Skip to main content
x
መንግሥት በፍርድ ቤቶች ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ የሚፈጥሩ ተጠርጣሪዎችን አስጠነቀቀ
ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ

መንግሥት በፍርድ ቤቶች ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ የሚፈጥሩ ተጠርጣሪዎችን አስጠነቀቀ

  • ምሕረት የመስጠትና ክስ የማቋረጥ ሒደት በሁለት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል
  • ክሳቸው የተቋረጠላቸው 528 ተጠርጣሪዎች ዛሬ ይፈታሉ

ተጠርጥረው የተከሰሱበት ጉዳይ በፍርድ አደባባይ እየታየ በችሎቶች ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ መፍጠር የጀመሩ ተከሳሾችም ሆኑ ሌሎች ተጠርጣሪዎች፣ ክስ ማቋረጥም ሆነ ምሕረት ማድረግ ማለት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ ይቆማል ማለት እንዳልሆነ አውቀው፣ የሕግ የበላይነትን ማክበር እንዳለባቸው መንግሥት አስጠነቀቀ፡፡

የፌዴራል ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ በጽሕፈት ቤታቸው ሰኞ ጥር 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፣ አንዳንድ ወገኖች የሕግ ማስከበር ሥራ የሚቆምና ወደኋላ የሚመለስ አድርገው ያስባሉ፡፡ ተጠርጣሪዎችንና ፍርደኞችን ክስ በማቋረጥም ሆነ ምሕረት በማድረግ እንዲለቀቁ ይደረጋል ማለት ግን፣ የሕግን የበላይነት ማስከበር ይቆማል ማለት አይደለም ብለዋል፡፡

ዋና ዓቃቤ ሕጉ እንዳብራሩት፣ ፍርድ ቤቶች መደበኛ ሥራቸውን እየሠሩ በተከሳሾች ላይ ፍርድ ሲሰጡ ‹‹መንግሥት እስረኞችን እለቃለሁ እያለ ለምን ይህንን ያደርጋሉ?›› በማለት የፍርድ ቤቱን ሥራ የሚቃወሙ አሉ፡፡ ዓቃቤ ሕግስ ለምን ክስ ይመሠርታል? ፖሊስስ ለምን ምርመራ ያደርጋል? የሚሉ የተለያዩ ወገኖች መኖራቸውንም አቶ ጌታቸው አክለዋል፡፡ ነገር ግን አንድ ተጠርጣሪ ተከሶ በፍርድ አደባባይ ከቀረበ በኋላ፣ ነፃነቱን ማረጋገጥና ማስከበር የሚችለው ሕጋዊ አካሄዶችን ተከትሎ፣ የተጠረጠረበትን የወንጀል ድርጊት በበቂ የመከላከያ ማስረጃ ማስተባበልና ነፃ መሆኑን ሲያረጋግጥ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቶችን በማወክ፣ በመበጥበጥ፣ ተገቢ ያልሆነ ዛቻና ማስፈራሪያ ቃላትን በማውጣት ከሕግ አደባባይ ለማምለጥ የሚደረግ ነገር ስህተት መሆኑንም አክለዋል፡፡

ተከሳሾች በፍትሕ አደባባይ በሚቀርቡበት ጊዜ፣ ‹‹መንግሥት እለቃለሁ እያለ ፍርድ ቤቶች የእኛን ጉዳይ የሚያዩት ለምንድነው?›› በማለት ሁከትና ብጥብጥ በችሎት የተጀመረበት አካሄድ ትክክል እንዳልሆነና እንደማይፈቀድም አቶ ጌታቸው አሳስበዋል፡፡ ‹‹መቼም ቢሆን የዚህ ዓይነት አካሄድና ተግባር ለድርድር አይቀርብም፡፡ አጥፊዎች ምን ጊዜም ቢሆን ከመጠየቅ አይድኑም፡፡ ሊታረሙና ሊስተካከሉ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ሁከትና ብጥብጥን እንደ መፍትሔ አይቶ የሚቀጥል ኃይል ካለ፣ ሕግን ለማስከበር የፍትሕ አካላት ያላሰለሰ ጥረት የሚያደርጉ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ዋና ዓቃቤ ሕጉ በቅርቡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ‹‹የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋትና አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር›› በማለት የተከሳሾችን ክስ በማቋረጥና ፍርደኞችን በምሕረት ለመልቀቅ ውሳኔ ላይ መድረሱን በማሳወቁ ምክንያት፣ በፍትሕ ዘርፉ ስለተሠሩ፣ እየተሠሩ ስላሉና ወደፊት ስለሚሠሩ ተግባራት አብራርተዋል፡፡

መንግሥት የፍትሕ ዘርፉንና ሌሎች የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለመፈጸም ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ማድረጉንና ግብረ ኃይሉም የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ አፈጻጸም ተግባራትን ለይቶ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ በአጭር ጊዜ ዕቅዱ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት የሕግ የበላይነትን ባከበረ መንገድ ክሳቸው በመታየት ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ክስ የማቋረጥ፣ በተመሠረተባቸው ክስ ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጦባቸው የተፈረደባቸውን ፍርደኞች ምሕረት የመስጠት ሥራ መጀመሩን ዋና ዓቃቤ ሕጉ ተናግረዋል፡፡ ክስ ለማቋረጥና ምሕረት ለማድረግ ተከሳሹ ወይም ተከሳሿ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ ሁከቶች፣ ብጥብጦችና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የሰው ሕይወት ያላጠፋና ከባድ የአካል ጉዳት ያላደረሰ፣ ትልልቅ የኢኮኖሚ አውታሮችን በማውደም ተግባር ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያልነበረው፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመቀልበስ በተደጋጋሚ አመፆችን ያልመራ መሆኑን ግብረ ኃይሉ በመሥፈርትነት ይዞ እየሠራ መሆኑን አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡

ሌሎች ክሳቸው የሚቋረጥላቸው ተከሳሾች ደግሞ፣ የሥርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑ ነገር ግን መንግሥት መሥራት የሚገባውን ሥራ ባለመሥራቱ የተነሳ በሌሎች ኃይሎች ፍላጎትና ዓላማ ተነሳስተው በጥፋትና በውድመት ላይ የተሳተፉ በመንግሥት ጥፋት ወደ ስህተት የገቡ ስለሆኑ፣ ክሳቸው እንደሚቋረጥና የምሕረቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚደረግ አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ግብረ ኃይሉ ባደረገው የማጣራት ሥራ መሥፈርቱን ያሟሉና በፌዴራል ደረጃ ክስ ተመሥርቶባቸው የተገኙ 115 ተጠርጣሪዎች ክስ መቋረጡን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ ፈቃደ ሥልጣኑ የፌዴራል ሆኖ ነገር ግን ክሶቹ በክልል ፍርድ ቤቶች የሚገኙ ተጠርጣሪዎችም ክሳቸው መቋረጡን አክለዋል፡፡ ከሁሉም ክልሎች ጋር ውይይት በማድረግና ስምምነት ላይ ተደርሶ ገለጻ መሰጠቱንም አቶ ጌታቸው ጠቁመው፣ ተጠርጣሪዎች መሥፈርቱን በማሟላት ክሳቸው እንዲቋረጥ መረጃውን ያቀረበው የደቡብ ክልል ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በክልሉ ባለፈው ዓመት በጌዴኦ ዞን በዲላ ከተማና ዙሪያው ወረዳዎች፣ በይርጋጨፌ፣ ኮቼሬና ገዳቦ ወረዳዎች በነበረ ሁከትና ብጥብጥ ተሳታፊ የነበሩ 361 ተጠርጣሪዎች ክስ ተቋርጧል፡፡ በሰገን ሕዝቦች አካባቢ ዞን በኮንሶ ወረዳ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ተሳታፊ የነበሩ 52 ተጠርጣሪዎች ክስ መቋረጡንም አክለዋል፡፡

በአጠቃላይ በፌዴራልና በደቡብ ክልል በመጀመርያው ዙር 528 ተጠርጣሪዎች ክስ መቋረጡን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ ክሳቸው የተቋረጠው 52 ግለሰቦች ጥር 7 እና 8 ቀን 2010 ዓ.ም. የተሃድሶ ሥልጠና ተሰጥቷቸው ረቡዕ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ተፈትተው ከቤተሰቦቻቸውና ማኅበረሰቡ ጋር እንደሚቀላቀሉ አረጋጋጠዋል፡፡ ግብረ ኃይሉ በሚቀጥሉት ሁለት ወራትም ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ምሕረት የሚደረግላቸውን ፍርደኞችና ተጨማሪ ክሳቸው የሚቋረጥላቸውን ተጠርጣሪዎች እያቀረበ፣ ምሕረት እንደሚደረግላቸውና ክሳቸው እንደሚቋረጥላቸው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ተናግረዋል፡፡

ምሕረትን በሚመለከት ዝርዝር ጥናት ተደርጎ ለፌዴራል ይቅርታ ቦርድ ሲቀርብ ቦርዱ የግብረ ኃይሉን ጥናት መዝኖና መርምሮ ለርዕሰ ብሔሩ ካቀረበ በኋላ፣ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሲያፀድቁት ምሕረት የሚደረግ መሆኑንም አቶ ጌታቸው አብራርተዋል፡፡ ክልልም በተሰጠው ፈቃደ ሥልጣን የክልሉ ይቅርታ ቦርድ ዓይቶ ለሚያፀድቀው አካል በመስጠት ምሕረቱ እንዲሰጥ እንደሚደረግም አክለዋል፡፡

መንግሥት በመካከለኛ ጊዜ ሊተገብራቸው ያቀደው ሦስት የሕግ ድንጋጌዎችን ማሻሻል ቀዳሚው ተግባር መሆኑን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ ይህም ከ50 ዓመታት በላይ በማገልገል ላይ የሚገኙትን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግንና የንግድ ሕግን ማሻሻል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ ሕጎች ረቂቆቻቸው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረባቸውንና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው እንደሚፀድቁ ተናግረዋል፡፡ ሌላው በረቂቅ ደረጃ ላይ ያለው ሕግ ደግሞ፣ የኃይል አጠቃቀም አዋጅ መሆኑን አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ ሕግ ለማስከበር ተመጣጣኝ የኃይል ዕርምጃ መውሰድ እንደሚቻል የሚገልጽ ቢሆንም፣ ‹‹ተመጣጣኝ የሆነ ኃይል ማለት ምን ማለት ነው?›› የሚለውን ለመወሰን የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡ ሌላው መንግሥት በመካከለኛ ጊዜ ዕቅዱ ማለትም እስከ በጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ድረስ ሊተገብራቸው ያቀዳቸው ነገሮች፣ በዓቃቤ ሕግ ተቋምና በፍርድ ቤት ተቋም የሚሠሩ ተግባራትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የእስረኞች የቀጠሮ አያያዝ፣ የጉዳዮች አፈጻጸምና አጨራረስ ላይ የሚታዩ መሠረታዊ ችግሮችን፣ ኅብረተሰቡ በምሬትና በብሶት የሚያነሳቸው የቀጠሮዎች መጓተትና ሌሎችንም ችግሮች የመፍታት ሥራ እንደሚያከናውን ዋና ዓቃቤ ሕጉ ጠቁመዋል፡፡

በፍትሐ ብሔር ፍትሕ አስተዳደርም ተመሳሳይ ችግሮች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው የተከሳሹ ሀብት ዕግድ ተጥሎበት ስለሚቆይ፣ ገንዘቡ ተንቀሳቅሶ ሀብት መፍጠር እንዳይችልና እንዳይወልድ ማድረግ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው መሬትን በሁከት ይወገድልኝና አጥሮ ማስቀመጥ ትልቅ እንቅፋት በመሆናቸው፣ በእነዚህ ችግሮች ላይ ሰፊ ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤትና ዓቃቤ ሕግ ነፃነታቸውን በጠበቃ አኳኋን እንዳይሠሩ የመንግሥት አካላትና የግል ባለሀብቱ እንደፈለጉ ገብተው የሚያሠሯቸው አሠራሮች እንዳሉ ከኅብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችም በደንብ ተፈትሸው፣ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሥራቸውን የሚሠሩበት አካሄድ እንደሚፈጠርም አስረድተዋል፡፡ በረዥም ጊዜ ዕቅድ መንግሥት የፍትሕ ሥርዓቱን አገሪቱ ከደረሰችበት የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የሚጣጣም ለማድረግና ለማዘመን እንደሚሠራም አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ስለፖለቲካ እስረኞች ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፣ ግለሰቦች ባላቸው የሙያ ተሳትፎ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ጋዜጠኞችም ባላቸው የሙያ ተሳትፎ ዓምደኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ፣ ነገር ግን እስካሁን ድረስ የፖለቲካ አባልና አመራር በመሆኑ የታሰረ የለም ብለዋል፡፡ የታሰረው የፖለቲካ ድርጅቱን ከለላ በማድረግ በፈጸመው ወንጀል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሐሳቡን በመግለጹ የታሰረ ጋዜጠኛ እንደሌለ፣ የታሰረውም ቢሆን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(6) ሥር የተደነገገውን ተላልፎ ቀስቃሽና ግጭት ፈጣሪ የሆኑ ጽሑፎችን በመጻፉ በፈጸመው ወንጀል ብቻ መሆኑን አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡ ‹‹የተከሳሹ ቤተሰቦችና ሌሎች አራጋቢዎች እከሌ የታሰረው ፖለቲከኛ በመሆኑና ጋዜጠኛ በመሆኑ ነው ስለሚሉ እንጂ፣ አንድም ሰው ፖለቲከኛ በመሆኑና ጋዜጠኛ በመሆኑ የታሰረ የለም፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት በሚሰጠው ምሕረት ሌሎች በቁጥጥር ሥር ያልዋሉና በውጭ  የሚገኙ ዜጎችን ስለማካተቱ ተጠይቀው፣ ያልተያዙ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙ ኃይሎች ካሉ፣ መንግሥት ባወጣው መስፈርት ተመዝነው የሚያሟሉ ሆነው ከተገኙ፣ በምሕረት አዋጁ መሠረት ምሕረት እንደሚደረግላቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ነፃ አውጪ ግንባር (ቤሕነግ)ን በምሳሌነት በመጥቀስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡