Skip to main content
x
መራጭ ተመራጭና አስመራጭ ሆድና ጀርባ የሆኑበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተካሄደበት ጊዜ

መራጭ ተመራጭና አስመራጭ ሆድና ጀርባ የሆኑበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮችን ለመምረጥ የሚደረገው ሽኩቻ ከፖለቲካዊ ቅስቀሳና እንቅስቃሴ ባልተናነሰ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ይገኛል፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ ይህ ተጋግሎ የቀጠለው ሽኩቻ፣ በቅርበት እየተከታተሉ የሚገኙት የአህጉራዊም ሆነ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ አስተዳዳሪዎች፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2020 እንደምታስተናግደው የሚጠበቀውን የቻን ውድድር አገሪቱ በገባችበት የምርጫ አተካሮ ምክንያት፣ ለሌላ አገር አሳልፈው ሊሰጡ የሚችሉበት ዕድል ሊፈጠር የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡

የምርጫው ሒደት ምንም እንኳ የግለሰቦች ፍላጎት በዋናነት ጥላውን ያጠላበት መሆኑ ባያከራክርም፣ በዚሁ እየታየ ካለው ስህተት ባሻገር፣ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) መርሕና የሕግና ድንጋጌዎች የጣሰ፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን የሚያጎላ፣ የአገሪቱን ክለቦችና ብሔራዊ ቡድን ጭምር በአህጉርና በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ ተሳትፎ በዕግድ ሲያስቀርና ሊያስቀጣ የሚችል የሕግ ጥሰቶች ገሃድ ሲወጣ እየታየ ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹ማን ላይ ሆነሽ ማንን ታሚያለሽ›› እንዲሉ ከየክልሉ ለፌዴሬሽኑ ምርጫ በአስመራጭነትም ሆነ ለምርጫ የተወከሉት ግለሰቦች፣ በአብዛኛው በየክልላቸው የመንግሥት ሥልጣን ያላቸው ሹመኞች ሆነው መገኘታቸው የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ሳለ፣ ራሳቸው ይህንኑ በየመድረኩ ሲያጎሉት እየተደመጠ ይገኛል፡፡ ይህም የእግር ኳሱ ዕድገት ጭምር ከድጡ ወደ ማጡ እያደረገ የሚገኝ አደገኛ አካሄድ ስለመሆኑ ጭምር ይነገራል፡፡

የአመራሮቹ ምርጫ፣ የውክልና ጥያቄና መሰል ጉዳዮች የሚያተራምሱት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ፣ ኢትዮጵያን ሌላ ማጥ ውስጥ የማስገባት አደጋ ከፊቱ ተጋርጦበታል፡፡ ከአደጋዎቹ መካከልም ቀደም ሲል እንደተገለጸው ቻን 2020 የአፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ ሻምፒዮናን መጥቀስ እንደሚቻል የሚናገሩት በርክተዋል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ)፣ ኢትዮጵያ ለ2020 የቻን ዋንጫ ዝግጅት በምን ዓይነት ቁመና ላይ እንደምትገኝ ገምጋሚ ቡድን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ የእግር ኳሱ ትልቅ የሥልጣን አካል ተብሎ የሚነገርለት የጠቅላላ ጉባዔው አባላት፣ ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊና ሥራ አስፈጻሚ ምርጫ የቀረቡ ዕጩ ተወዳዳሪዎችና የምርጫውን ሒደት አስመልክቶ እንዲያጣራ በጠቅላላ ጉባዔ የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴው፣ በአንድ የእግር ኳስ ጉዳይ ተመሳሳይ ቋንቋ መናገር ተስኗቸው ይታያሉ፡፡ በአጠቃላይ ሆድና ጀርባ የሆኑበት አጋጣሚ እየተፈጠረ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ከታኅሣሥ 16 ወደ ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ተሸጋግሮ የነበረው የፌዴሬሽኑ ምርጫ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ የካቲት 24 ቀን እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል፡፡ ምክንያት ተብሎ የቀረበው ደግሞ፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡ በአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን መኰንን ውሳኔ ለፊፋ በተላከው ደብዳቤ ምክንያት፣ ከአስመራጭ ኮሚቴው ብዙዎቹ ውሳኔው ‹‹እኛን አይመለከትም›› በሚል የደብዳቤውን ይዘትም ሆነ የምርጫውን መራዘም እንደማይደግፉት በይፋ ተናግረዋል፡፡ በተፈጠረው አለመግባባት ጉባዔው የጣለባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ እንዳልሆነ ጭምር ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

የአስመራጭ ኮሚቴው ትርምስ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት፣ ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከጋምቤላ ክልል የተወከሉት አቶ ዳግም መላሸን በትርጉም አልባው የምርጫ ሒደትና መጓተት እየተሰላቹ መሆኑን በመጥቀስ ከምርጫው ራሳቸውን ሊያገሉ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

የጋምቤላው ተወካይ ይህንኑ አስመልክቶ ከሰሞኑ ለመገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ እንደተመደጡት ከሆነ፣ የምርጫውን መራዘም ተከትሎ የነገሮች አካሄድ እየተመቻቸ አይደለም፡፡ በመሆኑም ከፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ወጥተው ለሥራ አስፈጻሚው ምርጫ መቅረብ የሚችሉበትን ሁኔታ ከክልሉ ኃላፊዎች ጋር በመምከር ላይ መሆናቸውን ጭምር ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡