Skip to main content
x
የሕግ የበላይነትን የሚፈታተኑ ድርጊቶች ይወገዱ!

የሕግ የበላይነትን የሚፈታተኑ ድርጊቶች ይወገዱ!

መንግሥት ሰሞኑን በመጀመርያ ዙር 528 ሰዎች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንደሚለቀቁ አስታውቋል፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ደግሞ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ያደረገውን ግምገማ ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው ባለ ስምንት ነጥብ ውሳኔ መሠረት ነው፡፡ ከፖለቲካ ጋር በተገናኘ ክሳቸው እንዲቋረጥ የተደረጉ ሰዎች ከእስር መፈታታቸው መልካም ጅምር ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሒደቱ ቀጥሎ በርካቶች ከእስር እንደሚለቀቁ ይጠበቃል፡፡ አገሪቱም እስርና ከመሳሰሉ ደስ የማይሉ ድርጊቶች ተላቃ ሁሉም ነገር በሕግ የበላይነት ሥር በብሔራዊ መግባባት ይከናወን ዘንድ መመኘት ይገባል፡፡ ይህ ምኞት የተሳካ ይሆን ዘንድ ደግሞ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተፈጸሙ ስህተቶች በይቅርታና በምሕረት እየታለፉ፣ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘው በፍቅርና በመተሳሰብ አገራቸውን ከገባችበት ቀውስ እንዲታደጓት የጋራ ጥረቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የአገሪቱ የሕግ ማስከበር አገልግሎት ይዞታን ማሳደግ አንዱ ነው፡፡ በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ሰዎች አካላዊም ሆነ ህሊናዊ ችግር ሳያጋጥማቸው በሕግ የሚዳኙበት ሥርዓት ሊኖር ይገባል፡፡ ከሕግ የበላይነት ጋር የተያያዙ ዋና ዋና ጉዳዮችን እያነሳን መነጋገር አለብን፡፡

የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብትን በተመለከተ በአንቀጽ 14፣ 15 እና 16 ድንጋጌዎች አሉት፡፡ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብት አለው ይላል፡፡ በሕይወት የመኖር መብት ያለው ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም፡፡ ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው፡፡ ይህንን የመሰለ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ባለበት አገር ውስጥ ግን ግጭት ሲፈጠር የሰው ሕይወት ያልፋል፡፡ የአካል ጉዳት ይደርሳል፡፡ ንብረት ይወድማል፡፡ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ያለበት የፖሊስ ባልደረባ አንድን ተጠርጣሪ ሲይዝ ጉዳት ሳይደርስበት ለሕግ የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡ ተጠርጣሪውም በፖሊስ ቁጥጥር ሲውል ለሕግ የመገዛት ግዴታ ስላለበት ከነውጠኛ ተግባር መታቀብ ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ፖሊሶች ተጠርጣሪዎችን ሲይዙ የኃይል ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ በሰላማዊ መንገድ እጃቸው ውስጥ የገባን ተጠርጣሪ እንኳን ለመምታት አይደለም፣ ከሌላ አካል ጥቃት በመጠበቅ ለሕግ ማቅረብ ሲገባቸው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ሲፈጽሙ ይስተዋላሉ፡፡ ሕግና ሥርዓት አክብረው ኃላፊነታቸውን የሚወጡ የፖሊስ ባልደረቦች ያሉትን ያህል፣ ከሕጉ በተቃራኒ ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ መኖራቸው የዘወትር ትዕይንት ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን ድርጊት ማረም ይገባል፡፡ ለአገር አይበጅም፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 18 መሠረት ኢሰብዓዊ አያያዝ ክልክል ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን በሕግ ጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ከዚህ ሕግ በተቃራኒ ስቃይ እንደሚፈጸምባቸው ይናገራሉ፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይህንኑ የሚመለከት ሪፖርት አቅርቧል፡፡ በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብትን በሚመለከት በአንቀጽ 21 የሠፈረ ድንጋጌ አለ፡፡ በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው፡፡ ከትዳር አጋሮቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸውና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘትና እንዲጎበኙዋቸውም ዕድል የማግኘት መብት እንዳላቸው በግልጽ ሠፍሯል፡፡ ይህንን የመሰለ የሕግ ጥበቃ እየተጣሰ ግን በጥበቃ ሥርና በእስር ላይ ያሉ ዜጎች ምሬት ጎልቶ ይሰማል፡፡ ከቤተሰቦቻቸውና ከቅርብ ወዳጆቻቸው ጀምሮ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ድረስ ከባድ ምሬት ይፈጠራል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አላስፈላጊ ድርጊት በማቆም በሕጉ መሠረት ብቻ መሥራት ካልተቻለ ሕዝብና መንግሥት እንዴት ይስማማሉ? ትኩረት የሚያስፈልገው አጀንዳ ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም ሆነ የሚመራው መንግሥት ለሕግ የበላይነት ትልቅ ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲጠፋ ለአገዛዝ የሚያመቹ ሕጎች እየወጡ አገሪቱን የበለጠ እስር ቤት ያደርጓታል፡፡ የዜጎችን መብትና ነፃነት ያፍናሉ ተብለው አቤቱታ የሚቀርብባቸው ሕጎች አሉ፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ ለአፈና ወጥተዋል በተባሉ ሕጎች ምክንያት በርካታ ጭቅጭቆች ተሰምተዋል፡፡ ከፕሬስ ሕጉ እስከ ፀረ ሽብር ሕጉ ድረስ በአፋኝነት ይረገማሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እያደረገ ባለው ድርድር የፀረ ሽብር ሕጉ አንዱ መደራደሪያ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ላቀረቡበት ፀረ ሽብር ሕግ ኢሕአዴግ ምላሽ ይሰጥበታል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሰረዝ፣ መሻሻልና መጨመር አለባቸው ያሉዋቸውን አቅርበዋል፡፡ የኢሕአዴግ ምላሽም የሚጠበቀው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግምገማ ሲጠናቀቅ መግለጫ የሰጡት የአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች አመራሮች፣ በአገሪቱ ለደረሰው ቀውስ ተጠያቂ አመራሩ መሆኑን አስታውቀው ለሕግ የበላይነት አፅንኦት መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ አገሪቱ ለገጠማት የፖለቲካ ቀውስ ተጨማሪ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል የሕግ የበላይነት አለመከበር ነው፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት በአግባቡ ተግባራዊ ቢደረግ ግን አወዛጋቢ ሕጎች እየወጡ አገር አትታመስም ነበር፡፡ ይህም ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ለወቅቱ የሚመጥን ምላሽ ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ጠንካራና አስተማማኝ የሆነ የተቋማት ግንባታ ያስፈልጋታል፡፡ አዋጭና ውጤታማ ሲስተም በመገንባት መዋቅራዊ ለውጥ ማድረግ ይገባታል፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል ዴሞክራቲክ ተቋማት ያብባሉ፡፡ በጥንካሬና በውጤታማነት ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡ ለግለሰብ ወይም ለቡድን የሚታዘዝ ቢሮክራሲ ሳይሆን፣ በሕግና ሥርዓት እየተመራ አገር የሚያገለግል መንግሥታዊ ሲስተም ሲዘረጋ ለሕግ የበላይነት ልዕልና ይኖራል፡፡ በሥልጣን መባለግ አይፈቀድም፡፡ ዜጎች ሕግ ያከብራሉ፣ በሕግ ይዳኛሉ፡፡ ለሕገወጥነት ክፍተት ስለማይኖር ሰላምና መረጋጋት ይፈጠራል፡፡ ዜጎች ሕግን ብቻ  ተገን ስለሚያደርጉ ከሕገወጥ ተግባራት ይታቀባሉ፡፡ ሕግ አስከባሪ አካላት (ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ዳኛ) በነፃነት ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡ ሕግ የጣሰ በሕጉ መሠረት ይከሰሳል፡፡ በሕጉ መሠረት ይከራከራል፡፡ ንፁህ መሆኑን ካረጋገጠ ነፃ ይወጣል፡፡ ካላረጋገጠ ደግሞ በሕጉ መሠረት ቅጣቱን ይቀበላል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ሕጉን ብቻ መሠረት አድርጎ ሲሠራ ማንም ጣልቃ እንዲገባበት መፈቀድ የለበትም፡፡ ፖሊስ ከመያዝ ጀምሮ ምርመራውን ሲያከናውን ያለ ጣልቃ ገብነት ሥራውን በሕጉ መሠረትና በነፃነት ማከናወን አለበት፡፡ የዳኝነት አካሉ በነፃነት ተግባሩን ሊወጣ ይገባል፡፡ ጣልቃ ገብነት ለአፈና፣ ለጭቆና፣ እንዲሁም ለጥፋት ካልሆነ በስተቀር ለአገር ፋይዳ የለውም፡፡ ይልቁንም ጦሱ ለአገር ይተርፋል፡፡ ይህም ብርቱ እሳቤ ያስፈልገዋል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት በጣም ቀላል ነው፡፡ ይህም የሚፈልገው ቅንነትና በጎ ፈቃደኝነትን ነው፡፡ ሥልጣንም ሆነ ሀብት ከአገር ህልውና በላይ እንዳልሆኑ መተማመን ተገቢ ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ በሕግ የበላይነት ሥር አገርን ማስተዳደር አስፈላጊ ነው፡፡ ሕግ የበላይ ሲሆን ሁሉም ነገር ይቀላል፡፡ በጉልበት ሁሉንም ነገር ከማከናወን በመውጣት ለትውልድና ለታሪክ ቅርስ የሚሆን ትሩፋት ማቆየት ይገባል፡፡ ይህችን የመሰለች ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚቆጠር ሕዝብ ያላት ታሪካዊት አገር በዕድገትና በብልፅግና መገስገስ የምትችለው፣ ዜጎቿ በሙሉ በብሔራዊ መግባባት ለአንድ ዓላማ ሲቆሙ ብቻ ነው፡፡ ይህም ዓላማ አንድነቷና ሰላሟ የተረጋገጠ አገር ለመገንባት የጋራ ራዕይ መያዝ ነው፡፡ ይህ ራዕይ ተግባራዊ ሲሆን ደግሞ ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚውም ሆነ ማኅበራዊ ጉዳዩ ሁሉ በሕግ የበላይነት ሥር እየተከናወነ ዜጎች የአገራቸው ባለቤትነት በተግባር ይረጋገጥላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ሕዝቧ የጋራ አገር እንደ መሆኗ መጠን፣ በመፈቃቀድና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ አንድነቷ ፀንቶ ይቀጥላል፡፡ ይህ ምኞት ይሳካ ዘንድ ደግሞ አላስፈላጊ ድርጊቶች መቆም አለባቸው፡፡ ሕዝብና መንግሥትን ቅራኔ ውስጥ የሚከቱ ድርጊቶች ለማንም አይጠቅሙም፡፡ ስለዚህ የሕግ የበላይነትን የሚፈታተኑ ድርጊቶች ይወገዱ መባል አለበት!