማነቆ ሆነው ቆይተዋል፡፡ አገሪቱ በተፈጥሮ፣ በባህል፣ በሃይማታዊና ባህላዊ ቅርሶችና ትውፊቶች ያላት ሀብት የካባተም ቢሆን፣ በዓለም የቱሪዝም ደረጃዋ ግን እጅጉን ዝቅተኛ ሆኖ የሚገኝ ነው፡፡ ከዓለም 120ኛ ከአፍሪካ 17ኛ ደረጃን ስለመያዟ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ዘርፉ መመንደግ የጀመረው ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ሲሆን፣ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር ብዙም ፈቅ ያላለ የውጭ ምንዛሪ ገቢና ከግማሽ ሚሊዮን ብዙም ያልዘለለ የቱሪስት ቁጥር ያስተናግድ የነበረው ዘርፍ፣ በአሁኑ ወቅት ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚገኝበትና ወደ ሚሊዮን የሚጠጉ ቱሪስቶችም አገሪቱን መዳረሻዎች መጎብኘት እንደጀመሩ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አኃዞች ይጠቁማሉ፡፡

በሳምንቱ አጋማሽ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የተቋማቸውን አፈጻጸም በሪፖርት ያሰሙት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሒሩት ወልደማርያም (ዶ/ር)፣ ባለፉት ሁለት ዓመት ከመንፈቅ በነበረው ጊዜ ውስጥ ዘርፉ የዕቅዱን 90 በመቶ ማሳካት እንደቻለ ለምክር ቤቱ አባላት አስታውቀዋል፡፡ በዚህ በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥም፣ ከጎብኚዎች ቁጥር ብሎም ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ አኳያ አበረታች ውጤቶች ስለመመዝገባቸው ጠቅሰዋል፡፡ በመንፈቅ ዓመቱ 485,806 የውጭ ጎብኚዎች መምጣታቸውንና 1.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በዚህ መንፈቅ ዓመት የታየው አፈጻጸም ባለፈው ዓመት ከታየው አኳያ የ10.5 በመቶ ብልጫ እንደነበረው በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚስትር ዴኤታ ወ/ሮ መዓዛ ገብረመድኅን፣ የዘርፉ አፈጻጸም ዘንድሮ ከሚጠበቀውም በላይ መሆኑን በመግለጽ ለበጀት ዓመቱ የተቀመጠው ዕቅድ እንደሚሳካ ያምናሉ፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ከቱሪዝም ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው 4.2 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ከ1.2 ሚሊዮን ያላነሱ ቱሪስቶች እንደሚመጡም ይጠበቃል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታዋ ዘንድሮ የቱሪስት ፍሰቱ ዝቅተኛ እንደሚሆን በሚጠበቅበት ጊዜ ሳይቀር የታየው እንቅስቃሴ ያልተጠበቀ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በቱሪስት መዳረሻዎች አካባቢ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ ሊባል የሚችል የቱሪስት ቁጥር እየተመዘገበ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

ይሁንና ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ዘርፉን ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንደከተተው የሆቴል ባለቤቶችና አስጎብኚ ድርጅቶች ሲናገሩ እየተደመጠ ነው፡፡ በተለይ ባለፈው ዓመት በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት በርካታ የጉዞ ፕሮግራሞች መሰረዛቸው ሲታወስ፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎችም ከወትሮው አፈጻጸማቸው እስከ 20 በመቶ ቅናሽ የታየበት እንቅስቃሴ ለማስተናገድ መገደዳቸውን ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡

በዚህ ሳያበቃም ከ380 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ኪሳራ እንዳጋጠማቸው በመግለጽ መንግሥት ድጋፍ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው መዘገቡም ይታወሳል፡፡ የፖለቲካ ውጥረቱን ተከትሎ ለአሥር ወራት የዘለቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የኢንተርኔት መዘጋት፣ እንደ አሜሪካና እንግሊዝ ያሉትን ጨምሮ በርካታ የቱሪስት መነሻ የሆኑ አገሮች በአገሪቱ ፖለቲካዊ ትኩሳት ምክንያት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ የሚያሳስቡ የጉዞ ማስጠንቀቂያዎችን ማውጣታቸው ኢንዱስትሪውን ሲፈታተን የቆየ ችግር ነበር፡፡

የኢትዮጵያን ኳድራንትስ አስጎብኝና የጉዞ ወኪል ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ቶኒ ሃይኪ አገሮች ያወጧቸው የጉዞ ማስጠንቀቂያዎች፣ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ ለደኅንነታቸው ዋስትና እንደሌላቸው የሚያሳስቡ በመሆናቸው ደንበኞች እንዳይመጡ ያደርጓቸዋል፤ በዚህም የዘርፉ እንቅስቃሴ ይዳከማል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

እንዲህ ባሉት ችግሮች አገሪቱ እየተናጠች ባለችበት ወቅት፣ ቱሪስቶችም ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው በቆየበት ጊዜ፣ በምን አኳኋን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ሊመጡ እንደቻሉ ጥያቄ ያጭራል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት 900 ሺሕ ገደማ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን ያስታወቀው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ባለፈው ዓመትም 887 ሺሕ ገደማ የሚጠጉ ቱሪስቶች መምጣታቸውን ገልጾ ነበር፡፡ ይህ አኃዝ እንደ ሚስተር ሃይኪ ባሉ የዘርፉ ተዋናዮች ዘንድ በሚገባ መፈተሽ እንዳለበት ይጠቀሳል፡፡ ሚስተር ሃይኪ እንደሚሉት ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ተለይተው መታየት አለባቸው፡፡

አንደኛው የአገሪቱን የቱሪስት መስህቦች በተለይም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙትን እንደ አክሱም ሐውልት፣ አክሱም ጽዮን፣ እንደ ቅዱስ ላሊበላ፣ እንደ ጣና ሐይቅና ገዳማቱ ብሎም እንደ ሰሜን ብሔራዊ ፓርክና የመሳሰሉትን ለመጎብኘት የሚመጡት ከሌሎቹ ‹‹ጎብኚዎች›› ተለይተው መታየት አለባቸው፡፡ እርግጥ ነው በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች በርካታ መዳረሻዎች ቢኖሩም፣ በዋና ዋናነት የሚጠቀሱት ግን በሰሜንና ደቡባዊ ክፍሎች የሚገኙት መስህቦች ናቸው፡፡ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች ከሚገኙት ውስጥ ሰፊውን ድርሻ የሚወስዱት ፓርኮች፣ ሐይቆችና የደቡብ ኦሞ ሸለቆ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በጠቅላላው አገሪቱ በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበቻቸው ዘጠኝ ባህላዊ ቅርሶች በአብዛኛው መገኛቸው በሰሜናዊና ደቡባዊ ክበብ ውስጥ በሚገኙት መዳረሻዎች ውስጥ ነው፡፡ የማይዳሰሱ ቅርሶችም በብዛት ይገኙባቸዋል፡፡

በሰሜኑ ክፍል የሚገኙ መዳረሻዎችን ከሚጎበኙ ቱሪስቶች ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የቅዱስ ላሊበላን አብያተ ክርስቲያናት ሳይገበኙ እንደማይመለሱ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ሚስተር ሃይኪ መነሻ በሚያደርጓቸው ምክንያቶች ሳቢያ ባህልና ቱሪዝም የሚያወጣቸው አኃዞች ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ከፍተኛ ቁጥር በሚያስተናግድበት ወቅት ላሊበላ በዓመት የሚያስተናግደው 50 ሺሕ ጎብኝዎችን ነው የሚሉት ሚስተር ሃይኪ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ግን ላሊበላን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር በግማሽ ቀንሶ ወደ 25 ሺሕ ዝቅ ማለቱን ይናገራሉ፡፡ አብዛኞቹ መዳረሻ ቦታዎች የመግቢያ ክፍያ ስለሚጠይቁ፣ ትክክለኛውን አሐዝ በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻልም ይናገራሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች እንደሚስማሙበት ሁሉ፣ ሚስተር ሃይኪም በመዳረሻ ቦታዎች ያለውን ደካማ የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት አቅም ይጠቅሳሉ፡፡ የመዳረሻ ቦታዎች የአቅም ውሱንነት በሚኒስቴሩ የሚጠቀሱትን አኃዞች ጥያቄ ውስጥ እንደሚከቱ፣ በኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን ቱሪስት ማስተናገድ የሚችሉ መዳረሻዎች ማግኘት እንደሚቸግር የሚያብራሩት ሃይኪ፣ ከቱሪስቶች ወይም ከጎብኝዎች ይልቅ የትራንዚት ተጓዦች ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ እንደሚያመዝን ይገልጻሉ፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ መስፋፋት ጋር በተጎዳኘ በርካታ የትራንዚት ተሳፋሪዎች እንደሚመጡ ተመልክቷል፡፡

 ይህም ቢባል ግን ቱሪስት የሚባለው ማን ነው? በምን አግባብ ነው ጎብኚዎች የሚገለጹት? ለሚለው ወ/ሮ መዓዛም ሆኑ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ጌትነት ይግዛው፣ በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት የሚያስቀምጠው ትርጓሜ መነሻ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ እንደ አቶ ጌትነት ገለጻ፣ ቱሪስት የሚባለው ‹‹ከመኖሪያ ቦታው ለመዝናናት፣ ለስፖርት፣ ለኮንፈረንስ፣ ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጎብኘት ወይም ለሕክምና ወይም ዘመድ አዝማድ ለመጠየቅ የሚጓዝ ሰው፤›› ያሉት አቶ ጌትነት፣ ይህም ሲባል ግን ከ24 ሰዓት ያላነሰና ከአንድ ዓመት ያልበለጠ የጊዜ ቆይታ በተጓዘበት አገር ውስጥ የሚያሳልፍ ማንኛውም ሰው ቱሪስት ተብሎ እንደሚመዘገብ አብራርተዋል፡፡

ምንም እንኳ አገሪቱ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት በሚሰጠው ትርጓሜ መሠረት ቱሪስቶችን እንደምትቆጥር ቢገለጽም፣ የአገሪቱ ቱሪስቶች ቁጥር የሚመዘገበው ግን ከኢሚግሬሽንና ከዜግነት ጉዳዮች መምሪያ በሚገኝ አኃዛዊ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ከኢሚግሬሽን የሚገኘው መረጃ ግን ከቱሪዝም ዘርፉ ተብሎ የሚመዘገብ ባለመሆኑ፣ ትክክለኛውን የቱሪስት ቁጥር እንደማያሳይ አቶ ጌትነት ገልጸዋል፡፡ በኢሚግሬሽን በኩል ሳይመዘገቡ በጎረቤት ድንበር በኩል በተለይም ከሶማሊያ፣ ከጂቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳን፣ ከኤርትራ በየቀኑ ድንበር አቋርጠው የሚገቡ በርካቶች የቱሪስት ትርጓሜውን ቢያሟሉ እንኳ ተገቢው መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ሳቢያ በዚህ አግባብ እንደማይመዘገቡ አቶ ጌትነት ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ቢባል ግን እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ቱሪስቶች በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች በኩል ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስለመሆናቸው ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

ከኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች መምሪያ የሚወሰደው መረጃ በየክልሉ የሚመዘገው የቱሪስት ቁጥር ላይ ድግግሞሽ እንዳይፈጥር ለማድረግ እንደሚረዳ ወ/ሮ መዓዛ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም በአገር ደረጃ ከዚህ ተቋም ብቻ በሚወሰድ አኃዝ የቱሪስቶች ቁጥር እንደሚወሰን ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል፡፡

በቱሪዝም ዘርፍ አከራካሪ ሆኖ የሚገኘው የገቢ መጠንና የቱሪስቶች ቁጥር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች ጋር ተዳምሮ የሚቀርብ በመሆኑ ነው፡፡ በትክክል የአገሪቱን መዳረሻዎች ለመጎብኘት የሚመጣው ቱሪስትና በአየር መንገዱ በሚጓጓዘው ተሳፋሪ መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ማስቀመጥ ትክክለኛውን የቱሪዝም ገቢና ቱሪስት ቁጥር ለመረዳት እንደሚያግዝ ሚስተር ሃይኪ ያምናሉ፡፡

የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ2006 ያወጣው ሪፖርትም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ የቱሪዝም ልማት ስትራቴጂን መነሻ በማድረግ ባንኩ ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ምንም እንኳ ለጉብኝት ወይም ለመዝናናት የሚመጣው የቱሪስት ቁጥር (እ.ኤ.አ. ከ2001 እስከ 2005 በነበረው ጊዜ ውስጥ) የ30 በመቶ ድርሻ ቢኖረውም፣ ለቢዝነስና ለስብሰባ የሚመጡት ቁጥራቸው ከ20 በመቶ በላይ እንደሆነ አስፍሯል፡፡

ይሁንና ለጉብኝትና ለመዝናናት የሚመጡት ጎብኝዎች ቁጥር ከአምስት እስከ አሥር በመቶ እንደሚያድግ ያመላከተው የዓለም ባንክ፣ በአንፃሩ የትራዚት ተጓዦች ቁጥር ግን ከ15 እስከ 25 በመቶ በሚገመት ፍጥነት እንደሚያድግ በጥናቱ አመላክቷል፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታየው የቪዛ አሰጣጥ ሒደት ከባድ በመሆኑ ለሌላ ጉዳይ የሚመጡ የውጭ ዜጎችም፣ የተንዛዛውን የቪዛ ሒደት በቱሪስት ቪዛ እንደሚያልፉ የገለጹት የዋይኤምኤች አማካሪ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለ መስቀል ናቸው፡፡

ከዚህ ሁሉ ባሻገር የቱሪዝም ዘርፉ የሚያስገኘው ገቢ የሚሰላበት ስልትም ሌላው የጥያቄ ምንጭ ነው፡፡ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው አንድ ቱሪስት በአማካይ የሰባት ቀናት ቆይታ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ በዚህ ወቅት በቀን 230 ዶላር እንደሚያወጣ ስለሚገመት፣ ይህ ገንዘብና የቆይታ ቀናቱ ለጠቅላላ የቱሪስቱ ቁጥር ተባዝቶ የሚገኘው አኃዝ የውጭ ምንዛሪ ገቢው ምን ያህል እንደሆነ ያመላክታል፡፡

ይህ ስሌት ምንም እንኳ እንደየቱሪስቱ አገባብና አመጣጥ ሊለያይ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም፣ በአማካይ በሚወሰድ ስሌት የሚተገበር በመሆኑ፣ የቱሪዝም ዘርፉ ካሉት የመዳረሻ ቦታዎች እጥረትና ካሉት የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የጥራትም የብዛትም አቅርቦት ችግር፣ ከቱሪዝም መሠረተ ልማት አውታሮች አነስተኛነት፣ በዘርፉ ከሚታየው ዝቅተኛ የሠለጠነ የሰው ኃይል አኳያና ከሌሎችም ዕይታዎች አንፃር፣ ለዘርፉ ከፍተኛ አፈጻጸም የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንቅስቃሴ ትልቁን ባለድርሻ እንደሚወስድ በርካቶች ያምኑበታል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚያወጣቸው አኃዛዊ መረጃዎች ትክክለኛነታቸው ባይታበልም፣ ሙሉ በሙሉ በዘርፉ የተገኘውን፣ ከአየር መንገዱና ከሌሎች የአገልግሎት መስኮች ከሚገኘው ገቢ ተነጥሎ በመቅረብ የፖሊሲ አውጪዎችም በዚሁ አግባብ እየቀረበላቸው ለውሳኔ አሰጣጣቸው የተስተካከለ ዕይታ እንዲያገኙ ማድረጉ ሊተኮርበት እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

በአሥራት ሥዩምና በብርሃኑ ፈቃደ