Skip to main content
x
ዶ/ር መረራ ጉዲና ጨምሮ የ22 ተከሳሾች ክስ ተቋረጠ
ዶ/ር መረራ ጉዲና

ዶ/ር መረራ ጉዲና ጨምሮ የ22 ተከሳሾች ክስ ተቋረጠ

በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶባቸው ጉዳያቸውን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በቀጠሮ በመከታተል ላይ የነበሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና እና 22 ተከሳሾች ክሳቸው እንዲቋረጥ መወሰኑ ተረጋገጠ፡፡

በዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ፊርማ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት የተላከው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ ዶ/ር መረራም ሆኑ ሌሎች በክስ ላይ የነበሩ ተከሳሾች ክሳቸው ተቋርጧል፡፡

‹‹ . . . በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6/3/ሠ መሠረት፣ ለሕዝብና ለመንግሥት ጥቅም ሲባል ክሱ እንዲነሳላቸው የተወሰነ መሆኑን አስታውቃለሁ፤›› ሲሉ ዋና ዓቃቤ ሕጉ፣ በተለያዩ መዝገቦች የተከሰሱ ግለሰቦች ክሳቸው መቋረጡን ለችሎቱ አስታውቀዋል፡፡

ሰኞ ጥር 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ከፌዴራል መንግሥትና ከደቡብ ክልል ብቻ በመጀመርያ ዙር 528 ሰዎች ክስ መቋረጡን፣ አቶ ጌታቸው በሰጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር፡፡

በፌዴራል መንግሥት 115 ክሶች መቋረጣቸው የተገለጸ ሲሆን፣ እስከ ማክሰኞ ጥር 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ድረስ ዶ/ር መረራን ጨምሮ በወንጀል ችሎቱ በቀጠሮ ላይ የነበሩ የ22 ተከሳሾች ክስ መቋረጡን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡