Skip to main content
x
የመሐንነት ሕክምና የሚሰጥ ማዕከል ተቋቋመ

የመሐንነት ሕክምና የሚሰጥ ማዕከል ተቋቋመ

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም የሕክምና ኮሌጅ አዲስ አበባ ውስጥ 22 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የመሐንነት ሕክምና ማዕከል እንዳቋቋመና ከሦስት ወራት በኋላም አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡

የዓለም የጤናማ እናትነት ወርን አስመልክቶ ኮሌጁ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኮሌጁ የጽንስና ማሕፀን ዲፓርትመንት ኃላፊ ታደሰ ኡርጌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ማዕከሉ የመሐንነትን ሕክምና የሚሰጠው በአርቲፊሻል (ሰው ሠራሽ) በሆነ ዘዴ ጽንስ የሚፈጠርበትን ሁኔታ በማመቻቸት ነው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ማዕከሉን ዘመኑ በደረሰበት የሕክምና ቴክኖሎጂ በመደራጀት ላይ ይገኛል፡፡

ሕክምናውም ለመጀመርያ ጊዜ የሚሰጠው ጤናማ የማራቢያ አካል ኖሯቸው ግን ችግር የደረሰባቸው ወገኖች የሴቷንና የወንድ ዘር በብልቃጥ ውስጥ በመክተትና የዘሩንም ውህደት ወደ ሴትየዋ ማሕፀን በማስገባት ይሆናል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሕክምና ዘዴ እየተለመደ ከመጣ በኋላ በቀጣይ ሌሎች የሕክምና ዜዴዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደታቀደ አስረድተዋል፡፡

ዲፓርትመንቱ በእናቶችና ሕፃናት፣ የመሐንነት፣ ጽንስ ማቋረጥ፣ የሴቶች የመራቢያ አካል የካንሰር ሕክምና፣ ከማሕፀን ጋር ግንኙነት ያላቸው ወይም ከሽንት ቧንቧ ጋር የተያያዙ ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረጉ አምስት ሰብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራሞችን ቀርጾ ወደ ትምህርት ገብቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል በመሐንነት ዙሪያ የሰብ ስፔሻሊቲ ሕክምና በመሠልጠን ላይ ያለው ባለሙያ በዚህ ዓመት መጨረሻ ይመረቃል፡፡ በቀጣይ ደግሞ ሌሎች አዲስ ሠልጣኞች ተመልምለው ወደ ሥልጠና እንደሚገቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአገር ውስጥ ያሉትም ሌሎች ሐኪሞች ሱዳን፣ ጋናና ህንድ ከሚገኙ አጋሮች ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ከኃላፊው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ይህንንም ሕክምና ለማግኘት ከወዲህ ከአንድ ሺሕ በላይ ሴቶች ተመዝግበው አገልግሎቱን ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ ለእነዚህም ታካሚዎች ካለመውለድ ወይም ከመሐንነት የተያያዙ ችግሮች ምን እንደሆኑ ተለይተው ታውቀዋል፡፡

በኮሌጁ የምቹ ክሊኒክ ኬዝ ቲም አስተባባሪ ሲስተር ፍቅርተ እሸቴ እንደገለጹት ክሊኒኩ ከተቋቋመ ሁለት ዓመት እንደሞላው በእነዚህም ዓመታት ለሰባት ሺሕ ወገኖች የቤተሰብ ዕቅድና የምክክር፣ የአፍላ ወጣቶች ሥነ ተዋልዶ፣ ሁሉን አቀፍ የጽንስ ማቋረጥና ሌሎችንም ከወለድ ጋር የተያያዙ የሕክምና አገልግሎት እንደሰጠ ተናግረዋል፡፡

በተለይ መውለድ ለማይፈልጉ ሴቶች ከሚሰጠው የማሕፀን ማስቋጠር ውጪ ለወንዶችም ቋሚ የሆነ የወሊድ መከላከያዎች እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ ወንዶች ቋሚ የወሊድ መከላከያ ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎት የላቸውም፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመት ውስጥ ይህ ዓይነቱ መከላከያ የተሠራላቸው ወንዶች ሦስት ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ የገጠር ነዋሪ ሲሆን ሁለቱ የከተማ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ከከተማ ወንዶች የገጠር ወንዶች ተጠቃሚ የመሆን ፍላጎት አላቸው፡፡

በመግለጫው እንደተወሳው፣ የወንዶች የወሊድ መከላከያን ለማከናወን በጣም ቀላልና ሥራውም ከ20 ደቂቃ የማይበልጥ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱም አገልግሎት በማግኘቱ የተነሳ በፊት ከነበረው ሁኔታ ወይም ስሜት ምንም የሚቀንሰው የለም፡፡ ግንኙነት በሚደረግበት ጊዜ የሚኖረው እርካታ እንደተጠበቀ ይሆናል፡፡ ወንዶቹ ይህንን አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ያልቻሉት በግንዛቤ ጉድለት እንደሆነ በመረዳት በአሁኑ ጊዜ በግንዛቤ ማሳደግ ሥራ ላይ እየተሠራ ነው፡፡

የቅዱስ ጰውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የሕክምና ዘርፍ ምክትል ፕሮቮስት ብርሃኔ ረዳኢ (ዶ/ር) ኮሌጁ ከፍተኛ የወሊድ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መሆኑን ገልጸው፣ ይህንንም አገልግሎት ዘመናዊና ምቹ በሆነ መልኩ ሊያስኬዱ የሚችሉ የተለያዩ የማስፋፊያና የግንባታ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በየወሩ እስከ አንድ ሺሕ እናቶች የወሊድ አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል 45 ከመቶ ያህሉ በቀዶ ሕክምና የወሊድ አገልግሎት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተለይ የጨቅላ ሕፃናትን ሕክምና አቅም ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

ከተከናወኑትም ተግባራት መካከል በራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል ውስጥ አንድ ወለል (ፍሎር) ኮሌጁ ለጨቅላ ሕፃናት ሕክምና አገልግሎት እንዲጠቀሙበት መደረግ ይገኝበታል፡፡

ከዚህም ሌላ በኮሌጁ ቅጥር ግቢ በመገንባት ላይ ላይ የሚገኘው የእናቶችና ሕፃናት ሕክምና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ሲጀምር እጅግ ዘመናዊ፣ በአገሪቱ ሞዴል የሆነና በአንድ ጊዜ 60 ሕፃናትን ማስተናገድ የሚችል ክፍል እንደሚኖረውም አስረድተዋል፡፡