Skip to main content
x
የቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ የፊደል ገበታ መቶኛ ዓመት ሊዘከር ነው
ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴን ከፊደል ገበታ ጋር ያስተሳሰረው የሠዓሊው ዕይታ

የቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ የፊደል ገበታ መቶኛ ዓመት ሊዘከር ነው

በቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ አማካይነት የተሰናዳው የፊደል ገበታ መቶኛ ዓመት በሚያዝያ ወር ሊዘከር ነው፡፡

ማክሰኞ ጥር 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ ልጆች የፊደል ገበታው መቶኛ ዓመት አከባበር ላይ አባታቸውን ሊያስታውስ የሚችል የመንገድ ስያሜ ወይም ሐውልት እንዲቆምላቸው ለመንግሥት አካላት ጥሪ የሚያደርጉበት መድረክ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በ1910 ዓ.ም. ‹‹ዕውቀት ይስፋ፤ ድንቁርና ይጥፋ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ›› በሚል ሐሳብ በግእዝና በአማርኛ የፊደል ገበታውን ከመልዕክተ ዮሐንስ ጋር እንዳሰናዱ የሚነገርላቸው ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ፣ ዩኒቨርሲቲዎችም ቤተ መጻሕፍት በስማቸው እንዲሰይሙ ጥሪ እንደሚያቀርቡም አቶ እንዳልካቸው ተስፋ ገልጸዋል፡፡

በራሳቸው ተነሳሽነት በተስፋ ገብረ ሥላሴ ስም ቤተ መጻሕፍት ከሰየመው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲና አቢሲኒያ ባንክ የአራት ኪሎ ቅርንጫፉን ከመሰየሙ በስተቀር መዘንጋታቸው ልጆቻቸውን እንዳስቆጫቸው አልሸሸጉም፡፡

ሚያዝያ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ይሰናዳል የተባለው መቶኛ ዓመት ክብረ በዓል የተለያዩ የእርሳቸውን ሥራ የሚያስታውሱ ዝግጅቶች በተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት ሠራተኞች ይከናወናል ተብሏል፡፡

እንደ አቶ እንዳልካቸው ማብራሪያ፣ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚሰጡ መጻሕፍትን ከግእዝ ወደ አማርኛ በማስተርጐም የግእዝ ዕውቀት ለሌላቸው የፀሎታቸው ትርጉም ምን እንደሆነ እንዲረዱ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡

ያለፉትን ማሞገስ ለመጪው ትውልድ ማፍሪያ ነው ያሉት አቶ እንዳልካቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና የቅርስ ባለአደራ ለሥራዎቻቸው ዕውቅና በመስጠት ትውልድ እንዲያስታውሳቸው አደባባዮችና የተለያዩ ተቋማት በስማቸው እንዲሰየሙ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ማዕረግን ሊሰጧቸው እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት (1928-1933) ብዙዎች በዱር በገደል ሆነው ወራሪውን እንደ እግር እሳት አላስቀምጥ ብለው ታላቅ የአርበኝነት ተጋድሎ ባደረጉበት ወቅት፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ የተለያዩ ወረቀቶችን እያባዙ የአገር ፍቅር ስሜትን የሚኮረኩር ጀግንነታቸውንም የሚገልጹ ጽሑፎች በከተማ ይበተኑ እንደነበር ይገለጻል፡፡