ኪነ ጠቢብ ቢኒያም ኃይለ ሥላሴ (1964 - 2010)
ብሔረሰብ ተኮር መዝሙር፣ እንዲሁም ተንፍሺ አዲስ አበባ፣ ሠራዊት ነን፣ ሰንደቃችን የሚባሉ ኅብረ ዝማሬዎችን ደርሷል፡፡ ከዚህም ሌላ የሀገር ፍቅርና የራስ ቴአትር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ቀደም ሲልም በሕፃናትና ወጣቶች ቴአትርም በርካታ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ ከአገር ውስጥ ተግባራቱ በተጓዳኝም የአገርን ገጽታ በሚያስተዋውቁ የውጭ አገር ጥበባዊ ጉዞዎችም ተሳትፏል፡፡
ይህን መሰል አስተዋጽኦ ያበረከተው ኪነ ጠቢብ ቢኒያም ኃይለ ሥላሴ ይባላል፡፡ ከአባቱ ከአቶ ኃይለ ሥላሴ ግዛውና ከእናቱ ከወ/ሮ ማያለም ዳኜ ነሐሴ 26 ቀን 1964 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደው ቢኒያም፣ ብዙ ሙያዊ ተግባራትን ማከናወን በሚችልበት ዕድሜው ማለትም በተወለደ በ46 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ከቆየ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ቢኒያም የቀብር ሥነ ሥርዓት ቤተሰቦቹ፣ አድናቂዎቹ፣ የሥራ ባልደረቦችና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት ጥር 4 ቀን 2010 ዓ.ም. በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
ነፍሰ ኄር ቢኒያም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በሰሜን ሸዋ ላሎ ማማ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ የጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ተከታትሎ ካጠናቀቀ በኋላ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1987 ዓ.ም. በቴአትር ጥበባት የመጀመርያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡