Skip to main content
x
ቦታውን እያስረከበ የመጣው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከባለሁለት አኃዝ ዕድገት ተራርቋል 

ቦታውን እያስረከበ የመጣው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከባለሁለት አኃዝ ዕድገት ተራርቋል 

  • እስከ ስምንት በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል

ተሰናባቹ የምዕራባውያኑ 2017 በርካታ ክስተቶችን አስተናግዷል፡፡ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ በግዙፉ ከሚጠቀሱ ክስተቶች መካከል መንግሥት የወሰደው የ15 በመቶ የምንዛሪ ለውጥ አንዱ ነው፡፡ አገሪቱ በኢኮኖሚ ረገድ ከምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ በመሆን ኬንያን ስለመብለጧም ይፋ የተደረገው በተካተተው ዓመት ነበር፡፡ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ያወጣው ሪፖርትም ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው የ8.3 በመቶ ዕድገት በዓለም ትልቁ በመሆኑ ቀዳሚነቱን ይዞ እንደነበር ማስነበቡ ይታወሳል፡፡

ይህም ሆኖ መንግሥት በአገሪቱ የበጀት ዘመን ማለትም በ2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት 11 በመቶ እንደሚያስመዘግብ ግምቱን አስታውቆ ነበር፡፡ መንግሥት ይህን ትንበያ ያስቀምጥ እንጂ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የኢኮኖሚው ዕድገት ከዘጠኝ በመቶ በታች ሲዋልል ከርሟል፡፡ የዓለም ባንክ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው ትንበያም ቢሆን፣ ኢኮኖሚው ከባለሁለት አኃዝ ዝቅ የሚል ዕድገት እንደሚኖረው አስፍሯል፡፡

የዓለም ባንክ ትንበያ የ8.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚኖር ይጠቅሳል፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅት በበኩሉ የ8.1 በመቶ ዕድገት አስፍሯል፡፡ ሌሎች ዓለም አቀፍ ትንበያዎችም ከ7.2 በመቶ እስከ 7.5 በመቶ እንደሚያድግ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ በተለይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥር 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ከኒውዮርክ ይፋ ያደረገው ሪፖርት፣ እ.ኤ.አ. ከ2009 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ በየዓመቱ የተመዘገበውን ዕድገት ሲያስቀምጥ፣ በአዲሱ የምዕራባውያን ዓመት የ7.3 በመቶ፣ በመጪው ዓመትም የ7.5 በመቶ ዕድገት ዕድገት እንደሚመዘገብ አስፍሯል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ በተመድ የዓለም የንግድና የልማት ጉባዔን ጨምሮ በርካታ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የተሳተፉበት ይፋ የተመድ ሪፖርት፣ ላለፉት ሰባት ዓመታት በአማካይ የአሥር በመቶ ዕድገት ሲመዘገብ መቆየቱን በማስፈር በአሁኑ ዓመትና በመጪውም የሚኖረው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ግን ከሰባት በመቶ እንደማይበልጥ አትቷል፡፡

 የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምንም እንኳ በውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖዎች እየታሸም ቢሆን፣ በዚህ ዓመት እንደሚያስመዘግብ የሚጠበቀው ዕድገት ግን ከጋና ቀጥሎ በአፍሪካ ትልቁ ነው፡፡ ጋና ከኢትዮጵያ የበላይነቱ በመረከብ በአፍሪካ ትልቁን የኢኮኖሚ ዕድገት እንደምታስመዘገብ የሁለቱ ተቋማት ትንበያ ያሳያል፡፡ ምንም እንኳ አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ ጋና የምታስመዘገበው ዕድገት 8.3 በመቶ እንደሆነ ያስፍሩ እንጂ፣ የተመድ ትንበያ ግን የጋና ዕድገት በዚህ ዓመት ከሚያስመዘግበው የ7.5 በመቶ መጠን ወደ 5.9 በመቶ በመጪው ዓመት ዝቅ እንደሚል አስፍሯል፡፡ ከሁለቱ አገሮች በተጓዳኝ ሩዋንዳ የሰባት በመቶ ዕድገት እንምታስመዘግብ ሲገመት፣ ኬንያ፣ ታንዛንያና ኡጋንዳም በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የሚባለውን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያስተናግዱ አገሮች ተርታ ይመደባሉ፡፡

በተሸኘው የምዕራባውኑ በጀት ዓመት ኢትዮጵያ የኬንያን የኢኮኖሚ የበላይት መረከቧ በስፋት ሲዘገቡ ከነበሩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ከአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት አኳያ (ጂዲፒ) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ72 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለው ምርትና አገልግሎት በማስመዝገብ የኬንያን ኢኮኖሚ በ29 ሚሊዮን ዶላር በመብለጥ የምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ለመባል መብቃቱን ኤምኤምኤፍ በሪፖርቱ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የቱንም ያህል እየገዘፈ ቢመጣ፣ በነፍስ ወከፍ ገቢ ረገድ የኬንያ የበላይነት ከእጥፍ በላይ ነው፡፡ ይህም የኬንያ ሕዝብ ቁጥር ከ50 ሚሊዮን በታች በመሆኑ ነው፡፡ የኬንያ የነፍስ ወከፍ ገቢ (ኢኮኖሚው ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ያስመገበው ውጤት በገንዘብ ተተምኖ ለጠቅላላው ሕዝብ ቁጥር ሲካፈል የሚገኘው ውጤት ሲሆን፣ እያንዳንዱ ዜጋ በዓመት በአማካይ ያገኘዋል ተብሎ የሚገመተው ገቢ ነው) ከ1,500 ዶላር በላይ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ከ740 ዶላር ብዙም ፈቅ አላለም፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዓመቱ ለሚያስመዘግበው ዕድገት ትልቁን ድርሻ የያዘው በመንግሥት ለመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ የሚለው ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እስከ 60 በመቶ የሚውለው የመንግሥት በጀት ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ የሚመደብ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ከፀደቀው የ321 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደውም የካፒታል በጀት ወጪ ሲሆን፣ በተለይ የመንገድ፣ የትምህርት፣ የክልሎች ድጎማና የመሳሰሉት ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡

እንደ ዓለም ባንክ ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት መንሸራተት ያሳየው፣ መንግሥት ለኢንቨስትመንት ከሚያውለው ገንዘብ እየቀነሰ ለብድር ዕዳ ክፍያ ማዋሉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ የተበደረው ገንዘብ መጠን እስከ 30 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ በልማት ድርጅቶች አማካይነት የሚበደረው ገንዘብ ሲታከልበት የአገሪቱ ዕዳ ከዚህም በላይ ከፍ እንደሚል እንደሚገመት የዓለም ባንክ ባለሙያዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚያቀርቧቸው ትንታኔዎች ውስጥ ሲጠቅሱና ምክር ሲሰጡ ማድመጥ የተለመደ ነው፡፡