Skip to main content
x
ጃፓንና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት ለመፈረም ድርድር ጀምረዋል
ፕሮፌሰር ኬኒቺ ኦህኖ

ጃፓንና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት ለመፈረም ድርድር ጀምረዋል

ለዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት ሲያቀርበው የቆየውን ውትወታ፣ በመንተራስ በጃፓንና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምት ለመፈረም የሚያስችሉ ድርድሮች ተጀመሩ፡፡ የመጀመሪያው ኦፊሴላዊ የድርድር መድርክ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

ከጃፓን በመጡ ባለሥልጣናትና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኃላፊዎች መካከል፣ ከጥር 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት ድርድር መካሄዱን ከጃፓን ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የድርድሩን ዝርዝር ጉዳይና ይዘት ለማወቅ የተደረገው ጥረት ባይሳካም፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ግን ድርድሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ እንደሆነ በመግለጽ ተቆጥቧል፡፡

በጃፓን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር የኢኮኖሚ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ዲቪዥን፣ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ማሳሂሮ ኢሺዳ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኃላፊዎችና ከሌሎችም ባለሥልጣናት ጋር በዝግ ስለመነጋገራቸውና ድርድር ስለመጀመራቸው ከመታወቁ በቀር፣ ዝርዝር መረጃ ከሁለቱም ወገን ማግኘት አልተቻለም፡፡ 

ይህ ይባል እንጂ ከሁለት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ከፍተኛ የምክክር መድረክ ወቅት፣ የጃፓን መንግሥት በኢንቨስትመንትና በታክስ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር የመደራደርና ስምምነት የመፈረም ፍላጎት እንዳለው አስታውቆ ነበር፡፡ በጃፓን መንግሥት ተወክለው የኢትዮጵያን መንግሥት በኢንዱስትሪ ጉዳዮች ላይ የሚያማክሩት ፕሮፌሰር ኬኒቺ ኦህኖ በወቅቱ ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የተደራራቢ ታክስ ማስቀረትን ጨምሮ ሌሎችም ስምምነቶች ከሚጠበቁት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ምንም እንኳ የኢትዮጵያ መንግሥት ለስምምነቱ ውትወታ ሲያደርግ ቢቆይም፣ በጃፓኖች በኩል ዘገምተኛ አካሄድና ቀዝቃዛ ምላሽ ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡ ከምክንያቶቹ መካከልም የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸው ዝቅተኛ ፍላጎት ነው፡፡ የዚህ መነሻው ደግሞ በርካታ ጃፓናውያን በኢትዮጵያ ስላለው አማራጭ የኢንቨስትመንት ዕድልም ሆነ በአጠቃላይ ስለአገሪቱ ያላቸው ዝቅተኛ ግንዛቤ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ገልጸው ነበር፡፡ ይኸው ችግር አሁንም ድረስ የሚጠቀስ ነው፡፡

የመጡት ጥቂት ኩባንያዎችም ቢሆኑ እያጋጠሟቸው የሚገኙ በርካታ የቢሮክራሲ ችግሮች እንደሚያስበረግጓቸው ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በተለይ ከቀረጥና ታክስ እንዲሁም ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡት ቅሬታዎች ሚዛን እንደሚደፉ ፕሮፌሰሩ በተደጋጋሚ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት ሲጠቅሱ ቆይተዋል፡፡

ይህም ሆኖ በሁለቱ አገሮች መካከል ለሚኖረው የኢንቨስትመንት ስምምት የሚያመቻቹ ሥራዎች ሲሠሩ ቢቆዩም፣ የተፈለገውን ያህል የጃፓን ኢንቨስተር ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት አልተቻለም፡፡ መንግሥት ለውጭ ኢንቨስተሮች የተመቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታ መፍጠሩን ይገልጻል፡፡

በአንፃሩ ከጃፓኖቹ ወገን የሚደመጠው ስሞታ ግን መንግሥት ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የምዕራቡ ዓለም አምራቾች እንዲሟሉላቸው የሚፈለጓቸውን ነገሮች መረዳት አልቻለም የሚለው ይገኝበታል፡፡ ለአብነት የሚጠቀሰው፣ የጃፓን ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንዲገቡ፣ በርካታ ሰዎችን መቅጠር የሚችሉ ፋብሪካዎችን እንዲተክሉ በመንግሥት መጠየቃቸው ነው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ኦህኖ ማብራሪያ የጃፓን ኩባንያዎች ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሆኑ የአመራረት ሒደቶች ታግዘው በጥቂት የሰው ኃይልና ቦታ ተወስነው ከፍተኛ ምርት ማምረት የሚችሉበት ዕድል እንዲሰጣቸው እንደሚፈልጉ፣ ነገር ግን ይህ ፍላጎታቸው በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ተገቢው ግንዛቤ ማግኘት አልቻለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ‹‹በርካታ ሰዎችን ቅጠሩ፣ ትልልቅ ማምረቻዎችን ገንቡ›› የሚሉ ጥያቄዎች ከመንግሥት ኃላፊዎች እንደሚቀርብላቸው ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ሆኖ በሁለቱ አገሮች መንግሥታት መካከል እየሰፋ የመጣው ኢንቨስትመንትን የማስተሳሰር ፍላጎት ጥቂት የጃፓን ኩባንያዎችን መሳቡ  አልቀረም፡፡ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ለጃፓኖች ፍላጎት በሚመች መንገድ ተለይቶ እንደሚገነባ የሚጠበቀው የማምረቻ ቦታ ተጠቃሽ ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን የኢትዮጵያ ትምባሆ ድርጅትን የ70 በመቶ ድርሻ ከመንግሥት የተረከበው ጃፓን ቶባኮ ኩባንያ እስካሁን ከጃፓን ወገን ከታዩት ሁሉ ከፍተኛው ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የጃፓን መንግሥት ላለፉት 45 ዓመታት አድርጎት በማያውቀው አኳኋን የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ መስጠቱም በርካታ አዳዲስ ጅምሮች ለመኖራቸው ማሳያ ነው፡፡