Skip to main content
x
ጉዞ ከጣይቱ እስከ ዓድዋ
የአምስተኛው ዙር የዓድዋ ተጓዦች የሽኝት ፕሮግራም

ጉዞ ከጣይቱ እስከ ዓድዋ

የቀድሞው የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮ በከተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ለተወጣጡ ጋዜጠኞች መግለጫ እየሰጡ ባሉበት መድረክ ያጋጠመ ነገር ነው፡፡ ኮሚኒስቱ ፊደል ካስትሮ ከጋዜጠኞች የሚሰነዘሩላቸውን ጥያቄዎች ይመልሱ ነበር፡፡ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል በነበረው ጦርነት የኩባ መንግሥት ለኢትዮጵያ ያደረገው ድጋፍ ሶማሊያ እንድትሸነፍ ትልቅ ሚና ተጫውቷል የሚል አንድምታ ላለውና ከአንዲት ጣልያናዊት ጋዜጠኛ ለተሰነዘረላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ግን አሽሙር ያዘለ ነበር፡፡

     ሁለቱ አገሮች በሚዋደቁበት ወቅት ኩባ ከ15 ሺሕ በላይ ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ ጎን አሠልፋ ነበር፡፡ በጦርነቱ ለተመዘገበው ድል የኩባ ወታደሮች ከኢትዮጵያውያን ወታደሮች የበለጠ ሚና እንዳልነበራቸው፣ ‹‹ስለ ኢትዮጵያውያን ጀግንነት አያቶችሽን ጠይቂ፤›› ሲሉ ምፀት የተሞላበት ምላሽ የሰጧት ወራሪውን የጣልያን ወታደሮች የኢትዮጵያ አርበኞች በዳግማዊ ምኒልክ ጠቅላይ አዝማችነት በዓድዋ ጦርነት ያነሱትን ድል በማስታወስ ነበር፡፡

የዓድዋ ድል የመላው ጥቁር ሕዝብ ብቻ ሳይሆን እንደ ካስትሮ ላሉ የኢትዮጵያ ወዳዶች ጭምር ኩራት፣ የአንድነት ተምሳሌት፣ የአገር ፍቅር መገለጫና ሌላም ብዙ ነገር ማለት ነው፡፡ ጣልያን በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ ላይ ዓይኗን ያሳረፈችው የአውሮፓ አገሮች አፍሪካን በተቀራመቱበት የቅኝ ግዛት ዘመን ነበር፡፡

ኢትዮጵያን ለመውረር ምክንያት ትፈልግ የነበረችው ጣልያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛቷ ሥር ለማድረግ መንገድ ይከፍትልኛል ብላ ያሰበችውን የውጫሌ ውል ከአፄ ምኒልክ ጋር በተወካይዋ አንቶሎኒ በኩል ተዋዋለች፡፡ በውሉ የተካተተው አንቀፅ 17 በአማርኛና በጣልያንኛው የነበረው ትርጉም ለየቅል ነበር፡፡ የአማርኛ ትርጉሙ ‹‹ንጉሠ ነገሥቱ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ግንኙነት ለማድረግ ወይም ለመነጋገር ሲፈልጉ በጣልያን ንጉሥ አማካይነት ሊያደርጉ ይችላሉ፤›› የሚል ነበር፡፡ የጣልያንኛ ትርጉሙ ግን ኢትዮጵያ በጣልያን የሞግዚት አስተዳደር ሥር እንደሆነች የሚያሳይ ነበር፡፡

አንቀፁን በሌላ እንዲቀየር የተደረገው ሙከራ ሳይካሳ ቀረ፡፡ አንቶሎኒም ሁኔታው ለጣልያን መንግሥት የክብር ጉዳይ እንደሆነ፣ ክብሩን ለማስጠበቅም ጦርነት እስከመክፈት እንደሚደርስ ፎከረ፡፡ ‹‹የዛሬ ሳምንት አድርገው፡፡ እኔ ሴት ነኝ፡፡ ጦርነት አልወድም፡፡ ነገር ግን አገሬ እንደዚህ ያለ ክብር የሚነካ ዘለፋ ከምትሸከም ጦርነትን እመርጣለሁ፡፡ ሂድ መንገዱ ጨርቅ ያድርግልህ፡፡ እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ፣ ደሙን ለአገሩ ፍቅር አፍስሶ፣ እሱ ወድቆ አገሩን የማያቆም እዚህ ያለ እንዳይመስልህ፡፡ ሂድ የኢትዮጵያን ሰው ባታውቀው ነው፡፡ ለአገሩ መሞት ማለት ለሐበሻ ጌጡ ነው፡፡ ሂድ ባሻህ ጊዜ ተመለስ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን፡፡ ያንተን ወንድነትና የጣይቱን ሴትነትም ያን ጊዜ እናየዋለን ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ፤›› ይህ የንግሥት ጣይቱ ብጡል ታሪካዊ ንግግርና ለዓድዋ ጦርነት የክተት ጥሪ ያህል ቦታ የሚሰጠው ንግግር ነው፡፡

ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ለጦርነቱ መዘጋጀት ጀመሩ፡፡ አጋጣሚውን በጉጉት ስትጠባበቅ የነበረችው ጣልያንም ጦሯን በፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት ጀመረች፡፡ በአራቱም አቅጣጫዎች በኔጄራሎች የሚመሩ ወታደሮችን አሰማራች፡፡

በወርሐ ጥቅምት 1888 ዓ.ም. ክተት ታወጀ፤ ጦርነቱም ተጀመረ፡፡ ከአምባላጌ እስከ መለ ድረስ በተደረጉ ሦስት ጦርነቶች የኢትዮጵያ ሠራዊት ጣልያንን ድል መንሳት ቻለ፡፡ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ዓድዋ ላይ የተደረገው ጦርነት ግን ከሁሉም ሚዛን የሚደፋና የጥቁር ሕዝቦች ኩራት፣ የአገር ወዳድነትና የጀግንነት ተምሳሌት ሆኖ ዛሬ ድረስ ይዘከራል፡፡

በዘመኑ የጦር መሣሪያ በመታገዝ የሚዋጉ የጣልያን ወታደሮችን ኢትዮጵያውያኑ አርበኞች ድል የነሱት በመድፍ፣ በናስሚስርና በተለያዩ ጠመንጃዎች ጋሻና ጦርንም ይዘው ነበር፡፡ ክተት ከታወጀበት ወር ጥቅምት ጀምሮ አቀበትና ቁልቁለቱን በባዶ እግራቸው አቋርጠው ነበር ጠላትን ዓድዋ ድረስ የገፉት፡፡

የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት የሆነውን የዓድዋ ድል ብሔራዊ በዓል ሆኖ እስከዛሬ እየተከበረ ይገኛል፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ መከበር የጀመረው ግን ጦርነቱ ከተካሄደ ከሰባት ዓመታት በኋላ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ የቅኝ ተገዥዎችን፣ የጥቁሮችን አንገት ቀና ያደረገና ዓለምን ያስደነቀው የድል ዜና የተሰማበት ይህ ታሪካዊ ቀን በተለያዩ ፕሮግራሞ ይዘከራል፡፡ ከነዚህ የመታሰቢያ ዝግጀቶች መካከል ጉዞ ዓድዋ አንዱ ነው፡፡

በአርቲስት ያሬድ ሹመቴ አስተባባሪነት በየዓመቱ የሚዘጋጀው የጉዞ ዓድዋ ፕሮግራም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት፣ ከጣይቱ ሆቴል ተጀምሮ ዓድዋ ላይ የሚጠናቀቅ የእግር ጉዞ ነው፡፡ በዚህ ጉዞ ላይ የሚሳተፉ ወጣቶች ምንም ዓይነት መጓጓዣ ሳይጠቀሙ ጉዞ ዓድዋ የሚደርሱት በእግራቸው ሲሆን፣ ጉዞው ከአንድ ወር በላይ እንደሚፈጅ ዓምና ከነበሩ የዓድዋ ተጓዦች መካከል የነበረችው አበባ በቀለ ትናገራለች፡፡

‹‹የመላው ጥቁር ሕዝብ ኩራት የሆነውን የዓድዋ ድልና ከድሉ በስተጀርባ የተዋደቁ እናቶችና አባት አርበኞችን ለመዘከር የሚዘጋጅ ፕሮግራም ነው፤›› የምትለው አበባ ጉዞውን ማድረግ የሚቻለው እንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ፣ ነገር ግን ደጋግማ ብትሄድ ደስተኛ እንደሆነች ትናገራለች፡፡

ከጣይቱ ሆቴል ተነስተው ከ1,000 ኪ.ሜ በኋላ ዓድዋ እስኪደርሱ 44 ቀናት ፈጅተዋል፡፡ ንጋት 12 ሰዓት፣ አንዳንዴም ከዚያ ቀደም ብለው ጉዞ የሚጀምሩ ሲሆን፣ ዕረፍት የሚያደርጉት ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ‹‹ጉዞው በመጀመርያዎቹ ቀናት በጣም አድካሚ ነበር፡፡ ገና ከአዲስ አበባ እንደወጣሁ ነበር እግሬ የቆሰለው፡፡ ከዚያም አንድ ቦታ ላይ ለሁለት ቀናት ቆይተን የተላጠው እግሬ በጨውና በውኃ ተዘፍዝፎ   የሚፈርጠው ከፈረጠ በኋላ ነው ጉዞ የቀጠልነው፤›› ትላለች የማይረሳትን ረዥሙን የዓድዋ ጉዞ ስታስታውስ፡፡

በጉዟቸው የተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎችን እየጎበኙ፣ መጻሕፍትን እያነበቡ ይውሉ እንደነበርም ትናገራለች፡፡ አዳራቸው በተለያዩ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ ቤት ለእንግዳ ባሉ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ማደሪያ ውስጥ ነበር፡፡ የዓድዋ ተጓዥ መሆናቸውን የተረዱ በየከተማውና በየቀበሌው ያገኟቸው በግ አርደው ደግሰው ይቀበሏቸው እንደነበርም ታስታውሳለች፡፡

‹‹ለመኝታ ስንዘጋጅ እንኳን እግራችንን ያጥቡልን ነበር፤›› የምትለው አበባ በጉዞዋ ቱባውን ኢትዮጵያዊ ባህል ማየት መቻሏን ትናገራለች፡፡

የጉዞው መገባደጃ ሲቃረብ በዓድዋ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ ድል እንዲቀናት ትልቅ ሚና የተጫወቱ በታሪክ የሚታወሱ አርበኞች መካከል የመረጡትን የማዕረግ  ስማቸው አድርገው ይወስዳሉ፡፡ ከአበባ አብረው ከተጓዙት መካከል የሆነው ያሬድ እሸቱ  ባሻ አውዓሎም ሐረጎት የሚል የማዕረግ ስም ተሰጥቶታል፡፡ ‹‹ጉዞ ላይ ብዙ መጻሕፍት ይነበባሉ፡፡ በመጻሕፍቱ ውስጥ በአገሪቱ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያላቸው ጀግኖች ይነሳሉ፡፡ ከእነዚያ ውስጥ የመረጥኩት ጀግና ባሻ አውዓሎም ሐረጎትን ነበር፤›› ይላል፡፡

ስለ ባሻ አውዓሎም ሲገልጽ የጣልያንን ወታደሮች አሳልፈው ለኢትዮጵያ አርበኞች የሰጡ ሰላይና የአገር ባለውለታ ናቸው ይላል፡፡ እኚህ አርበኛ ኢትዮጵያውያን በሰንበት አይዋጉም፡፡ ድንገት ሄዳችሁ በሰንበት ብትዋጉ ድል የእናንተ ነው በማለት የጣልያን ወታደሮች አሞኝተው ከምሽጋቸው እንዲወጡ ያደረጉ ናቸው፡፡

‹‹ጉዞው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነው ያሳለፍነው፡፡ አብረን መሆናችን ደስ ይላል፡፡ ታሪኩን እያነበብን በሄድን ቁጥር ደግሞ ስሜት ውስጥ እንገባ ነበር፡፡ በተለይ ታሪኩ የተፈጸመበት ቦታ ሄደሽ ስትቆሚ የሚኖረው ስሜት የተለየ ነው፤›› የሚለው ያሬድ ብዙ አማራጮ እያሉ በእግር ሄዶ ይህንን ታሪካዊ ቦታ መጎብኘት ትልቅ ነገር መሆኑን ይናገራል፡፡

‹‹ዓድዋ ለኔ አሁን ላለንበት መሠረት የጣለ ታሪካዊ ክስተት ነው፤›› የሚለው ያሬድ ለ44 ቀናት ያህል በእግር ሲጓዙ ከድካሙ ይልቅ ኢትዮጵያዊነቱ ይሰማው እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በቀን እስከ 50 ኪሎ ሜትሮችን ይጓዙ የነበረ ቢሆንም፣ ድካሙ ግን በመጀመርያዎቹ ቀናት የነበረውን ያህል እንዳልነበር አበባ ታስታውሳለች፡፡ አምስተኛው ዙር ጉዞ ዓድዋ በትናንትናው ዕለት (ጥር 8 ቀን 2010 ዓ.ም.) በ25 ተጓዦች የተጀመረ ሲሆን፣ በሞዛይክ ሆቴል የሽኝት ፕሮግራም ተዘጋጅቶላቸው ነበር፡፡